በኢትዮጵያ የሸማቾችን ጤንነት፣ ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመጠበቅ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ላይ ሰፍሯል። ሕጉ ሸማቾች ከእቃዎችና አገልግሎቶች እጥረት ወይም አደገኛ ሁኔታ እንዲጠበቁ ዋስትና ይሰጣል።
ሸማች ማን ነው?
ሸማች የሚለውን ቃል ሀገራት እንዳላቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል። በኢትዮጵያም ለሸማች የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 2 ንኡስ ቁጥር 4 ስር እንደተደነገገው ሸማች ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ እቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው እንደሆነ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ትርጉም ይዘት የሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል በሸማችነት ያልተካተተ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
የሸማች መብቶች
በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 14 መሰረት ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት፣ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት፣ የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ መብቶች አሉት፡፡
ሸማቹ በማንኛውም ነጋዴ በትሕትና እና በአክብሮት የመስተናገድ እንዲሁም በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ ፣የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ ወይም በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎችን በአንድነትና በነጠላ ካሳ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብቶቹ በአዋቹ ሰፍረዋል፡፡
የተከለከሉ ተግባራት
የሸማቹን መብቶች ከግብ ለማድረስ አዋጁ በአንቀጽ 22 ስር ነጋዴዎች ማድረግ የሌለባቸው የተከለከሉ ድርጊቶችን ዘርዝሯል፡፡ እነዚህም የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስላላቸው ጥራት፣ መጠን፣ ብዛት፣ ተቀባይነት፣ ምንጭ፣ ባህርይ፣ ስለጥቅሞቻቸው የተሳሳተ መረጃ መስጠት፣ የንግድ ዕቃዎችን ሞዴል፣ አዲስ የተሰሩ፣ የተለወጡ፣ እንደገና እንደ አዲስ የተሠሩ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለጽ የሌላውን ነጋዴ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች በአሳሳች ሁኔታ መግለፅ፣ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውሱንነት መኖሩን ካልገለፀ በስተቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን አለመሸጥ ፣ ስለዋጋ ቅናሽ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ ማስተላለፍ ናቸው፡፡
በአንቀጽ 22 ስር ነጋዴዎች ማድረግ የሌለባቸው የተከለከሉ ድርጊቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም፡፡ አንድ ሸማች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የአይነት ጥቅም እንደሚያገኝ በመግለፅ ከንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገቡ የዋስትና ግዴታዎችን አለመወጣት፣ የንግድ ዕቃዎች የሚያስፈልጓቸው ዕድሳት ወይም ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎቻቸው፣ እንደማያስፈልጋቸው አድርጎ ማቅረብ፣ ማንኛውም አገልግሎት የመስጠት ሥራን ከሚጠበቀው ወይም በንግድ ሥራው ከታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት የለበትም፡፡
ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆኑ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃቸው ከተቀመጡላቸው ደረጃዎች የወረዱ፣ የተመረዙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፉ ወይም ከባእድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፣ በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ግብይት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም፣ የሸማቹን መብት ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ”የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አልሸጥም” ማለት፣ የደረጃ ማሕተም የሚያስፈልጋቸውን የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ያለደረጃ ማሕተም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፣ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በንግድ ዕቃዎቹ ላይ ወይም በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ፣ የንግድ ዕቃዎች የተሠሩበትን ሀገር አሳስቶ መግለፅ፣ በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈፀም አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ፣ ሕገወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሳሪያ መጠቀምም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሕግ ተጠያቂነት
