የነፍስ ጩኸት

0
137

የጊታሩ አውታር ሲመታ የተለየ የነፍስ ህመም ይደመጣል። ድምፁ ለስላሳ ነው፤ ነገር ግን ልብን ሰንጥቆ ይገባል።

ግጥሞቹ የናፍቆት፣ የትካዜ፣ የብቸኝነት እና የጽናት ውሕድ ናቸው። አድማጩን ወደ ጥልቅ የስክነት እና የጥሞና ዓለም ይዘውት ይጓዛሉ። በትዝታ ይዘፍቁታል። ይህ ዜማ ብሉዝ (Blues) ይባላል። ብሉዝ ሙዚቃ ብቻ አይደለም፤ የሰው ልጅ የህልውና ትግል፣ የነፍስ ስሜታዊ መታደስ እና የታሪክ ሰነድ ነው።

ለመሆኑ ይህ አፈታሪካዊ የሙዚቃ ዘውግ የት፣ በማን፣ እንዴት እና ለምን ተጀመረ? የነርቭ ሳይንስ  ስለዚህ ህመም አዘል ሙዚቃ ፈውስነት ምን ይላል? ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋርስ ያለው  ውርርስ ምንድን ነው?

የብሉዝ ሙዚቃ  አመጣጥ ታሪክ በደስታ የተሞላ ሳይሆን በወደቁ የሰው ልጅ እንባዎች እና በሰንሰለት ድምፅ የታጀበ ነው። የጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ በአሜሪካ ደቡባዊ ግዛቶች (በተለይም በሐይቁ አቅራቢያ በሚገኘው የሚሲሲፒ ዴልታ ውስጥ ነው።

ብሉዝ የተወለደው ከአፍሪካ ተወስደው በባርነት ቀንበር ሥር በሚያቃስቱ ጥቁር አፍሪካውያን አሜሪካውያን እጅ ነው። በእርሻ ቦታዎች (በተለይም በጥጥ ማሳዎች) ላይ የሚሰሩ ባሪያዎች ድካማቸውን፣ ጭቆናቸውን፣ የነፍስ ቁስላቸውን እና የነጻነት ጥማታቸውን ለመግለጽ የሚዘፍኗቸው የሥራ ዜማዎች፣ እንጉርጉሮዎች እና ሃይማኖታዊ  ዜማዎች የብሉዝ መሠረቶች ናቸው።

“ብሉዝ” የሚለው ስም የመጣው “In the Blue Devils” (በከባድ ትካዜ እና ጭንቀት ውስጥ መሆን) ከሚለው ዘይቤያዊ አባባል እንደሆነ ይነገራል። ባሪያዎቹ መከራቸውን እና ሰብአዊ ክብራቸውን ማስጠበቂያ መንገድ አድርገው ጊታር፣ ባንጆ እና ሃርሞኒካ  በመጠቀም የነፍሳቸውን ጩኸት በዜማ ቀረፁት።

ብሉዝ ሙዚቃ የጥሪ እና መልስ ስልት ይከተላል።  ድምፃዊው አንድ ስንኝ ሲናገር፣ ጊታሩ ወይም ሃርሞኒካው መልስ  ይሰጣል። ጊታሩ እንደ ሁለተኛ ዘፋኝ ሆኖ ያሰማል፤ ይቃሰታል፤ ይጮሃል። አንዳንድ ጊዜ ከዘፋኙ በላይ ጊታሩ ልብን ሰርስሮ የመግባት አቅም አለው።

በምዕራባውያን የሙዚቃ ኖታ ውስጥ  የማይገኙ በ3ኛ፣ በ5ኛ እና በ7ኛ ኖታዎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቅን የድምፅ ማሳነሶች አሉት። ይህም ጊታሪስቱ የአውታሩን ድምፅ ወደ ላይ በመጎተት የሰው ልጅ የለቅሶ እና የቁስል ድምፅ እንዲያወጣ ያደርገዋል። ብሉዝ ወደ ሰው ስሜት ጠልቆ የሚገባው በዚህ ስልት ነው።

በቶሮንቶ  እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች የተደረጉ የነርቭ ሳይንስ ጥናቶች ለረጅም ጊዜ ሲያጠያይቅ የነበረውን ጥያቄ መልሰዋል። ይህም ጥያቄ “ሰው ለምን ሃዘን እና ትካዜ የሚበዛበትን ብሉዝ ሙዚቃ አዳምጦ ይረጋጋል?” የሚል ነበር። እንደ ነርቭ ሳይንቲስቶች ገለጻ አንድ ሰው ብሉዝ ሲያደምጥ በአንጎሉ ውስጥ አስደናቂ ባዮኬሚካላዊ ሂደቶች ይከናወናሉ።

