“ኪንትሱጊ”

0
249

በጣም የምትወዱትና ትልቅ ዋጋ ያለው የሸክላ እቃ  ከእጃችሁ አምልጦ መሬት ላይ ቢወድቅና ቢከሰከስ ምን ታደርጋላችሁ?

አብዛኛው ሰው ይበሳጫል፤ የተሰበሩትን ስብርባሪዎች ሰብስቦ ወደ ቆሻሻ መጣያ ይጥላቸዋል። በጣም ከተቆጨ ደግሞ ስብርባሪዎችን በማይታይ ማጣበቂያ (ግሉ) ደብቆ ለማጣበቅ ይሞክራል።

ጃፓናውያን ግን ፈጽሞ እንዲህ አያደርጉም። የተሰበረውን እቃ ስባሪውን በጥንቃቄ ይሰበስቡታል፤ ከዚያም «ኡሩሺ» ከተባለ የተፈጥሮ ማጣበቂያ እና ከንጹህ የወርቅ ዱቄት ጋር በማዋሃድ የተሰበሩበትን ስንጥቆች በወርቅ አጣብቀው ይሰራሉ።

ውጤቱም እቃው ከመሰበሩ በፊት ከነበረው ይበልጥ ውድ፣ ማራኪ፣ ታሪክ አዘል እና በወርቃማ መስመሮች ያጌጠ ድንቅ የጥበብ ስራ ሆኖ ይወጣል!

ይህ ጥበብ “ኪንትሱጊ” ይባላል። ኪንትሱጊ የሸክላ ማጣበቂያ ስልት ብቻ አይደለም፤ “የተሰበረ ነገር፣ የታመመ ህሊና እና የተዛነፈ ህይወት ከመሰበሩ በፊት ከነበረው ይበልጥ ያምራል” የሚል ታላቅ አምላካዊና ስነ-ልቦናዊ የህይወት ፍልስፍና ነው!

ቦኒ ኬምስኬ “ዘ ፖይቲክ ሜንድ” በሚለው መጽሐፉ  እንዳሰፈረው የኪንትሱጊ ታሪክ የሚጀምረው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በጃፓን ነው። አሺካጋ ዮሺማሳ የተባለው የጃፓን ንጉሥ በጣም የሚወደው የሻይ መጠጫ የሸክላ እቃ ይሰበርበታል። ንጉሡ በጣም ስለተቆጨ እቃው ተጠግኖ እንዲመጣለት ወደ ቻይና ይልከዋል።

ከቻይና ተጠግኖ ሲመለስ ግን የተሰበሩት ክፍሎች አስቀያሚ በሆኑ የብረት ስቴፕለሮች  ተያይዘው ነበር። ንጉሡ በስራው ባለመደሰቱ የጃፓን ባለሙያዎችን ጠርቶ “ከዚህ የተሻለ፣ ውበት ያለው የመጠገኛ መንገድ ፈልጉ” ሲል አዘዛቸው።

የጃፓን የእጅ ባለሙያዎች ማሰብ ጀመሩ። “ስብራትን መሸሸግ አይቻልም፤ ታዲያ ለምን ስብራቱን ወደ ውበት አንቀይረውም?” የሚል ሃሳብ መጣላቸው። ከዚያም ስብርባሪዎችን በዛፍ ሙጫ እና በጥሩ የወርቅ ዱቄት አዋህደው ሰፉ። ንጉሡ እቃውን ሲያየው ከመሰበሩ በፊት ከነበረው ይበልጥ አምሮና በወርቅ ደምቆ አገኘው።

በጃፓንኛ ኪን ማለት ወርቅ ማለት ሲሆን ትሱጊ ማለት ደግሞ ማያያዝ/መቀጠል ማለት ነው። ኪንትሱጊ “በወርቅ ማያያዝ” የሚል ትርጉም ይይዛል።

ሊዮናርዶ ኮረን “ዋቢ ሳቢ ፎር አርቲስትስ፣ ዲዛይነርስ፣ ፖየትስ፣ ኤንድ ፊሎሶፈርስ” በሚለው መጽሀፉ እንዳለው ኪንትሱጊ የመነጨው “ዋቢ-ሳቢ” ከሚባለው የጃፓናውያን ጥንታዊ ፍልስፍና ነው። ዋቢ-ሳቢ ማለት በጎደለው፣ በተሰበረውና ፍጹም ባልሆነው ነገር ውስጥ ውበትን የማየት ጥበብ ማለት ነው።

