በእግርዎ ወይም በታኪሲ ሲሄዱ አልያም በሰፈርዎ አንድን ታዳጊ እናቱ ወይም አባቱ ስድብ እና የእርግማን ሲያወርዱበት መስማት በሀገራችን የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደ ችግር የማናየው እና የተለመደው ችግር ስደብ በልጆች ዕድገት ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እና በወደፊት ማንነታቸው ላይ ትልቅ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ነው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ክፍል ሀኪም እና መምህር ዶ/ር ታምራት ተፈራ የተናገሩት፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ አሁን ባለንበት ደረጃ ወጥ የሆነ ስምምነት ላይ ባይደረስም የሰው ልጅ ስብዕና ይገነባል ተብሎ የሚታሰበው የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዓመታት በተለይ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ወሳኝ የሰው ልጅ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ እና ባህሪያዊ መሰረቶች የሚወሰኑበት ፣ የአንጎል እድገት በማይታመን ሁኔታ የሚፈጥንበት፣ የስሜት ሕዋሳት እና መሰረታዊ የሞተር ክህሎቶች እድገት የሚታይበት እና በተለይ ደግሞ በነዚህ የመጀመሪያዎቹ እድሜ ልጆች ከወላጆች ጋር ያላቸው ትስስር እና ቅርርብ ለወደፊት ግንኙነቶች ትልቅ መሰረት የሚጣልበት ጉልህ የእድገት ደረጃ መሆኑን ነው።
የአንድ ሰው የወደፊት ስነ ልቦናዊ ማንነት፣ ስሜታዊ ቁጥጥር፣ በራስ መተማመን እና ሌሎች በጣም ጉልህ ማንነታዊ መገለጫዎች በነዚህ የመጀመሪዎቹ ዓመታት የሕጻናት እድገት እና የወላጆች አያያዝ ይወሰናል። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው ከተወለዱ ጀምሮ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበትን መንገድ ከለቅሶ ጀምሮ መረዳት እንደሚገባቸው ነው። በልጅነት ወቅት በአብዛኛው ከጎናቸው ያለው ወላጅ ብቻ ስለሆነም ዓለምን የሚመለከቱበት “ዓለም ጥሩ ናትም፤ መጥፎ ናት” ብለው ለመወሰን የሚችሉበት ትንሽዬ መስታዎቶች ናቸው፡፡ ወላጅ መልካም አሳዳጊ ከሆነ፤ “ዓለም ጥሩ ናት” ብለው ሲረዱ ወላጅ መጥፎ ከሆነ ደግሞ ዓለምም እንደዛ ናት ብለው ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ በለቅሶ ወቅትም ሆነ ዕገዛ ፍለጋ ሲጠይቁ ወላጆች ከጎናቸው ካልሆኑ ዓለም በሙሉ እንደዛ ነው ብለው ይረዳሉ፡፡
በሕጻናንነታቸው ወይም በልጅነታቸው ወቅት የወላጆች በቂ ትኩረት ያላገኙ እና ቸልተኝነት ያጋጠማቸው ወይም በቂ የወላጆች ቅርርብ እና ትኩረት የተነፈጋቸው ልጆች ለምሳሌ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው ጋር ብዙ ሰዓት የማያሳልፉ ሕጻናት ወይም በተቋማት ውስጥ ያደጉ ከፍርሃት እና ጭንቀት ጋር የተቆራኘ ስነ ልቦናዊ እና አካላዊ ለውጦችን ያሳያሉ። በጊዜ ሂደት ይህ ራስን የመግዛት፣ ትኩረት የማጣት ፣ ያለመፈለግ ስሜት ፣ በራስ አለመተማመን እና የመማር ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።
