የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዋንጫ እ.አ.አ የካቲት 8 ቀን 1957 በሱዳን ርእሰ ከተማ ካርቱም መመስረቱን ካፍ ኦንላይን ኒውስ እስታውሷል፡፡
መስራች ሀገራቱ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብጽ ነበሩ።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመኾን “የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ቡድኖች ዋንጫ”ን እአ.አ በ1964/65 የውድድር ዘመን መጠንሰሷን ‘አሌ’ የሚል ዘርፉን በአንክሮ የሚከታተል የስፖርት ባለሙያ ባይኖርም ማስታዎስ ግን ተገቢ ነው።
የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ቡድኖች ዋንጫ በብኵርና ወቅቱ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና የነጻነት አባት ስም «ክዋሜ ንክሩማህ ዋንጫ» ተብሎ ይጠራ ነበር። ኋላ ላይ ግን ስያሜው ከተዋቂ ግለሰብ ይልቅ በአኅጉሩ ስም ይጠራ የሚለው ድምጽ ሚዛን በመድፋቱ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ተቀይሮ እነኾ 62ኛ ዓመቱን እየተሻገረ ይገኛል ።
የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቡድኖች ዋንጫ በተጀመረ ማግስትም ኢትዮጵያ በምሥራቁ ጮራ ድሬ ዳዋ ኮተን የእግር ኳስ ቡድን ተወክላ በውድድሩ መሳተፍ መቻሏን ታሪክ በወርቃማ ቀለም ከትቦት እናገኘዋለን።
ድሬ ዳዋ ኮተን እስከ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በመዘለቅም የኢትዮጵያን ስም በበጎ አስጠርቷል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድንም እ.አ.አ በ1967ቱ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ቡድኖች ዋንጫ ውድድር እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የድሬ ዳዋ ኮተንን ፍኖት አስቀጥሏል፡፡
ድሬ ዳዋ ኮተን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድኖች በ1960ዎቹ አጋማሽ ጠንካራ ከነበሩት የአፍሪካ የእግር ኳስ ቡድኖች ጋር በመፎካከር እስከ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ እና ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሀገራቸውን ወክለው ተጫውተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣሙን በምድብ ድልድሉ በመግባት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን በመኾን በታሪክ መዝገብ ስሙ ሰፍሯል።
በ2026/2027ቱ የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ መርሐ ግብር 56 የእግር ኳስ ቡድኖች ለመፎካከር ተመዝግበው የጨዋታ ድልድል ውስጥ ገብተዋል።
በካፍ የ2025/2026 የደረጃ መለኪያ መሥፈርት መሠረትም ስምንት አውራ ቡድኖች አንደኛውን ዙር ‘ገድፈው’ በሁለተኛው ዙር በቀጥታ ወደ ውድድሩ የሚገቡ ይኾናሉ።
እነርሱም፦ አል አህሊ፣ አዛም ኤ.ፍሲ፣ ዩ.ኤስ.ኤ አልጀር፣ ሲ.አር ቤሉይዝዳድ፣ ራጃ ካዛብላንካ፣ አስ ፋር፣ አስ ማኒማ እና ካይዘር ቺፍስ የእግር ኳስ ቡድኖች ናቸው። 48ቱ ቀሪ ቡድኖች ደግሞ የመጀመሪያውን የቅድመ_ ቅድመ የማጣሪያ ጨዋታዎች ያደርጋሉ ሲል ካፍ ኦንላይን ኒውስ አስታውቋል።
በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ድል የሚነሱ ቡድኖች ሁለተኛውን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ይቀላቀላሉ፤ ከ56 ቡድኖች በሁለተኛው ለቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚበቁት 32 ቡድኖች ይኾናሉ ማለት ነው።
በዚህ ጨዋታ ስምንቱ አውራ ቡድኖች በድልድሉ ውስጥ ተካተው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያም በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በሲዳማ ቡና ተወክላለች።
ሲዳማ ቡና በ2018 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር 38 ጨዋታዎችን አድርጎ በ19 ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
በ11 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
ከ38 ጨዋታዎች የተሸነፈው በሰምንት ጨዋታዎች ነው።
ከጠቅላላው ጨዋታም 68 ነጥብ በመሰብሰብ የዋንጫ ባለቤት በመኾን ድሉን እያጣጠመ ይገኛል።
በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያን የወከለው ሲዳማ ቡና የቅድመ _ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውንም ከቻዱ ክለብ ኤግሎንስ ጋር የሚያደርግ ይኾናል።
መቀመጫውን ሃዋሳ ከተማ ያደረገው ሲዳማ ቡና ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል፡፡
የተለያዬ የአጨዋወት ሥልትን የሚከተሉ አዳዲስ ኹነኛ ተጫዋቾችንም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር በማዛወር ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።