በእኛ ዓለም አብዛኛው ሰው ፍጹምነትን ይፈልጋል። እቃዎቻችን፣ ህይወታችን፣ ትዳራችንና ማንነታችን ፍጹም እንከን የሌለውና ያልተሰበረ እንዲሆን እንመኛለን። ነገር ግን በተፈጥሮ ህግ ውስጥ ፍጹም የሆነ ነገር የለም።

የኪንትሱጊ ፍልስፍና የሚያስተምረን ነግሮች አሉ። ስብራት፣ ውደቀት እና ጠባሳ የታሪካችንና የማነታችን አካል ናቸው እንጂ የመጨረሻችን አይደሉም።

አንቺ ቁስልሽን፣ ስህተትሽንና ውድቀትሽን መሸሸግ ወይም ማፈር የለብሽም። ለአንተም ህይወትህ የተሰበረበት ቦታ ላይ ነው ትልቁ የወርቅ ብርሃን የሚበራው!

ይህንን የጃፓኖች ጥበብ ወደ ሰው ልጅ ህይወትና ስነ-ልቦና ስናመጣው አስደናቂ እውነታዎችን እናገኛለን። እያንዳንዳችን በህይወታችን መንገድ ላይ እንሰበራለን።

በምትወደው ሰው ክህደት አእምሮህ ይሰበር ይሆናል፤ በንግድህ ወይም በስራህ ከስረህ ህልምህ ይበተን ይሆናል፤ በህመም፣ በኀዘን ወይም በስጋት የውስጥ ማነትሽ ይደማ ይሆናል።

በእነዚህ ጊዜያት የሰው ልጅ አእምሮ ሁለት አይነት መንገድ ይከተላል። የመጀመሪያው መንገድ “ስብራቱን መሸሸግ” ነው። እንደተጎዳን ላለማሳየት የውሸት ሳቅ እንስቃለን፣ ቁስላችንን በሴት፣ በአልኮል ወይም በስራ ብዛት እንሸፍናለን።

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ “የተሰበረውን ህይወት መጣል” ነው። ተስፋ መቁረጥ፣ እኔ አልረባም ብሎ ራስን መጥላት እና ህይወትን ማቆም ነው። የኪንትሱጊ ፍልስፍና ግን ሶስተኛ የመውጫ መንገድ ይሰጠናል። እሱም “ስብራትህን በወርቅ ቀባው!” ይለናል።

አንደኛ ስብራትህን በወርቅ መገንባት ማለት ታሪክህን ተቀበል፣ ያጋጠመህን ውድቀት፣ ሀዘንና ስህተት አትካድ፣ እሱ ያንተ የታሪክ አካል ነው ማለት  ነው።

ሁለተኛ ከቁስልህ እውቀት ቅሰም። ወርቁ የሚያመለክተው በውድቀትህ ያገኘኸውን እውቀት፣ ጥንካሬ እና ጥበብ ነው።

ሦስተኛ በጠባሳህ ኩራበት። በደረትህ ወይም በአእምሮህ ላይ ያለው ጠባሳ ማለፍህንና መትረፍህን የሚያሳይ የድል ምልክት እንጂ  የእፍረት ምልክት አይደለም።

በእኛ ባህል ውስጥም የኪንትሱጊ መንፈስ ያላቸው ጥበቦችና አባባሎች አሉ። አባቶቻችን  “ያልተፈተነ ህይወት ዋጋ የለውም” ይላሉ።

አንድ ሰው ሲሳካለት “እገሌ እኮ ተፈትኖ የወጣ፣ የጠነከረ ሰው ነው” እንላለን። ቀደምት አባቶቻችን በረጅም የታሪክ ጉዟቸው ውስጥ በጦርነት፣ በድርቅ እና በፖለቲካ ማዕበል ብዙ ጊዜ ተሰብረዋል። ነገር ግን ሁልጊዜም ያንን ስብራት በመንፈሳዊነት፣ በጽናትና በይቅርታ በወርቅ እያጣበቁ እዚህ ደርሰዋል።

ሆኖም ግን በግለሰብ ደረጃ  የተሰበሩ ወይም በህይወት የወደቁ ሰዎችን የመውቀስና የማግለል አዝማሚያ የምናሳይ አለን። ኪንትሱጊ ግን ይነግረናል። የተሰበረን ሰው አትጣለው፤ በእውቀትና በፍቅር አጣብቀው፤ ከመሰበሩ በፊት ከነበረው ይበልጥ ድቅ ድንቅ ሰው ሆኖ ይወጣል ይላል።

