በዐውሎ ነፋሱ መሀል

0
192

ዛሬ ዓለማችን በሁከት ማዕበል ዜናዎች እና ድርጊቶች የተሞላች ትመስላለች። የኢኮኖሚ ውጥረት፣ የጂኦፖለቲካ ግጭቶች፣ የመረጃ ጎርፍ እና የዕለት ተዕለት የሕይወት ሩጫ አእምሯችንን እያናወጡት ይገኛሉ። ጥያቄው “ዓለም በግርግር ውስጥ ሆና፣ ጊዜ እየሮጠብን፣ ውስጣዊ ሰላማችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?” የሚለው ነው።

ይህ ጽሁፍ የጥንታውያን ጠቢባንን ሚስጥር፣ የጦር መሪዎችን የጽናት መርሕ እና የዘመናዊ የነርቭ ሳይንስ ግኝቶችን በማቀናጀት ለዚህ ጥያቄ ጥልቅና ተግባራዊ ምላሽ ይሰጣል።

በቪየትናም ጦርነት ወቅት አድሚራል ጄምስ ስቶክዴል የተባሉ አሜሪካዊ የጦር አዛዥ በጠላት እጅ ተማርከው ለሰባት ዓመታት ያህል በከባድ እንግልት እና ማሰቃየት ውስጥ አልፈዋል። በዚያ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ አብረዋቸው ከታሰሩት ወታደሮች መካከል አብዛኞቹ ተስፋ በመቁረጥና በአእምሮ ስብራት ሲሞቱ ስቶክዴል ግን በአካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ተርፈዋል።

በኋላ ላይ “ስቶክዴል ፓራዶክስ” ተብሎ በተሰየመው መርሐቸው  ለውስጣዊ ሰላምና ጽናት መሠረቱ የሁለት ተቃራኒ እውነታዎች ስምምነት መሆኑን ገለጹ። “በመጨረሻ እንደምታሸንፍ እና እንደምትወጣ ያለህን ጽኑ እምነት በፍጹም አትጣ፤ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ አሁን ያለህበትን ጨካኝ እና አስቸጋሪ እውነታ ያለ ምንም ማወላወል ፊት ለፊት ተጋፈጠው” አሉ።

አብዛኞቹ እስረኞች የሞቱት “በገና እንፈታለን”፣ “በፋሲካ እንወጣለን’ እያሉ በሐሰተኛ ተስፋ በመኖራቸው እና ያ ሳይሆን ሲቀር አእምሯቸው በመሰበሩ ነበር።  የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር ነበር የሞቱት። ውስጣዊ ሰላም ማለት እውነታን መሸሽ ወይም “ሁሉም ነገር ጥሩ ነው” ብሎ በሐሰት መደለል አይደለም። ይልቁንም የችግሩን ግዝፈት በግልጽ መቀበል እና  ነገር ግን አእምሯችን በችግሩ እንዳይሸነፍ ማድረግ ነው።

በ6ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ሮማዊው ፈላስፋ እና የመንግሥት ባለሥልጣን ቦኢቲየስ በሐሰት ተወንጅሎ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በጨለማ ቤት ውስጥ ተጥሎ ነበር። በዚያ የመጨረሻ የሕይወት ዘመኑ “የፍልስፍና መጽናናት” የተሰኘውን ድንቅ መጽሐፉን ጻፈ።

ቦኢቲየስ “የዕድል መንኮራኩር” የሚል ጽንሰ-ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዝና እና ውጫዊ ሰላም ሁልጊዜ እንደሚሽከረከሩ ገልጿል። መንኮራኩሩ ወደ ላይ ሲወጣ ደስታ፣ ወደ ታች ሲወርድ ደግሞ መከራ ይመጣል።

የቦኢቲየስ ዋና ትምህርት ይህ ነው “ውጫዊ ነገሮች ያንተ አይደሉም፤ ስለዚህ ሊወሰዱብህ ይችላሉ። ያንተ የሆነውና ማንም ሊወስደው የማይችለው ብቸኛው ነገር የአእምሮህ ውስጣዊ ሁኔታ ብቻ ነው።”

