የፋሲል ግንብ

0
132

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁ? ደኅና ናችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች በዚህ ሳምንት ጽሑፋችን ደግሞ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የሚገኘው የፋሲል ቤተ-መንግስትን በምናብ እናስጎበኛችኋላን፡፡

ልጆችዬ – ፋሲል ግቢ ወይንም ነገሥታት ግቢ በጎንደር ከተማ የሚገኝ የቤተ-መንግስታት ግምቦች ስብስብ ነው። ልጆች ግቢው የተመሰረተው በ1628 ዓ.ም. በዓፄ ፋሲለደስ ነበር።  ፋሲል ቤተመንግስት  በግቢ ውስጥ በስተደቡብ የተቀመጠ ሲሆን ሁለት ፎቅና 123 ደረጃዎች ያሉት ህንፃ ነው። ከጣሪያው ላይ ባለው መመልከቻ በረንዳ እስከ ጣና ሐይቅ ድረስ መመልከት ይቻላል። በውስጡ 20 ክፍሎች ሲኖሩት ከላይ የሚገኙት ክብ ክፍሎች ለጸሎትና መሰል የሃይማኖት ሥራዎች ንጉሱ ይጠቅምበት እንደነበር ይነገራል። ከላይ ያለው ጠፍጣፋው ክፍል ደግሞ ንጉሱ ለህዝቡ የሚናገሩበት ነበር፡

ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር 900 ሜትር ርዝመት ሲኖረው በውስጡ 70 ሺህ ስኩየር ሜትር የመሬት ይዞታ ያካልላል። አጼ ፋሲለደስ የመጀመሪያውንና ታላቁን ግንብ ያሠሩ እንጂ፣ ከርሳቸው በኋላ የተነሱት ነገሥታትም ለ220 ዓመታት የየራሳቸውን ህንጻ በመስራት ቦታው በቅርስ እንዲዳብር አድርገዋል። በግቢው የመጨረሻውን ህንጻ ያሠራችው ደግሞ ንግሥት ብርሃን ሞገስ ትባል ነበር።

ልጆችዬ- ፋሲል ግቢ፣ የውሃ እጥረት እንዳይገጥመው በማሰብ በአንገረብ እና ቀሃ በተሰኙ ሁለት ወንዞች መካከል ነበር የተመሰረተው። ከግቢው በስተደቡብ የጎንደር አደባባይ ሲገኝ፣ ቦታው ለገበያነት፣ ለአዋጅ መንገሪያነት እና ለወንጀለኛ መቅጫነት ያገለግል ነበር።

በአሁኑ ወቅት የጎንደር ከተማ መናፈሻ በመሆን ያገልግላል። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር ግምብ በዙሪያው 12 በሮች ሲኖሩት፣ እነዚህ በሮች ግልጋሎታቸውን የሚወክሉ ስያሜ ነበሯቸው። አንዳንዶቹ በሮች ከውጨኛው አለም ጋር ይገናኙ የነበሩት በትላልቅ ድልድዮች ነበር። ምንም እንኳ አብዛኞቹ የግቢው ቤቶች በጦርነትና እሳት ቢወድሙም ዋና ዋናዎቹ ህንጻዎች ግን እስከ አሁኑ ዘመን ዘልቀው ይታያሉ።

ከእነዚህ ጉልህ ህንጻዎች መካከል የፋሲለደስ ግምብ፣ ትንሹ የፋሲል ግምብ፣ የታላቁ እያሱ ግምብ፣ የዳዊት ፫ ዙፋን ቤት፣ ምንትዋብ ግምብ፣ የምንትዋብ መዋኛ፣ የፈረሶች ቤት፣ የፈረሰኞች አለቃ ቤት፣ አንበሶች ቤት፣ የበካፋ ግምብ፣ የበካፋ ሰገነት፣ የቀዳማዊ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት፣ ዮሐንስ ቤተ መጻሕፍት፣ አዋጅ መንገሪያን፣ ክረምት ቤት፣ ቋል ቤት(የሰርግ ቤት)እና ግምጃ ቤት ማርያም፣ አጣጣሚ ሚካኤል የሚሰኙ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል። በተጨማሪ ከፋሲል ግቢ ወጣ ብሎ በስተሰሜን ራስ ግምብ ይገኛል።

ተረት

ፀሐይ እና ነፋስ

ልጆች አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ ፀሐይና ነፋስ ረጅም መንገድ አብረው ጉዞ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ጓደኛሞች አብረው እየሔዱ ጨዋታ አንስተው ሲያወሩ ነፋስ ፀሐይን አንድ ጥያቄ ጠየቃት «ሰዎች የምትፈልጊውን ነገር እንዲያደርጉልሽ የምታደርጊያቸው በምንድን ነው?» ሲል ነፋስ ጠየቃት ፀሐይም የነፋስን ጥያቄ ሰማችና «እኔማ ከሰዎች የምፈልገውን መጠየቅ ብፈልግ በጣም ቢቆጡ፣ ቢሳደቡ እንኳን ቀስ አድርጌ በትህትና በፍቅር ረጋ ብዬ እጠብቃቸውና የምፈልገውን እንዲሰጡኝ /እንዲያደርጉልኝ/ አደርጋለሁ» አለችው፡፡

ነፋስ ወዲያውኑ ቀበል አደረገና ‘‘በጣም ተሳሳትሽ የምን መለማመጥ? የምትፈልጊውን ለማግኘት በጉልበት መጠቀም ነው እንጂ’’ አለ፡፡ ‘‘ፀሐይ እንደሱማ አይቻልም’’አለች፡፡

