የማነ ብርሃን ውብጽጌ ይባላል፤ ትውልድ እና ዕድገቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ (ሰዴ ሙጃ) ልዩ ስሟ መንዝላማ በተባለች ውብ ገጠር አካባቢ ነው፡፡ ሲወለድ ሙሉ አካሉ ጤነኛ የነበረ ቢሆንም፣ ከዐይኑ አካባቢ በበቀለች ትንሽ ዕጢ ምክንያት ከሰባት ዓመቱ በኋላ የዐይን ብርሃኑን ሙሉ በሙሉ አጣ፡፡ የብርሃን መሸፈን ግን የራሱን ፍላጎትና ተስፋ አልሸፈነውም፤ ይልቁንም የጽናቱ መነሻ ሆነ፡፡
የማነ ብርሃን የዐይን ብርሃኑ ሲጨለመበት ታዲያ ቤተሰቡን ጨምሮ በአካባው ነዋሪዎች ጫና ይደርስበት ነበር፤ እናቱ ከአካባቢው ሰው በመሸማቀቅ ታፍርበትና ትጠላው እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ እህትና ወንድሞቹ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እሱ ግን ውሎው በቤት ውስጥ ነበር፡፡ የሚደርስበትን ጫና ለመግለጽ አውቆ ጥፋቶችን ያጠፋ እንደነበርም ይናገራል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥቂት የብርሃን ጭላንጭል ይታየው ስለነበር የቤተሰቡን ፍየሎችና ከብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡
በዚያ ሁሉ መከራ ውስጥ ግን የአባቱ ፍቅርና ድጋፍ ብቸኛ መጠጊያው ነበር፡፡ የማነ ብርሃን ለመማር የነበረውን ከፍተኛ ጉጉት የተረዳው አባቱ ታዲያ በቤት ውስጥ ፊደልና የግዕዝ ትምህርት እንዲቆጥር አገዘው፡፡
እኩዮቹ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ማየቱ ቁስል የሆነበት የማነ ብርሃን፣ የቄስ ትምህርት ለመማር ብሎ ከቤት ጠፋ፡፡ ሆኖም ቤተሰቦቹ ፈልገው መለሱት፤ ከባድ ግርፋት እንደደረሰበትም ያስታውሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተስፋ የሚያስቆርጡ ስድቦች በደርሱበትም የማ ብርሃን ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ “እንዳውም በውስጤ ብርታትን እንድሰንቅ አቅም ሆነኝ” ይላል፡፡ በዚህም በተደጋጋሚ መጥፋቱን የቀጠለው የማነ ብርሃን፣ አባቱ እጁን ሰጥቶ በአካባቢው ወደሚገኘው ገዳም ሚካኤል ቤተክርስቲያን ያስገባው ዘንድ አስገደደው፡፡
በዚያም ቁጥር፣ መልክዓ ማርያምና መልክዓ ኢየሱስን በትጋት አጠና፡፡ ሆኖም የዓይን ዕይታው ስለሌለ ለዕለት ጉርሱ መለመን ነበረበት፡፡ ለልመና በወጣ ቁጥር ግን ውሾች ያጠቁት ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ በሌሎች እጅ የመጠበቅን አስቸጋሪነት ተረድቶ የራሱን መንገድ ዘየደ፤ ወጥመድ በማዘጋጀት ጅግራዎችንና ቆቆችን እያጠመደ በመሸጥ የትምህርትና የምግብ ፍላጎቱን ማሟላት አሟላ፡፡
ከዚያም ይማርበት ከነበረበት አካባቢ ለቆ ወደ ጋይንት በመሄድ ዜማ ቤት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ አባቱ ሊጠይቀው ሲመጣ፣ የዜማ መምህሩ በሰጡት መልካም ምክር መሠረት አባቱ ወደ ደብረ ታቦር ሆስፒታል ወስዶት የዓይኑ ዕጢ በሕክምና እንዲወገድለት ተደረገ፡፡ ሆኖም ዕይታውን ማሻሻል አልተቻለም ነበር፡፡ ከሕክምናው መልስ ትምህርቱን ወደ ቅኔ ቤት በመቀየር ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ባሕር ዳር አመራ፡፡
ባሕር ዳር ጎርደማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንም የአቋቋም ትምህርቱን ጀመረ፡፡ በዚያም ሕይወቱን የለወጠውንና በጎ ተጽዕኖ ያሳደረበትን ወዳጁን ይኸይስን ተወዳጀ፡፡ ይኸይስ በባሕ ዳር ጎርደማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተዋወቀው ጓደኛው ነው፡፡
