የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካዋ ሂዩጂን ኦሪገን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በድምቀት ተካሂዷል ።
የነገዎቹን ተስፈኛ አትሌቶች በሚጠቁመው በዚሁ ውድድር ላይ አሜሪካ በ12 ወርቅ፣ 7 ብር እና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ፣በድምሩ 24 ሜዳሊያዎችን በመሠብሠብ ውድድሩን በአንደኛነት አጠናቃለች ።
የምሥራቅ አፍሪካዋ ኬንያ በ4 የወርቅ ፣ 3 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሠብሠብ ከዓለም 2ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሀገር ሆና አጠናቃለች።
ጣሊያን፣ ጃማይካ፣ አውስትራሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና ሌሎች ደግሞ ከ3ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
የኬንያ አትሌቶች በቀጣይ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ለሀገራቸው የአትሌቲክስ ውጤታማነት አረንጓዴ መብራት የበራላቸው ተስፈኛ ሆነው ታይተዋል።
ኬንያ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችውን የኦሪገን ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን በአድናቆት ዘግበውላቸዋል። የነገ ብሩህ ተስፋቸውንም አመላክተዋል ።
ዘ ስታንዳርድ “ኬንያ በወጣት አትሌቶች ልማት ያላትን ጥንካሬ የሚያሳይ ማረጋገጫ ” ሲል ዘገባውን አስፍሯል ።
ዘ ስታር የተሰኘው የዘገባ ማዕከል ደግሞ የኬንያን ከ20 ዓመት በታች አትሌቶች ሥብሥብ “የኬንያ ከ20 ዓመት በታች ባታሊዮን ” ሲል ጠርቷቸዋል ። 4 ወርቅ ፣3 ብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማምጣት ከአስተናጋጇ አሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ መሆኗንም አጉልቶ ዘግቧል ።
ዘ ስታር በዘገባው የኬንያን ወጣት አትሌቶች ከማወደሱም በተጨማሪ ከአፍሪካ የኬንያ ቀንደኛ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብላ የተጠበቀችው ኢትዮጵያ በ6 ሜዳሊያዎች ከአውስትራሊያ ጋር በጋራ 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ዘግቧል ።
የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ስለ ኬንያ ወጣት አትሌቶች ሲዘግቡ “ለኬንያውያኑ ይህ የዛሬ ሜዳሊያ ብቻ አይደለም ፤የነገም ተስፋቸው ጭምር እንጂ ” በማለት ዘግበውላቸዋል።
የኬንያ ወጣት አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለይም በ1 ሺህ 500 ሜትር፣ በ3 ሺህ ሜትር እና በ5 ሺህ ሜትር ላይ ያሳዩት ጥንካሬ የኬንያ የሯጮች ትውልድ በቀጣይም የዓለምን የሩጫ መሞች ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ተተንብዮላቸዋል።
የኬንያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቶች በውድድሩ በአንደኛነት ካጠናቀቀችው አዘጋጇ አሜሪካ የበለጠ ውዳሴ የተቸራቸው በብዙ ምክንያቶች እንደሆነም የመገናኛ አውታሮቹ የየራሳቸውን አመክንዮ አቅርበዋል ።
ኬንያ እንደ አሜሪካ በርካታ ተሳታፊዎች የሌሏት መሆኑ ፣የአትሌቲክስ መሠረተ ልማቶቿ ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ ያነሱ መሆናቸው በምክንያትነት ከቀረቡት አንጓዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው ።
የኬንያ ሚዲያዎች የወጣቶቻቸውን ድሎች “የወጣቶቻችን ብርታት ፣የትውልድ አርዓያነት ፣የቀጣዩ አትሌቲክሳችን ጥሩ ምልክቶች እና አፍሪካን በዓለም መድረክ እንድንመራ ያስቻሉን” በሚሉ ደማቅ ዘገባዎች አወድሰዋቸዋል።
በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀት ሩጫ ዓለም የሚያውቃቸውና የሚያደንቃቸው አትሌቶች መፍለቂያ ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኬንያ እና ኢትዮጵያ መሆናቸው ይታወቃል ።
አበበ ቢቂላ እና ደራርቱ ቱሉ በሚሉ ስሞች የሚጀምረው የዓለም የወንዶች እና የሴቶች የረጅም ርቀት ሩጫ ድሎች ዛሬ ላይ በትውልድ ቅብብሎሽ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያንን አትሌቶች በመሙ ላይ አሳይቶናል ።በጎዳናዎች ላይም አስተዋውቆናል።
ማራቶን ፣ግማሽ ማራቶን ፣ሀገር አቋራጭ ፣10ሺህ ሜትር፣ 5 ሺህ ሜትር፣ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና ሌሎችም የረጅም ርቀት ሩጫዎች ሲነሱ ስማቸው አብሮ የሚነሳው የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ዛሬም ድረስ ለነዚህ ክብሮች ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው ።
የኬንያ ወጣት አትሌቶች የኦሪገን ድል በዓለም የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ አትኩሮት እና አድናቆት የተቸረው ከአሜሪካ ጋር በመፎካከራቸው ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በውድድሩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት ከኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች በልጠው በመገኘታቸውም ጭምር እንጂ።
ኬንያውያን ወጣት አትሌቶች በአዋቂዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የነገ የሀገራቸው ተስፋ መሆናቸውን በኦሪገን አሳይተዋል ። እኛስ ?
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