ዶ/ር ታምራት እንደሚገልፁት በተለይ ደግሞ በታዳጊነት ዕድሜ ክልል (1 እስከ 7) የሚበረታቱበት ፣ጎበዝ ፣ የሚባሉበት… ዕድሜ ክልል ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ መስደብ እና ማንቋሸሽ ካለ ግን ልጆች ቤተሰብ ዓለማቸው እና ዓለምን ማሳያቸው ስለሆነ ዓለም ክፉ ናት ብለው በተቃራኒ ሁሉንም ነገር መጥፎ አድርጎ መገንዘብ ይኖራል፡፡
በሀገራችን በልጆች አስተዳደግ ብዙ ጠንካራ የሚባሉ ሁኔታዎች አሉ የሚሉት የስነ ልቦና ሃኪሙ ለምሳሌ ከጎረቤት ጋር መጫወት፣ ከተፈጥሮ ጋር እንደልብ ተግባብተው አፈር አቡክተው ማደጋቸው… እኛ ባንረዳም ለልጆቹ ትልቅ ስብዕና ግንባታ ያለው ነገር ነው፡፡ ወላጆች በተቃራኒው ክፋትን አስበው ባይሆንም እንኳን ልጆቻቸውን የማትረባ፣ አትጠቅምም፣ ከንቱ….. እያሉ በሰደቡ ቁጥር ግን ልጁ የስድቡ ትርጉም በጊዜው በደንብ ባይረዱትም ቃላቱን እንዳለ ወደ አዕምሮ በመውሰድ “እኔ ጥቅም የለኝም አልረባም፤” የሚል ግንዛቤ እየያዘ ያድጋል፡፡ ልጆች የምንናገራቸውን ነገር አዕምሮ መዝግቦ ለተነገረው ነገር ትርጉም ይሠጠዋል የሚሉት ዶ/ር ታምራት ልጅዎች ነገሩን ከዕውነታው ዓለም ጋር ስሜት ሰጥቶ የማመዛን ደረጃ ላይ ስላልደረሰ እንዳለ አዕምሮ ላይ ይቀመጣል፡፡
ስድብ ብቻ ሳይሆን “አንተን ብዬ ነው እንደዚህ የሆንኩት” የሚል የወላጅ ወቀሳ ለወላጆቻቸው መሰቃየት የሱ ችግር እንደሆነ አስበው እንዲሸማቀቁ ፣ ራሳቸውን እንዲወቅሱ፣ሸክም እንደሆኑ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ይህ ደግሞ የልጁ ስብዕና ሠዎች አይወዱኝም ብሎ ስለሚያስብ ሰዎች እንዲወወዱት ብቻ ጥረት የሚያደርግ፣ ለተበደለውም ነገር እኔ ነኝ ጥፋተኛ ብሎ ራሱን እንዲኮንንን የሚደርግ ስብዕናን ይላበሳል፡፡
ልጆች ጥፋት ካጠፉ መቅጣት ትክክለኛ ነገር ነው የሚሉት ነገር ማስተማር ትክክል ነው የሚሉት ባለሙያው የቅጣቱ ዓይነት ግን ስድብ እና ድብደባ መሆን አይገባውም፡፡
ከቤት አትውጣ ተብሎ ሲነገረው ከቤት ከወጣ ሊመጣበት የሚችለውን ችግር በዝርዝር በምክንያት ማስረዳት ከተቻለ የሚደረገው ነገር ከቤት ትዕዛዙን ጥሶ ከወጣ የሚደርስበት ቅጣት ለሱ ተብሎ የተደረገ መሆኑን ይገነዛባል፡፡ ትላንት ላጠፋው ጥፋት ዛሬ መደብደብም በራሱ ተገቢ ቅጣት አይደለም ይላሉ፡፡ ልጆችን መደብደብ ብቻውን ወደ ፊት ሰው ሁሉ የሚደበድባቸው፣ ያለ ምክንያት የሚቆጣቸው ፣ቁጣ በሙሉ እነሱን ጥፋተኛ የሚያደርግ እንደማጥቃት እየቆጠሩት በጣም ቶሎ የሚናደድ ስብዕናን እንዲገነቡ ያደርጋል፡፡
ወላጆች ልጆችን በስድብ ከማጥቃት ውጭ እናት እና አባት ርስ በርሱ የሚያወሩበት መንገድ፣ እናት ከጎረቤት ጋር ፣ እናት ከትልቅ ልጆች ጋር የሚያደርጉት ንግግር ትክክል ካልሆነ ለሚመለከቱት ትንንሽ ልጆች የወደፊት ህይወት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡
