በምክክር ችግርን እንፍታ ሀገርን እናጽና!

0
44

ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩና ያንን ልዩነት ለመፍታት በታለመ ሁሉን አቀፍ ውይይት   የሚካሄድ ነው፡፡ ይህ ሂደት በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ አለመግባባቶች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባትን ለመፍጠር  በሀገራዊ ባለቤትነት የተያዘ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው የምክክር ሂደት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በበኩሉ ሀገራዊ ምክክር ማለት በአዋጁና የኮሚሽነሮች ምክር ቤት በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በሚለዩ አጀንዳዎች ላይ በተለያዩ አካላት የሚካሄድ ውይይት ነው፡፡ ውስብስብ የለውጥ ሂደቶችን ለመቆጣጠር ምክክርን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ሰፋ ባለ መልኩ ባለድርሻ አካላትን አካቶ ይካሄዳል፡፡ በሂደቱም በተለምዶ ውስን ሊሂቃን ብቻ ከሚያደርጉት ውይይትና ስምምነት ወጥቶ ሰፊውን የህበረተሰብ ክፍል በማካተት ወደ አሳታፊነት በማሳደግ ይካሄዳል፡፡

ሀገራዊ ምክክሮች የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ይካሄዳሉ፡፡ ዓላማቸውን መሰረት በማድረግም የአጭር ጊዜ ግብን ለማሳካት የሚካሄድ ሀገራዊ ምክክር አንዱ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ምክክር የሚደረገው በዋናነት ቀውስን ለመከላከልና የተፈጠሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ታስቦ ነው፡፡ ምክክሩ በአጭር ጊዜ፣ በውስን ጥረትና የሚመለከታቸውን ሀይሎች ብቻ በማሳተፍ የሚካሄድ ሲሆን ሊፈጠር የሚችል ቀውስንና ግጭትን ለመከላከለል ወይም የተፈጠረ ቀውስን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውል የምክክር ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሂደት ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚከናወን ሲሆን የፖለቲካ ውዝግቦችን በመፍታት መለስተኛ የሆነ መግባባትን እንደገና ለመፍጠር ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህ ሂደት የአጭር ጊዜ ግብ ያለው ሲሆን ጥቂት ተልዕኮዎች እና አጭር ቆይታ ይኖረዋል፡፡ በምክክሩ የሚሳተፉት አካላት ውስን ቁጥር ያላቸው በመሆናቸው የምክክር ሂደቱን ለማከናወን ይቀላል፤ ሰፊ መሰረት ያለው እና አካታች የሆነ ምክክርን የግድ አይጠይቅም፡፡

መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ሀገራዊ ምክክር ደግሞ በባህሪው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ፣ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያካትት፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ መሰረታዊ ልዩነቶች ላይ በማተኮር ልዩነቶቹን ለማጥበብ የሚደረግ ምክክር ነው፡፡ በውጤቱም የመንግሥትና ማኅበረሰብ ግንኙነቶችን እንደገና ለመወሰን ወይም አዲስ ማህበራዊ ውል ለመመሥረት የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን ሀገርን ወደ አዲስ የዲሞክራሲና ልዩነቶችን ከሀይል አማራጭ ይልቅ በመመካከር የመፍታት ባህልን ለማዳበር መሰረት የሚጥል የምክክር ዓይነት ነው፡፡

አንዳንድ ሀገራዊ ምክክሮች ሁለቱንም ያጣመረ ዓላማ ይዘው የአጭር ጊዜ ችግሮችን ለመፍታትና ላለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ይካሄዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የምክክር ዓይነት ሁለቱንም ዓላማዎች የያዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግስትና እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙት የማሻሻል፣ መተማማን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠር፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ  የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ  በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሠላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካና የማህበራዊ መደላድል ለማመቻቸት እንዲሁም ለሀገራዊ መግባባትና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባትም ያስችላል፡፡

 

ምክክር በሀገር ደረጃ ሲደረግ የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር፣ ሰላምን የሚያስፍን እና ሀገርን ወደተሻለ እድገት የሚመራ ታላቅ መሳርያ ነው፡፡ በአጠቃላይ ምክክር ሀገርን ከብተና እና ከውድቀት የሚታደግ፣ የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠናክር ወሳኝ ሀገራዊ መደላደል ነው፡፡ ምክክር ሀገርን ለማረጋጋት እጅግ መሠረታዊ እና ምትክ የሌለው መሣሪያ ነው፡፡ በኃይል ወይም በግዴታ የሚመጣ ሰላም ጊዜያዊ ሲሆን፣ በምክክርና በውይይት የሚገኝ መረጋጋት ግን ዘላቂ እና አስተማማኝ ነው፡፡

በአጠቃላይ ምክክር የጊዜ፣ የገንዘብ እና የጉልበት ብክነትን በመቀነስ ወደ ተሻለ እድገት የሚያመራ ሰላማዊ መንገድ ነው።

ስለሆነም፣ የጥላቻ ድምፆችን ትተን፣ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ሁሉም በሩን በሰፊው የሚከፍትበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ የመንግሥት፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና እያንዳንዱ ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የዜጎችን ድምፅ በጥንቃቄ በማዳመጥና በመደማመጥ መፍትሔ መፈለግ የሁሉም ኃላፊነት ነው። የሀገራችንን ሠላም ለመመለስ ሁሉም በእኩልነትና በፍትሀዊነት የሚኖርባትም እንድትሆን ዛሬውኑ በቅንነት እና በእውነተኛ መደማመጥ ለመመካከርና መፍትሔ ለማምጣት ልብን መክፈትና  እጅን ለሠላም መዘርጋት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

 

በኲር የሐምሌ 27  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here