ቡድኑ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ለሚጠብቀው አኀጉራዊ ጨዋታ ልምምዱን አጠናክሮ መቀጠሉን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ሲዳማ ቡና የመጀመሪያውን ጨዋታም ከሜዳ ውጭ የሚያደርግ ይሆናል።
ተጋጣሚው የቻዱ ንጃሜናው ኤግሎንስ ኤፍ.ሲ በቻድ ከፍተኛው ሊግ የ2025/2026 የውድድር መርሐ ግብር 22 ጨዋታዎችን አድርጎ በ18 ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
በአራት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
ቡድኑ በውድድር ዘመኑ የተሸነፈበት ጨዋታ የለም። 58 ነጥብ በመሰብሰብም የቻድ የውስጥ ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
የቡድኑ የኋላ የተከላካይ ክፍል ጠንካራ መኾኑ ይነገራል። ይሁን እንጅ የአጥቂው ክፍል የሚያወላዳ አይደለም። ግብ ጠባቂዎች ለአየር ላይ ኳሶች “አሞራ “ሲኾኑ በምድር የሚመጡ ኳሶች ግን ይፈትኗቸዋል ነው የተባለው።
የኾነው ኾኖ ሲዳማ ቡና ተጋጣሚው በቅርብ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ቪዲዮ በምልሰት በመመልከት 50+አንድ በልጦ መሥራት ይጠበቅበታል እንላለን፡፡
የኢትዮጵያው ተወካይ ሲዳማ ቡና ይህን ጨዋታ በድል የሚወጣ ከኾነም በሁለተኛው ዙር ከሱዳኑ አል ሂላል እና ከብሩንዲው ኤግል ኖይር አሸናፊ ከኾነው ቡድን ጋር የሚጫወት ይኾናል።
ወደ አፍሪካ ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አልፈናል። ይህ የውድድር ዓይነት የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ2004 ነው፡፡
ውድድሩ የቀድሞውን የካፍ ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አዋህዶ የተቋቋመ መኾኑን የካፍ መረጃ ያስረዳል።
ውድድሩ ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ትልቁ የአኀጉሩ የእግር ኳስ ቡድኖች ውድድር እንደኾነ ካፍ አስታውሷል፡ ፡
በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ታሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን በመወከል ብኵርና አለው፡፡
ቡድኑ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በማለፍ ታሪክ የሰራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ነው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስን ዱካ ተከትለውም ወላይታ ድቻ፣ ፋሲል ከነማ እና ባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድኖች በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክለው የተጫወቱ ባለታሪክ ቡድኖች ናቸው።
ዘንድሮ በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን መቀመጫውን አዲግራት ከተማ ያደረገው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ቡድን ነው።
ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከሱዳኑ ክለብ አል ሂላል አልሳሂል ቡድን ጋር ተደልድሏል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ክብር የበቃው በኢትዮጵያ ዋንጫ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሲሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአኀጉራዊ ዋንጫ ተሳታፊ ኾኖ ተደልድሏል።
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን በተጫዋቾች የክረምት ዝውውር በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። መሣ ለመሣም ለካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ወልዋሎ የመጀመሪያውን ጨዋታ በፖርት ሱዳን ስታዲየም ያካሄዳል ነው የተባለው።ይሁንና የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ወጣ ገባ በመኾኑ ጨዋታው የሚደረግበት ቦታ ሊቀየር እንደሚችል ካፍ ፍንጭ ሰጥቷል።
የመልስ ጨዋታው ደግሞ ከመስከረም 1 እስከ 3/ 2019 ዓ.ም ባሉት ቀናት ይደረጋል ነው የተባለው።
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን ተጋጣሚ የሱዳኑ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ አል ሂላል አል ሳሂል ኤስ.ሲ (በአጭሩ ሂላል አልሳሂል ይሉታል) በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ መስተጓጎል ደርሶበታል።
በሱዳን የሀገር ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታ ለረጅም ጊዜያት ሳንካ አጋጥሞታል ሲል ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል።
የትኛው ክለብ ማንን አስፈርሞ ውጤታማ ይሆናል ? ወደፊት በጋራ የምንመለከተው ነው።
(ሙዋ ሊሙ)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