ይኸይስ ዘመናዊ ትምህርት ይማር ስለነበር የማነ ብርሃንንም በአጼ ሰርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል አስመዘገበው፡፡
የማነ ብርሃን “ልመናን አልወድም፤ የሰውን እጅ ማየትም አይፈልግም” ይላል፡፡ በመሆኑም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከደሴ ጭሳጭስ በማስመጣትና በመሸጥ ራሱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የማንንም ሰው እጅ ሳይጠይቅ፣ በራሱ ጥረትና ንግድ ፍላጎቶቹን እያሟላ አጠናቀቀ፡፡
የማ ብርሃን እንደሚናገረው ውጤቱ የጠበቀውን ያህል ባይሆንም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ በማምጣት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመግባት የግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርቱን ተከታተለ፡፡
“ግዕዝን የመረጥኩት በጣም ስለማነበውና ስለምወደው ነው፤ ወደፊትም በርካታ ምርምሮችን ለማድረግና የግዕዝ መምህር ለመሆን አቅጃለሁ” ሲልም ነው ያጫወተን፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታው በአጠቃላይ ሦስት ነጥብ ሦስት (3.3) ውጤት በማምጣት ከአካል ጉዳተኞች ተማሪዎች በላቀ ውጤት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘቱን በማንሳት ለሁሉም (በተለይ ለመምህሮቹ እና በፈተና ወቅት ለሚደግፉት አንባቢዎቹ) ምስጋና አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ታዲያ ያንን ሁሉ ፈተና በጽናትታግሎ አሸንፎ የስኬት ማማ ላይ ደርሷል፡፡ ትዳር መስርቶ፣ የራሱ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ቦታ አፍርቶ ይኖራል፡፡ ከራሱ አልፎ እገዛ የሚፈልጉ ሰዎችን የመርዳት አቅም መፍጠሩንም ነው ያጫወተን፡፡
የማነ ብርሃን እንደነገረን በቀጣይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ጠቃሚ አስተያየቶችን በመስጠት፣ አዲስ የጀመረውን ፕሮጀክት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመሥራት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
የየማነ ብርሃን ታሪክ ለሁላችንም ትልቅ ትምህርትን እና ተሞክሮን ይሰጣል፡፡ አካል ጉዳተኝነት የአዕምሮ ወይም የዓላማ ጉዳተኝነት አይደለም፡፡ “ማንኛውም ልዩ ፍላጎት ያለው ሰው፣ ሙሉ አካል ያላቸው ሰዎች ሲንቁትና ሲያንቋሽሹት ቅስሙ ሳይሰበር ያንን እንደ ማበረታቻና እንደ ትልቅ ተነሳሽነት መውሰድ አለበት፡፡ ጥረት ካለ የማይሳካ የለም፡፡ እውነተኛ ጥረት ሲኖር፣ ትናንት ያገለሉህና የናቁህ ሁሉ ዛሬ ወደ አንተ መቅረባቸው አይቀሬ ነው” ሲልም ነው መልዕክት ያስተላለፈው፡፡
መረጃ
ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የሚደረግ ድጋፍ በሰብአዊ መብት፣ በእኩል ተሳትፎ እና በክብር የመኖር መብት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።በዚህም ዋና ዋና የድጋፍ ዘርፎች የሚከተሉት ናቸው
- የመሰረተ ልማት እና የአካል ተደራሽነት
- የትምህርት እና ስልጠና ድጋፍ
- የጤና እና የመልሶ ማቋቋም (Rehabilitation) አገልግሎት
- የኢኮኖሚ እና ስራ እድል ፈጠራ
- ማህበራዊ እና ህጋዊ ከለላ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ዋናው ነጥብ፡ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የሚደረግ ድጋፍ የችሮታ ወይም የእርዳታ ጉዳይ ሳይሆን የመብት እና የእኩል ተሳትፎ ጉዳይ ነው!
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


