ከጓሮ -ዓለም አቀፍ ገበያ

0
264

በዓለም አቀፍ ገበያ አረንጓዴው ወርቅ የሚል ተቀፅላ ስም ተሰጥቶታል – አቮካዶ፡፡ ከቡና እና ከቅባት እህሎች ንግድ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ መንግሥት እና አርሶ አደሮች ፊታቸውን ወደ አቮካዶ ልማት እያዞሩ ይገኛሉ።

የግብርና ሚኒሥቴር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ  የአቮካዶ ምርቷን ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ ገበያዎች መላክ መጀመሯ ደግሞ የዘርፉን ተስፋ ሰጪነት ያሳያል። በተለይም በአማራ ክልል እየተተገበረ ያለው የአቮካዶ ክላስተር ልማት የበርካታ አርሶ አደሮችን ሕይወት ከመቀየሩም ባሻገር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።

በክልሉ ልማቱ ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች አንዱ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጓንጓ ወረዳ ነው፡፡ የወረዳው  አርሶ አደሮች ባሕላዊውን የእርሻ ሥራ ወደ ዘመናዊና ገበያ ተኮር የፍራፍሬ ልማት እየቀየሩት ይገኛሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት ደግሞ በወረዳው የሚኖሩት አርሶ አደር ፈንታሁን ካሳሁን ናቸው። በአካባቢው አዲስ የተሻሻለ የአቮካዶ ልማትን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም አርሶ አደር ናቸው።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም የፍራፍሬ ልማት ብዙም የተለመደ አልነበረም። ሆኖም አርሶ አደር ፈንታሁን የግብርና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ምክር በመቀበል ከሦስት ዓመታት በፊት የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን ማልማት ጀመሩ። በተለይም በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ሀስ እና ኢቲንገር የተባሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በመምረጥ ማሳቸውን አረንጓዴ አልብሰዋል።

“ከዚህ በፊት በአካባቢያችን አትክልትና ፍራፍሬ የመትከል ልምድ አልነበረንም። የግብርና ባለሙያዎች ችግኞቹን ካመጡልን በኋላ አሠራሩን አሳዩን፤ እኛም ሞከርነው። አሁን ውጤቱ እጅግ አስደሳች ነው” ይላሉ አርሶ አደር ፈንታሁን የጀመሩበትን ጊዜ ሲያስታውሱ።

የአርሶ አደር ፈንታሁን ትልቁ ስኬት የራሳቸውን ኑሮ  ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን አርሶ አደሮች አስተሳሰብ መቀየር መቻላቸው ነው። የእሳቸውን የፍራፍሬ ልማት እና ያገኙትን የገቢ ለውጥ የተመለከቱ  አርሶ አደሮች አሁን ላይ በሰፊው ወደ አቮካዶ ልማት እየገቡ ነው። በርካታ አርሶ አደሮች የአቶ ፈንታሁንን ፈለግ በመከተል የአቮካዶ ችግኞችን ተክለው እንክብካቤ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የግብርናው ዘርፍ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ አዳዲስ የልማት አቅጣጫዎችን እየተከተለ ይገኛል። በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ሲሆን ከባሕላዊ የአመራረት ዘይቤ ወጥቶ በኩታገጠም ወደ ማምረት ሽግግር እየተደረገ ነው።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ (የሆልቲካልቸር) ቡድን መሪ  አቶ አዲሱ ዓለሙ ለበኵር እንደገለጹት በዚህ ዓመት በተሻለ እና በተጠናከረ መልኩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በተለይም ስነ ምህዳራቸው ለልማቱ  ተስማሚ የሆኑ እና ከፍተኛ እምቅ አቅም ያላቸው ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተለይም አቮካዶን በስፋት ለማምረት ጓንጓ፣ ዳንግላ፣ አየሁ ጓጉሳ እና ዚገም ወረዳዎች በዋናነት ተለይተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በዘንድሮው ዓመት ትልቁ ትኩረት የተሰጠው የአቮካዶ ክላስተር አሠራርም በመተግበር ላይ ነው። ለአብነትም በጓንጓ ወረዳ ጥሩ ብርሐን በተባለ ቀበሌ 100 ሄክታር መሬት በአቮካዶ ክላስተር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