ዓለም ስትታወክ ውስጣዊ ሰላማችን የሚጠፋው በራሳችን ቁጥጥር ስር የሌሉ ውጫዊ ነገሮችን (የዓለም ኢኮኖሚ፣ የሰዎች ጠባይ፣ የጊዜ መሮጥ) ለመቆጣጠር ስንሞክር ነው። በራሳችን ቁጥጥር ስር ባለው አእምሯችን ላይ ብቻ ስናተኩር ግን፣ ውጫዊው ማዕበል የውስጥ ደሴታችንን ማፍረስ አይችልም።

በዘመናችን በነርቭ ሳይንስ  እና ስነ-ልቦና ዘርፍ ትልቅ አብዮት የፈጠሩት ዶክተር ሊዛ ፌልድማን ባሬት “ሀው ኢሞሽን አር ሜድ” (ስሜቶች እንዴት ይፈጠራሉ?) በተሰኘው መጽሐፋቸው አእምሯችን ውጫዊውን ዓለም እንዴት እንደሚያስተናግድ በጥናት አስደግፈው አሳይተዋል። እንደ ጥናቱ ገለጻ አእምሯችን የውጭውን ዓለም ክስተቶች ቀጥታ አያስተናግድም። ይልቁንም ለክስተቶቹ «ትርጉም» ይሰጣቸዋል።

የአእምሮ ቅንብር (Cognitive Reframing)፦ ውጫዊው አካባቢ ውጥረት ሲፈጥር አእምሯችን አደጋ ላይ ነኝ የሚል ትርጉም ካስቀመጠ የአድሬናሊን እና ኮርቲሶል ሆርሞኖችን በመልቀቅ አካላችንን እና አእምሯችንን ያውከዋል።

– ስሜታዊ ጥራት (Emotional Granularity)፦ ዶክተር ባሬት እንደሚያስረዱት ውጥረትን በግልጽ የመለየት ብቃት ያላቸው ሰዎች (ለምሳሌ፦ ደስ አልተሰኘሁም ከማለት ይልቅ አሁን የተሰማኝ ስሜት የጊዜ እጥረት ስጋት ነው) አእምሯቸው በፍጥነት የማረጋጋት እርምጃ እንዲወስድ ያደርጋሉ።

በተጨማሪም ባዮሎጂስቱ ሮበርት ሳፖልስኪ “ዋይ ዜብራስ ዱ ኖት ጌት አልሰርስ”  በተሰኘው ጥናታዊ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፤ የሜዳ አህያዎች ከአንበሳ ሲያመልጡ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። ነገር ግን አደጋው ሲያልፍ ወዲያውኑ ወደ ሙሉ ሰላምና ረጋ ያለ ሁኔታ ይመለሳሉ። ሰዎች ግን አደጋው ካለፈ በኋላም ወይም ገና ያልመጣን ስጋት በማሰብ አእምሯቸውን በጭንቀት ያሰቃያሉ። ውስጣዊ ሰላም ማለት አእምሮን ከአላስፈላጊ የወደፊት ስጋት ውይይቶች የማላቀቅ ጥበብ ነው።

የጥንቱ ቻይናዊ ጠቢብ ላኦ ዙ  በጻፈው “ዳኦ ዴ ጂንግ” በተሰኘው መጽሐፉ የውኃን ተፈጥሮ ለውስጣዊ ሰላም እንደ ትልቅ ምሳሌ ያቀርባል። ውኃ ከድንጋይ ጋር ሲገናኝ አይጣላም፤ ይልቁንም ድንጋዩን ከብቦት ወይም አልፎት ይፈሳል።

ደቻይንኛ “ው ዌይ” ማለት ያለ ግብግብ መኖር ወይም ከተፈጥሮ ፍሰት ጋር መስማማት ማለት ነው። በዘመናችን ብዙ ጊዜ ኃይላችንን የምንጨርሰው መለወጥ የማንችላቸውን እውነታዎች በመታገልና በመቃወም ነው። ለማይለወጠው ነገር መገዛት፣ ሊለወጥ የሚችለውን ደግሞ በጥበብ መለወጥ የውስጣዊ ሰላም ትልቁ ምስጢር ነው።

እነዚህን ጥንታዊና ዘመናዊ እውቀቶች ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት እንቀይራቸው?

