በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ መካከል ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 162 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው -የዝዋይ ሐይቅ፡፡ ሐይቁ ቀደም ብሎ የዝዋይ ሐይቅ ይባል ነበር – በቅርበት የምትገኘው ዝዋይ ከተማን መነሻ አድርጐ፤ አሁን ላይ ከተማዋ ባቱ ሐይቁም የደምበል ሐይቅ የሚል ስያሜ መያዛቸውን ድረገፆች አስነብበዋል፡፡
የኃይቁ ስፋት 434 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡ ሐይቁን በደቡብ ምስራቅ የካታር ወንዝ፣ በሰሜን ምእራብ አቅጣጫ የመቂ ወንዝ ይመግቡታል፡፡ ከሐይቁ የሚወጣው ብቸኛ ወንዝ ደግሞ የቡልቡላ ወንዝ ነው፡፡
በሐይቁ መካከል ቱሉ ጉዶ፣ ፀዳቻ፣ ገሊላ፣ ፉንዱሮ እና ደብረ ሲና የተሰኙ ደሴቶች ይገኛሉ፡፡ ደሴቶቹም የዛዬ ጐሳ መኖሪያ ናቸው፡፡
የዝዋይ ሐይቅ ለባቱ እና መቂ ከተማ ኗሪዎች የገቢምንጭ ነው፡፡ አርሶ አደሮች አትክልት በማምረት ይተዳደራሉ -ከሐይቁ ውኃ በመሳብ፡፡
ሐይቁ አእዋፍ መመልከት ለሚሹ ጎብኚዎች ተመራጭ ነው፡፡ “ስቶርክ”ወይም አባኮዳ የተሰኘው ግዙፍ የወፍ ዝርያ ዓሳ ለመያዝ ሲሽቀዳደም ማየት ለጐብኚዎች ትልቅ ሀሴት ይፈጥራል፡፡ የሐይቁን ዙሪያ ዓሳ አስጋሪዎች እና ዓሳ ጥብስ ሻጮች ያደምቁታል፡፡ ከአባኮዳ በተጨማሪ “ዳርትስ፣ ሄሮይንስ ፣ ፔሊካን” የመሳሰሉት ዓእዋፍት የሐይቁ ጌጦች ናቸው፡፡
የዝዋይ ሐይቅ በ2018 እ.አ.አ በዩኔስኮ ተመዝግቧል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ ለአበባ ልማት 700 ሄክታር መሬት በመሰጠቱ በውኃ መሳቢያ ሞተር በቀን ከ115517 ሊትር መውጣቱ ተፅእኖ አድራሽ ሆኗል፡፡ በቅርበት የሚገኘው የመጠጥ ውኃ ማሸጊያ ኢንድስትሪም ሌላው የሐይቁን ውኃ በመሳብ ተጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ እና መሰሎች የሚያደርሱት ተፅእኖ በ70 ዓመታት ውስጥ ሐይቁን ሊያደርቁ ይችላሉ ተብሎም በስጋትነት ተቀምጧል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት እና በተቆርቋሪነት ስሜት መገልገል ፣ መጠበቅ እንደሚገባቸው ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው- በድረ ገፆች፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ብሪሊያንት ኢትዮጵያ፣ ሀስቲኪንግ እና ስኘሪንግስ-አርሲሲ ዶት ኦርግ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