አቶ አዲሱ በስልክ እንዳብራሩት “ከዚህ ቀደም  በተበታተነ መልኩ የነበረውን ችግኝ የመትከል ልምድ በመቀየር በተመረጠ አንድ ቀበሌ ላይ አተኩረን ሠርተናል” ብለዋል። ምንም እንኳን በጉድጓድ ዝግጅት እና ተያያዥ ችግሮች የታቀደውን 100 ሄክታር ሙሉ በሙሉ መሸፈን ባይቻልም በ54 ሄክታር መሬት ላይ ከ15 ሺህ በላይ የአቮካዶ ችግኞችን መትከል ተችሏል። ይህ እንቅስቃሴ በአንድ ቀበሌ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተደረገው ርብርብ ከ75 ሺህ 500 በላይ የአቮካዶ ችግኞች በተለያዩ አካባቢዎች ተተክለዋል። አሁን ላይ ከመትከልም ባለፈ የኩትኳቶ፣ የአረም  እና ማዳበሪያ (ኮምፖስት) የመጨመር ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ ይገኛሉ።

አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት የፍራፍሬ ልማትን የገቢ ምንጭ አድርጎ በስፋት እየተቀበለው ነው። በተለይም  ሀስ እና ኢቲንገር የተባሉት የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። እነዚህ ዝርያዎች ለውጭ ገበያ ተመራጭ ከመሆናቸውም በላይ ሳይበላሹ ረዘም ላለ ጊዜ የመቆየት አቅም አላቸው። በተጨማሪም ቁመታቸው መጠነኛ በመሆኑ ለመንከባከብ እና ፍሬያቸውን ለመልቀም ምቹ ናቸው። የዞኑ ግብርና መምሪያም እነዚህን የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

በሌላ በኩል ፖፓያ፣ ማንጎ፣ ሙዝ እንዲሁም እንደ አፕል እና ብርቱካን የመሳሰሉ የደጋ እና የቆላ ፍራፍሬዎችም እየለሙ ይገኛሉ። በዞኑ በዘንድሮው ዓመት  700 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ስኬታማ ሆኗል።

የፍራፍሬ ልማቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ነው። አቶ አዲሱ አቮካዶን “የደሃ ቅቤ” በማለት ይገልጹታል። ከገበያ ምንጭነቱ ባሻገር በገጠርም ሆነ በከተማ የህብረተሰቡን የስነ-ምግብ (Nutrition) ፍላጎት በማሟላት በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል እየፈጠረ ይገኛል። ወጣቶች ተደራጅተው ችግኝ በማፍላት፣ በመንከባከብ እና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በተጓዳኝም የፍራፍሬ ዛፎቹ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራን በማገዝ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

በአማራ ክልል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት እያደገ የመጣው የአቮካዶ ልማት የክልሉ አርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ አቅም ከማሳደግ አልፎ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ክልሉ የአቮካዶ ምርትን በስፋት በማምረት ዘርፉ ትልቅ አቅም እንዳለው በተግባር እያሳየ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሆልቲካልቸር ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ አበበ መኮንን ለበኵር ጋዜጣ አስታውቀዋል። በስፋት አቮካዶ ከሚለማባቸው አካባቢዎች መካከል በምዕራብ አማራ ዞኖች የሚገኙት ሰሜን ሜጫ፣ ባሕር ዳር ዙሪያ እና ከተማዋ፣ ደቡብ አቸፈር፣ ሰሜን አቸፈር፣ ዳንግላ፣ ጓንጓ፣ ቡሬ ዙሪያ፣ ጃቢ ጠህናን፣ ደምበጫ፣ ማቻከል፣ ደብረ ኤልያስ፣ ጎንደር ዙሪያ እና ደራ ወረዳ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በክልሉ በልማቱ የተሸፈነው የመሬት ስፋትም 14 ሺህ 69 ሄክታር የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 309 ሄክታሩ በዘመናዊ የክላስተር የአስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግርዋል፡፡ ከዚህ ሰፊ መሬትም አንድ ሚሊዮን 71 ሺህ 560 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡

በክልሉ ለታየው የአቮካዶ ልማት እድገት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተለይም በምዕራብ አማራ እና ከፊል ጎንደር ቀጠና ያለው የስነ-ምህዳር ምቹነት እና ለአቮካዶ ልማት ተስማሚ የሆነ አፈር መኖሩ ዋነኛው ነው፡፡ በተጨማሪም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውኃ ሃብት መኖሩ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት (የሙቀት እና የዝናብ መጠን) እንዲሁም ተስማሚ ከፍታ ልማቱን አሳልጠውታል፡፡

በመንግሥት በኩል ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ከክልል እስከ ወረዳ ያለው አመራር በጀት መድቦ ለመሥራት ያለው ፍላጎት እንዲሁም የሰፋፊ ክላስተር ልማት እያሳየ ያለው አበረታች ለውጥ ሌላው የስኬቱ ሚስጥር ነው፡፡ ታታሪ እና የማምረት ልምድ ያላቸው አርሶ አደሮች መኖር፣ የሰው ኃይል እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጨመሩ እንዲሁም ምርትን ለውጭ ገበያ የመላክና የድህረ-ምርት ዝግጅት ጅምር ልምዶች መኖራቸው ዘርፉን ይበልጥ አጠናክረውታል ነው ያሉት፡፡

ምንም እንኳ ዘርፉ ተስፋ ሰጪ እድገት እያሳየ ቢሆንም ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም የሚያደርጉ ማነቆዎች አልጠፉም፡፡ ከእነዚህም መካከል ልምድ ያላቸው ከፍተኛ ተመራማሪዎች በብዛት አለመኖር፣ በክልሉ በቂ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ ለመደረጋቸው እና የተሻሻሉ ዝርያዎችን አባዝቶ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ውስንነት ይገኙበታል፡፡

ልማቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፍ፣ ለአቮካዶ ምርምር  የሚሆን በቂ የመሬት አቅርቦት አለመኖር፣ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት ተገቢውን የእንክብካቤ አሰራር አለመተግበር እና ዘላቂነት ያለው የገበያ ትስስር አለመኖር በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ አዳዲስ የተዳቀሉ ዝርያዎችን በማፍለቅ በኩል ያለው ክፍተት፣ በተቋማት (ምርምር፣ ግብርና እና ሌሎችም) መካከል ያለው የቅንጅት ጉድለት ሌሎች የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡

እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ክልላዊ ስትራቴጂክ እና ማሰልጠኛ ሰነዶች መዘጋጀታቸዉን ነዉ ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። በተጨማሪም በቀጣይ ዓመት ልማቱን በሰባት ወረዳዎች በክላስተር በስፋት ለማከናወን እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ክልሉ ከሚመረተው ምርት ውስጥ 70 በመቶውን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት፣ በሀገር ውስጥ ላሉ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች በቂ ጥሬ እቃ ለማቅረብ እንዲሁም በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

መረጃ

የአቮካዶ ምርት የሚሰጣቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች

 

  • የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ፦ ደረጃውን የጠበቀ የአቮካዶ ምርት (በተለይም ሀስ አቮካዶ) ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይቻላል።
  • ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት፦ ከአቮካዶ የሚወጣው ዘይት ለምግብነት ብቻ ሳይሆን ለመዋቢያ ምርቶች (Cosmetics)፣ ለሳሙና እና ለተለያዩ የቆዳ እና የፀጉር መንከባከቢያ ቅባቶች ማምረቻነት በስፋት ያገለግላል።
  • የሥራ ዕድል ፈጠራ፦ ምርቱን በማምረት፣ በመሰብሰብ፣ በማጓጓዝ እና በማቀነባበር ሂደት ውስጥ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

በአጠቃላይ አቮካዶን በምግባችን ውስጥ ማካተት ለጤናችን እጅግ ጠቃሚ እና ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

 

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የነሐሴ 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here