ገና በ5 እና 6 ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች መስማት እና ማየት የሌለባቸውን ነገር ከፊትለፊታቸው ማድረግ ልጆቹ አዕምሮ ላይ የሚያሳድረው ጠበሳ እና ወደፊት በሚኖራቸው ሕይወት ያለው ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡ በብዛት በህክምና የምናገኛቸው የድባቴ መኖር፣ትዳር መፍታት እና ትዳር ውስጥ አለመቆየት፣ ሱስ ውስጥ መግባት እንዲሁም የአዕምሮ ህመም አስተዳደጋቸው ላይ የተከሰተ ከላይ ያየነው ችግር ውጤት ነው፡፡
በልጅነታቸው ሰድበን ያሳደግናቸው ልጆች በጣም ብዙ ዓይነት ስብዕና ይኖራቸዋል፡፡ልጆች አድገው ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትም የዚሁ አስተዳደግ ውጤት ነው፡፡
በልጅነታቸው ስድብ እና አላስፈላጊ ድበደባ ካለ ለአዕምሮ ህመም በከባድ ሁኔታ ይጋለጣሉ፤በራስ መተማመናቸው ዝቅ ይላል፣እኔ በቂ አይደለሁም ብሎ ማሰብ በልጅነታቸው ይታተምባቸዋል፣ ምንም ነገር ሲያደርጉ በቂ አለመሆናቸውን እና ስኬታማ እንደማይሆኑ ለራሳቸው ይነግራሉ፣ ውስጣቸው ሁልጊዜ ራሱን የሚተች፣ ዝቅ የሚያደርግ ድምፅ ይሠማቸዋል፣ ምንም ነገር ሳይጀምሩ አይሳካም የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፤ ያደረጉት ሲሳካ ደግሞ እነሱ ያደረጉት አይመስላቸውም፣ ራሳቸውን አያደንቁም፣የደስታ ስሜት የላቸውም፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ይሄ ደግሞ በሰዎች ዘንድ ለመወደድ እና ለመደነቀቅ ሲሉ ምንም ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ያደርጋቸዋል፡፡ ብዙ ሴቶች ብዙ ድብደባ እና ጭቆና ያለበት ትዳር ውስጥ የሚኖሩትም ምንም ባያጠፉ እንኳን “ጥፋቱ የኔ ነው ፡፡” ብለው የሚያስቡ እና ሌላ ሰው አይፈልገኝም ብለው የሚያስቡ በዚህ መንገድ አስተዳደጋቸው ችግር ያለበት በመሆኑ ነው፡፡
ዶ/ር ታምራት እንደሚሉት የስድብ እና መጥፎ ቃላት ችግርን በዝርዝር ስንመለከት በሰብዓዊ ማንነት ላይ ቃላት የልጆችን መሠረት የመገንባትም ሆነ የማፍረስ ትልቅ አቅም ያላቸው ነገሮች እንደሆኑ ስለሚያስገነዝብ በተቻለ መጠን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በታዳጊነት /በልጅነት ዕድሜ ልጆቻችን ሲፈልጉን መገኘት እና ዓለማቸው እኛ እንደሆንን ካወቅን እኛ ባሳየናቸው መንገድ እንደሚሄዱ አውቆ በመገንባት በኩል መጠንቀቅ ይገባል፡፡
ተወደደም ተጠላም ቃላት የሰውን ልጅ ደካማም ጠንካራም ያደርጋል፡፡ ከአፍ የወጣ ቃል እንደተሰነዘረ ሰይፍ ከማቁሰል መመለሻ ብልሐት የለውም፤ የሰይፍ ቁስል ሲውል ሲያድር ሲሽር በክፉ ቃል የሚፈጠር ቁስል ግን ጠባሳውን ከአይምሮ ለመፋቅ በእጅጉ ይፈትናል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