ሀ) የመረጃ ንጽሕናን መጠበቅ ፦

አእምሯችን በየቀኑ የሚያስተናግደው የመረጃ መጠን ከአቅሙ በላይ ሆኗል። በየደቂቃው የሚወጡ አስደናቂና አስፈሪ ዜናዎች አእምሮን በመግጠም ወይም መሸሽ (Fight or Flight) ሁኔታ ውስጥ ያቆዩታል። በቀን ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ከስልክና ከዜና መራቅ የአእምሮን የነርቭ ሥርዓት ለማረጋጋት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ለ) የትኩረት ድንበር ማበጀት ፦

በየቀኑ ጠዋት አእምሯችንን ይህንን ጥያቄ መጠየቅ አለብን “አሁን የሚያስጨንቀኝ ነገር በእኔ ቁጥጥር ስር ነው ወይስ አይደለም?” በቁጥጥር ስር ካልሆነ (ለምሳሌ፦ የዓለም ነዳጅ ዋጋ፣ የሌሎች ሰዎች አስተያየት)  በቃላትና በሐሳብ ከመታገል ይልቅ በግልጽ መቀበል ይገባል። በቁጥጥር ስር ከሆነ (ለምሳሌ፦ የእኔ ምላሽ፣ የእኔ የሥራ ጥረት፣ የእኔ የዕረፍት ጊዜ)  ሙሉ ትኩረቴን እዚያ ላይ  ማድረግ ያስፈልገኛል።

ሐ) «የስቶክዴል» እውነታን መቀበል

ችግሮችን ባለመካድ ፊት ለፊት መጋፈጥ ግዴታ ነው። “ኑሮው ተወዷል” የሚለውን እውነታ አምኖ በመቀበል፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ? ወደሚለው ተግባራዊ እርምጃ መሸጋገር ጥሩ ነው። ጭንቀት የሚፈጠረው በእውነታው እና እኛ እንዲሆን በምንመኘው ነገር መካከል ባለው ክፍተት ነው፤ ክፍተቱን በመቀበል ማጥበብ ይቻላል።

መ) የጸጥታ ጊዜ ማዘጋጀት ፦

በየቀኑ ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ሙሉ በሙሉ በጸጥታ መቀመጥ። ያለምንም ስልክ፣ ያለምንም ሙዚቃ ወይም ውይይት ለብቻ መሆን። ይህ አእምሮ በቀን ውስጥ ያከማቸውን ጥቃቅን ስሜቶች እንዲያብራራና እንዲያጸዳ ዕድል ይሰጠዋል።

ውስጣዊ ሰላም ማለት ችግርና ግርግር የሌለበት ሕይወት ማለት አይደለም። ውስጣዊ ሰላም ማለት በማዕበሉ መሀል ሆኖ የረጋ ልብ እና አእምሮ መገንባት ማለት ነው።

አድሚራል ስቶክዴል በእስር ቤት የጠነከረው፣ ቦኢቲየስ በጨለማ ቤት ውስጥ ሆኖ የፍልስፍና ጥጉ ላይ የደረሰው፣ የነርቭ ሳይንስ ጥናቶችም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው። የውጭው ዓለም ሊያናውጠን የሚችለው የውስጡን መቅደሳችንን በራሳችን ፈቃድ አሳልፈን ስንሰጠው ብቻ ነው።

ዓለም በራሷ ፍጥነት መሮጧን፣ ኢኮኖሚው መለወጡን፣ ግርግሩም መቀጠሉ አይቀርም። ነገር ግን በዚያ ሁሉ መሀል፣ አእምሯችንን የመቆጣጠር፣ ትርጉሙን የማስተካከል እና የማይናወጠውን ውስጣዊ ሰላማችንን የመጠበቅ ሙሉ ሥልጣንና ጥበብ በእጃችን ላይ ይገኛል።

እንጠቀምበት እንጂ!!።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የነሐሴ 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here