አዋጁ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ችሎት በነጋዴዎችና ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚወስደውን አስተዳደራዊ ርምጃ እና ቅጣት በአንቀጽ 32 እና 42 ስር ይደነግጋል። በዚህም ፀረ-ውድድር የሆኑ የንግድ አሠራሮችን ማለትም በበላይነት የተያዘ ገበያን አላግባብ መጠቀም፣ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ፀረ-ውድድር ስምምነት ወይም በህብረት የሚያዝ አቋም፣ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር እና ውህደትን በተመለከተ የተከለከሉ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙ በአንቀጽ 32 ንሱስ ቁጥር (2) መሰረት ተገቢ አለመሆኑ ገልጾ ድርጊት እንዲቆም የማድረግ፣ የተጎጂውን የመወዳደር አቅም ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ የሚያስችል ርምጃ የመውሰድ፣ የአጥፊው የንግድ ፈቃድ እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የማድረግ ርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል።
ከላይ ከተዘረዘሩት አስተዳደራዊ ርምጃዎች በተጨማሪ በአዋጁ በአንቀጽ 42 ስር ስለሚወሰዱ አስተዳደራዊ ቅጣቶች የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም በበላይነት የተያዘን ገበያ አላግባብ የሚጠቀም ነጋዴ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ፣ ፀረ-ውድድር ስምምነቶችን የሚያደርግ የዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን 10 በመቶ፤ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር የሚፈፅም የዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ፤ ውህደትን በተመለከተ የተከለከሉ ተግባራትን የሚፈፅም/በውህደት ድርጊት የሚሳተፍ ነጋዴ/ የዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል። ከላይ በተጠቀሱት ጥፋቶች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ ያደረገ ነጋዴ ያልሆነ ሰው ደግሞ ከ10ሺ እስከ 100ሺ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
ከአስተዳደራዊ ቅጣቱ በተጨማሪ የወንጀል ተጠያቂነት ሲኖረው ሸማች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የአይነት ጥቅም እንደሚያገኝ በመግለፅ በሸማቹ አሻሻጭነት ከእሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በሸማቾቹ ቁጥር ልክ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የአይነት ጥቅም እንደሚያገኝ የሚገልፅ የፒራሚድ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ ወይም ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር እንዲሁም ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆኑ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃቸው ከተቀመጡላቸው ደረጃዎች የወረዱ፣ የተመረዙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፉ ወይም ከባእድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ የዓመታዊ ሽያጭ ገቢውን ከ 7 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ መቀጮ እና ከ ሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 43 ንኡስ አንቀፅ (2) ስር ተደንግጓል።
በአዋጁ አንቀጽ 22 ስር ከተመላከቱ ክልከላዎች ውስጥ አንዱን የተላለፈ ማንኛውም ነጋዴ የዓመታዊ ሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ መቀጮ እና ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 43ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ተደንግጓል።
በተጨማሪም የአዋጁን አንቀጽ 24 በመተላለፍ የንድግ እቃዎችን አከማችቶ ወይም ደብቆ ወይም በሕገወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ የተያዘው የንግድ እቃ የሚወረስ ሆኖ የዓመታዊ ሽያጩን ከአምስት እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እና ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአንቀፅ 43 ንኡስ አንቀፅ (4) ተደንግጓል፡፡
የሕግ አንቀጽ
- የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 በአንቀፅ 14/1/ ስር ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛቸው እቃ ወይም አገልግሎቶች ጥራትና አይነታቸውን በተመለከተ በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት እንዳለው በግልፅ አስቀምጧል፡፡
- የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አ/ቁ 661/2002 በአንቀጽ 8 ንኡስ ቁጥር /1/ እና 16 ንኡስ አንቀፅ /1/ ስር በታሸገ የመድኃኒት ወይም የምግብ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ነጋዴዎች መድኃኒቱ ወይም ምግቡ ገላጭ ፅሑፍ ካልተደረገበት ለገበያ ሊያቀርቡት የማይችሉ መሆኑን በመግለፅ የተቀመጠ ድንጋጌ አለው፡፡
- አዋጅ ቁጥር 813/2006 ከወጣባቸው መሰረታዊ የሆኑ ዓላማዎች ውስጥ ዋነኛው ሸማቾች ለደህንነታቸው እና ለጤናቸው ተስማሚ የሆኑ የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን ማረጋገጥ እደሆነ በአዋጁ አንቀፅ 3 ንኡስ አንቀፅ /1/ ስር በግልፅ ሰፍሯል፡፡
- የንግድ ውድድር እና ሸማቾችና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀፅ 5፣ 7፣ እና 8 ስር ማንኛውም ነጋዴ በበላይነት ያያዘውን ገበያ ያላግባብ ለመጠቀም እንደማይችል፣ እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራትን መፈፀም ለማንኛውም ነጋዴ ክልክል መሆኑን አስቀምጧል፡፡
ምንጭ- የፌደራል አቃቢ ሕግ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