አንደኛው የፕሮላክቲን  እና ኦክሲቶሲን  ኬሚካሎች መለቀቅ ነው። አንጎላችን የብሉዝን አሳዛኝ እና ትካዜ አዘል ዜማ ሲሰማ አካላችን እውነተኛ ህመም ወይም ኀዘን ውስጥ እንደገባ ያስባል። ይህንን ህመም ለማስታገስ አንጎል ፕሮላክቲን የተባለውን ማረጋጊያ ሆርሞን (በልቅሶ ጊዜ የሚለቀቅ) ይረጫል። ነገር ግን እውነተኛ አደጋ ስለሌለ ሆርሞኑ አድማጩ ላይ ጥልቅ የስክነት እና የመረጋጋት ስሜት ይፈጥራል።

ሁለተኛው ዶፓሚን የተባለው ኬሚካል ይመረታል። የብሉዝ ጊታሪስቶች አውታሩን ሲስቡ አንጎል ድምፁ ወዴት እንደሚሄድ ለመገመት ይሞክራል። ያልተጠበቀው የድምፅ መዛነፍ በነርቭ ደረጃ የደስታ ሆርሞን የሆነውን ዶፓሚን  እንዲለቀቅ ያደርጋል።

ሦስተኛው ነገር ስሜታዊ ማጽዳት መከሰቱ ነው። ብሉዝ ያደመጠ ሰው የራሱን የተጨቆነ ህመም በሙዚቃው ውስጥ ስለሚያየው የአንጎሉ አሚግዳላ (የስሜት ማዕከል) ረክቶ የጭንቀት ሆርሞን (ኮርቲሶልን) መቀነስ ያሳያል።

ብሉዝ በብዙ  ድምፃውያን እና አቀናባሪዎች የተገነባ ነው።  ሮበርት ጆንሰን የዴልታ ብሉዝ አባት ይባላል። በ1930ዎቹ “ጊታር የመጫወት ጥበብ ለማግኘት አራት መንገዶች በሚገናኙበት መስቀለኛ መንገድ  ላይ ነፍሱን ለዲያብሎስ ሸጠ” የሚል አፈ-ታሪክ ተሰራጭቶበታል። የእሱ “ክሮስ ሮድ ብሉዝ” እና “ስዊት ሆም ቺካጎ” የሙዚቃው መሠረቶች ናቸው።

ቢ.ቢ. ኪንግ የብሉዝ ንጉሥ ነው። “ሉሲል” ብሎ በሚጠራት ጊታሩ በሚጫወተው ነጠላ ኖት  ዓለምን ማርኳል። “ዘ ትሪል ኢዝ ጎን” የተሰኘው ዜማው በዓለም ታሪክ ከታወቁ ዘፈኖች አንዱ ነው።

ማዴ ዋተርስ ብሉዝን ከገጠር ወደ ከተማ (ቺካጎ) በማምጣት የኤሌክትሪክ ጊታር በመጠቀም “ቺካጎ ብሉዝ”ን ፈጠረ። ” ሆቼ ኮቼ ማን” ዘፈኑ በዓለም ይታወቅለታል። ቤሲ ስሚዝ  እና ማ ሬይኒ “የብሉዝ እቴጌዎች” በመባል የሚታወቁ የሴቶችን በደል እና ጥንካሬ በብሉዝ ያበሰሩ ፈርቀዳጆች ናቸው።

ታዋቂው የብሉዝ ሙዚቀኛ ዊሊ ዲክሰን እንደተናገረው ብሉዝ ሥሩ ነው፤ ሌሎቹ የሙዚቃ ዘውጎች በሙሉ የብሉዝ ፍሬዎች ናቸው።

ብሉዝ ለዘመናዊው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የሰጠው አስተዋፅዖ መለኪያ የለውም። የሮክ ኤንድ ሮል  እና ፖፕ መወለድ የመጣው ከብሉዝ ነው። ኤልቪስ ፕሬስሊ፣ ዘ ቢትልስ፣ ዘ ሮሊንግ ስቶንስ እና ኤሪክ ክላፕተን በሙሉ የብሉዝ ቀጥተኛ ውጤቶች ናቸው።

ብሉዝ የጃዝ፣ አር ኤንድ ቢ እና ሂፕ-ሆፕ መሠረት ነው። የብሉዝ የኮርድ መዋቅር እና የስሜት አቀራረብ እነዚህን ሁሉ ዘውጎች ወልዷል። ብሉዝ ለዘመናዊ ሙዚቃ የጊታር ቴክኒኮች መሠረት ጥሏል። ዛሬ በዓለም ላይ የሚሠሩ የጊታር ሶሎዎች እና አጫዋዎቶች በሙሉ የብሉዝ ጊታሪስቶች የፈጠሯቸው ቴክኒኮች ናቸው።