ነፋስም እኔ እችላለሁ ተመልከች ‘‘ያ’’ መንገድ ላይ የሚጓዘውን ሰውዬ በደቂቃ ውስጥ ልብሱን በየተራ ብትንትን አድርጌ አስወልቀዋለሁ’’ሲል ፎከረ፡፡ ነፋስም በአንዴ ኃይሉን አነሣና የሰውየውን ልብስ ለማስወለቅ መታገል ጀመረ፡፡ ይኼኔ ሰውየው ልብሱን እንዳይወስድበት በኃይል ልብሱን ጭብጥ አድርጎ አስጣለ /አዳነ/፡፡ ነፋስም ሰውየው ስላሸነፈው ተናደደና አቧራ አስነሥቶ ሰውየው ዐይን ላይ በትኖበት ጥሎት ሔደ፡፡ ፀሐይም በመገረም እየተመለከተችው “እሺ አያ ንፋስ አሸንፈህ የፈለከውን አገኘህ’’ ብላ ጠየቀችው ነፋስም ‘‘ይገርምሻል ልብሱን አልለቅም ሲለኝ አቧራ አንሥቼ ዐይኑ ላይ ጨመርኩበት’’ አላት፡፡

ፀሐይ ሳቅ እያለች «አይ አያ ነፋስ፡፡ በትግል አልሆን ሲልህ በጉልበት ለመጠቀም ሞከርክ? ግን እንደዚህ አይደለም እኔን አስተውለህ ተመልከተኝ’’ አለችውና ልታሳየው ወደ ሰውየው ሔደች፡፡

ሰፊ ከሆነው ከሰማይ መቀመጫዋ ብድግ አለችና ሰውየውን ገና ጠዋት ከሚመጣው ሙቀቷ ሰላምታ አቀረበችለት ሰውየውም የፀሐይን ሙሉ ፈገግታና ትህትና በጣም ደስ አሰኝቶት ከሙቀቷ ስር ቁጭ አለ፡፡ እንደገና ከሰዓት በኋላ መንገድ ሲሔድ ሰላም አለችውና ከሙቀቱ ጭምር አደረገች፡፡ ‘‘በጣም ስለሞቀህ ለምን ኮትህን አታወልቅም?’’ ስትል ጠየቀችው ደስ ብሎት ምንም ሳይከፋው ፈጠን ብሎ  ‘‘እሺ’’ አለና ውልቅ አድርጎ ያዘው፣ አሁንም ሙቀቷን ጨመረችና ‘‘ሸሚዙን ብታወልቀው’’ አለችው አወለቀው ሙቀቷ በጣም እየጨመረ መጣ፡፡

‘‘ለምን በቀዝቃዛ ውኃ አትታጠብም ስትል ቀስ አድርጋ ጠየቀችው በጣም ደስ ይለኛል አለና  ሰውነቱን በቀዝቃዛ ውኃ አስነከረችው፡፡’’

ይሔኔ ነፋስ በጣም ደነቀው፡፡ በራሱ ኃይለኝነት በጣም አፈረ፡፡ ሰዎች ነፋስን ብርድ በመጣ ቁጥር የበለጠ እየፈሩት ወደ ሙቀት እንደሚሸሹት አወቀ፡፡ ፀሐይ ግን በትህትና በፍቅር ሰዎችን ስለምትቀርብ ወደ ቅዝቃዜ ብትወስዳቸው እንኳን ቅር አይላቸውም፡፡ በደስታ እንደሚከተሏት ተመለከተ፡፡ የፀሐይን ጥሩ ፀባይ በጣም አደነቀ፡፡

አዎን ልጆች ከሰፈር አብሮ አደጎቻችሁ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ እንዲሁም ከወላጆቻችሁ ጋር ስትኖሩ የምትፈልጉትን ለማግኘት በመሳደብ፣ በኃይል፣ በመማታት አይደለም፡፡ ነፋስን አይታችኋል አይደል? ክፉና ኃይለኛ መሆን ሰዎች እንዲርቁን እንዲጠሉን አዋቂዎችም እንዲረግሙን ያደርገናል፡፡ እና ልጆች ልክ እንደ ፀሐይ ጥሩና ደግ ትሁትና ታዛዥ ሆናችሁ ሰዎትን ብትቀርቡ ሁሉም ይወዳችኋል፣ ይመርቃችኋል፡፡

ሞክሩ

  1. ቅኝ ገዥነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገች ሀገር ማን ናት?
  2. የሰው ልጅ ስንት የደም ዓይነቶች አሉት?
  3. ድምፅ በጠጣር ነገር ላይ በሰከንድ ስንት ሜትር ይጓዛል

መልስ

1.ፓርቹጋል

2.ሦስት

3.5960 ሜትር

 

ነገር በምሳሌ

  • ልብ ሳይገዙ፣ ነገር አያብዙ

ድፍረቱ ሳይኖርህ አደርጋለሁ አትበል፤

  • ሶስት ጊዜ ለካ፣ አንድ ጊዜ ቅደድ፤

ከመጀመርህ በፊት ደግመህ አስብ፤

  • ስንቅህን ባህያ፣ አመልህን በጉያ፤

ባህሪህን ወደ ውጭ አታንፀባርቅ፤

  • ለሹመት ካልመከሩለት ለጥርስ ካልከደኑለት፤

ለመሾም ቅድሚያ ሰውዬውን ማወቅ ያስፈልጋል

  • ልብ ዳኛ ዓይን እረኛ

ያዩትን ለመፈፀም የሕሊና ፈቃድ ያሻል።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here