በብሬኔ ብራውን የተጻፈው ዘ ጊፍትስ ኦፍ ኢምፐርፌክሽን መጽሀፍ ዛሬ ህይወታችሁ ተሰብሮ፣ አእምራችሁ ተጨንቆ ወይም ህልማችሁ ተበታትኖ ከሆነ እነዚህን 3 የኪንትሱጊ መመሪያዎች በመከተል ማሸነፍ ትችላላችሁ ይለናል።

  1. ስባሪዎቻችሁን ሰብስቡ፦

በመጀመሪያ ደረጃ የተሰበረውን መቀበል አለባችሁ። «አልተጎዳሁም» እያላችሁ አትዋሹ። ተጎድታችኋል፣ ተሰብራችኋል፣ ተሸንፋችኋል። ስባሪዎቻችሁን በሙሉ በሰከነ አእምሮ ሰብስባችሁ ተመልከቷቸው። ህመማችሁን ማወቅ ለመፈወስ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

  1. የወርቅ ሙጫችሁን አዘጋጁ፦

በጃፓናውያን ጥበብ ስብራቱ የሚያያዘው በወርቅ ነው። የእናንተ ወርቅ ደግሞ ከውድቀታችሁ ያገኛችሁት ትምህርት፣ ይቅርታ፣ ፀሎት እና አዎንታዊ አስተሳሰብ ነው። “ይህ አጋጣሚ ምን አስተማረኝ?” ብላችሁ ጠይቁ። ህመማችሁን ወደ እውቀት ቀይሩት።

  1. ጠባሳችሁን በክብር አሳዩ፦

የተጠገነውን እቃ ጃፓናውያን በክብር ያስቀምጡታል። እናንተም ቢሆን ከውድቀታችሁ በኋላ ስትነሱ ያለፈውን ታሪካችሁን አትደብቁ። “እኔ እኮ እንደዚህ አይነት ከባድ ጊዜ አሳልፌ የተነሳሁ ሰው ነኝ” ብላችሁ በክብር ተናገሩ። ጠባሳችሁ የጥንካሬያችሁ ማረጋገጫ ነው።

አንድ ድንቅ የኪንትሱጊ ባለሙያ እንዲህ ብሎ ነበር “እቃው ሳይሰበር በፊት ተራ የሸክላ እቃ ነበር፤ ከተሰበረና በወርቅ ከተጠገነ በኋላ ግን በዓለም ላይ ወደር የሌለው ብቸኛ የጥበብ ስራ ሆነ።”

እኛም እንደዚያ ነን! በህይወት ያጋጠመን ውድቀት፣ ክህደት፣ ወይም ኀዘን አላጠፋንም። ይልቁንም ተራ የነበረውን ህይወታችንን በወርቅ አጣብቆ፣ በዓለም  ላይ ድንቅና ጥንካሬ ያለው ባለ ታሪክ ያደርገናል።

ስለዚህም በተሰበሩት የህይወታችን ክፍሎች ላይ አናልቅስ፤ በወርቅ አጣብቀን በክብር እንነሳ! በህይወታችን ላይ ያሉት ወርቃማ ስንጥቆች የእኛ ውበቶች ናቸው።

 

 

ማረፊያ

“ውበት የሚጀምረው ራስህን ለመሆን በምትወስንበት ቅጽበት ነው” ኮኮ ቻኔል_የፋሽን ዲዛይነር፡፡

“የአንዲት ሴት ውበት በፊቷ ገጽታ ላይ አይደለም፤ እውነተኛው የሴት ውበት የሚንጸባረቀው በነፍሷ ውስጥ ነው” ኦድሪ ሄፕበርን-ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናይትና የፋሽን ተምሳሌት፡፡

“ሁሉም ነገር ውበት አለው፤ ነገር ግን ሁሉም ሰው አያየውም” ኮንፊሺየስ_ጥንታዊ የቻይና ፈላስፋ፡፡

“ፍጹም አለመሆን ራሱ ውበት ነው” ሜሪሊን ሞንሮ-ታዋቂ አሜሪካዊት ተዋናይት እና ሞዴል ፡፡

“ውበት በገጽታ (በፊት) ላይ አይደለም፤ ውበት በልብ ውስጥ ያለ ብርሃን ነው” ካህሊል ጂብራን_ታዋቂ ሊባኖሳዊ-አሜሪካዊ ገጣሚ፣ ጸሐፊ እና ሰዓሊ፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here