በአፍሪካ አሜሪካውያኑ ብሉዝ እና በኢትዮጵያውያን ትዝታ መካከል ያለው ተመሳሳይነት አስደናቂ ነው። ሁለቱም የሙዚቃ ስልቶች በቦታ ቢራራቁም በነፍስ ግን መንትዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ትዝታ ቅኝት እና የብሉዝ ቅኝት ሁለቱም ባለ አምስት ኖት (ፔንታቶኒክ) መሠረት አላቸው። ሁለቱም በድምፅ መካከል የሚደረጉ ጥቃቅን መዛነፎችን (Microtones) በመጠቀም የህመም እና የትካዜ ስሜት ይፈጥራሉ።

ብሉዝ ስለ ማጣት፣ ናፍቆት እና ጽናት እንደሚዘፍነው ሁሉ የትዝታ ቅኝታችንም ከወደድነው ስለመለያየት፣ ስለ አገር ናፍቆት እና ስለ ህይወት ትካዜ ይዘፍናል።

የኢቲዮ-ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ የኢትዮጵያን ቅኝቶች ከብሉዝ እና ጃዝ ስኬሎች ጋር በማዋሐድ የዓለምን ትኩረት ስቧል። መሐሙድ አህመድ እና አለማየሁ እሸቴ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ፈርቀዳጆች ሆነው የብሉዝን ብራስ መሳሪያዎች አጠቃቀም እና የነፍስ ጩኸት ስልት ከትዝታ፣ ከባቲ እና ከአንቺ ሆዬ ጋር አዋህደውታል። ዓሊ ቢራ የኦሮሞን ባህላዊ ዜማዎች ከብሉዝ አኮስቲክ ጊታር አጫዋወት ጋር በመቀላቀል የማይረሱ ዜማዎችን አበርክቷል።

ዛሬም ቢሆን የኢትዮ-ብሉዝ ባንዶች የሁለቱን ዓለም አውታሮች በማዋሐድ ድንቅ የሙዚቃ ጣዕም ለዓለም ያቀርባሉ።

ዛሬ ብሉዝ በንግድ ደረጃ እንደ ፖፕ ሙዚቃ ገበያውን ባይቆጣጠረውም እንደ ዘላለማዊ የሙዚቃ መቅደስ ይቆጠራል። እንደ ጋሪ ክላርክ ጁኒየር፣ ጆ ቦናማሳ እና ኪንግፊሽ  ያሉ ወጣት ተተኪዎች ብሉዝን ከዘመናዊ ሂፕ-ሆፕ እና ሮክ ጋር እያዋሐዱት ይገኛሉ። ብሉዝ ዛሬም ቢሆን እውነተኛ ሙዚቃን፣ የቀጥታ የስታዲየም ኮንሰርቶችን እና ጥልቅ ስሜትን የሚሹ አድማጮች መጠጊያ ነው።

በ1977 ዓ.ም ናሳ  ቮየጀር አንድ የተሰኘችውን መንኮራኩር ወደ ጥልቅ አጽናፈ-ዓለም (ጥልቁ ሕዋ) ሲልካት ከምድር ውጭ ያሉ ህይወት ያላቸው ፍጥረታት (ኤሊያንስ) ካሉ የሰው ልጅን ማንነት፣ ስልጣኔ እና ነፍስ እንዲረዱ የታሸገ የወርቅ ሲዲ አብሮ ተልኮ ነበር። በዚያ ዲስክ ላይ ከተቀረጹት ጥቂት የሰው ልጅ ድንቅ ታሪኮች መካከል አንዱ የብሉዝ አባቱ የብላይንድ ዊሊ ጆንሰን “ዳርክ ዎዝ ዘ ናይት፣ ኮልድ ዎዝ ዘ ግራውንድ” የተሰኘው የብሉዝ ዜማ ነበር።

ማረፊያ

ዕደጉ

 

እናንት ወጌሻዎች

የአዳምን ዘር ማንዘር

ወግ የምታስይዙ፣

ኃፍረተ ሥጋውን

ዘወትር በስለት

ከምትገዘግዙ፣

እስቲ ከፍ በሉና…

ጭንቅላት ግረዙ።

ቴዎድሮስ ፀጋዬ (ነፍሰጡር ስንኞች)

(አቢብ በዓለሜ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here