የሚሊዮኖች ስጋት

0
330

ምዕራብ አውሮፓ በያዝነው የፈረንጆች 2026 ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛውን የሙቀት መጠን አስተናግዷል፤ ስዊዘርላንድንና ፈረንሳይን ጨምሮ አንዳንድ ሀገሮች በበጋው ከፍተኛውን የሙቀት ማዕበል እያስተናገዱ ነው። በያዝነው ነሐሴ ወርም ከፍተኛ ሙቀቱ ቀጥሏል።

ይህ ወር በመላው አውሮፓ እና በሌሎችም የሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ አካባቢዎች የእረፍት ጊዜ ነው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐሳብ የሰጡት የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት (WMO) ቃል አቀባይ ክሌር ኑሊስ አንዳንድ ሠራተኞች ግን እረፍት እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል፤ ቃል አቀባይዋ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በርካታ የሚቲዎሮሎጂ እና የውኃ አገልግሎቶች፣ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር እና ምላሽ ሰጪ ቡድኖች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች እየታዘብናቸው ባሉት እጅግ ከባድ የአየር ሁኔታ ለውጥ ክስተቶች ምክንያት ያለ እረፍት እንዲሠሩ እየተደረጉ ይገኛሉ።

“ጉዳዩ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ብቻ አይደለም” ያለሉት ቃል አቀባይዋ “ከባድ ዝናብ እና ሞቃታማ አካባቢ አውሎ ነፋሶችንም (tropical cyclones) እየታዘብን ነው። ስለዚህ፣ በፍጹም በእረፍት ስሜት ውስጥ አይደለንም” ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የድርቅ ስጋት አሳሳቢ መሆኑን ነው የጠቆሙት፤ ይህም በግብርና፣ በመጓጓዣ፣ በኃይል አቅርቦት እና በወንዝ የውኃ መጠን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ነው የገለፁት። የዱር እንስሳት ላይ አደጋን ይጨምራል የሚል ስጋትንም አስከትሏል።

ባሳለፍነው ጥር እና የካቲት ወር ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ 40 የሚጠጉ የዘርፉ ሳይንቲስቶች፤ መዳረሻቸውን ‘ትዌይትስ’ ወደተባለው ግዙፍና ራቅ ያለ የበረዶ ግግር አድርገው ነበር። ይህ የበረዶ ግግር፣ ወደፊት ለሚመጡት ትውልዶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የባሕር ከፍታ መጨመር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል እርግጠኛ ያልሆነ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያለው ነው።

ሳይንቲስቶቹ ጥናታቸውን ለማካሄድ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የዋልታ አካባቢ የአየር ሁኔታ በመቋቋም የሠሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ስላሉት ለውጦች አዳዲስ መረጃዎችንና ግንዛቤዎችን ይዘው ተመልሰዋል።

እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ የሙቀት መጨመር  በረዶውን በፍጥነት እያቀለጠ ነው፡፡

በሌላ በኩል በኤል ኒኖ (El Niño) መከሰት ምክንያት በየቦታው አሰሳሳቢ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ኤል ኒኖ የአየር ሁኔታ ሥርዓቶችን በማወክ እና የዓለምን የሙቀት መጠን በማሳደግ የሚከሰት፣ በተፈጥሮ የሚደጋገም እና ብዙውን ጊዜ በታኃሳስ ወር የሚበረታ የአየር ንብረት ክስተት ነው።

ኤል ኒኖ የዓለምን የሙቀት መጠን በመጨመር እንዲሁም በተለያዩ አህጉራት ድርቅን እና የሰብል ውድመትን በማስከተል ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ዘንድሮም ኤል ኒኖ እጅግ ከፍተኛ እና ዓለምን እየለወጠ ያለ ክስተት ሆኗል፡፡ ይህ በየጊዜው የሚከሰት የአየር ንብረት ክስተት በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በአሁኑ ወቅት በሦስት አህጉራት ላይ ድርቅን እና የሰብል ውድመትን እያስከተለ ይገኛል።

በዓለም ላይ ከፍተኛ ዝናብ ከሚያገኙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ፓናማ፣ አንዳንድ አካባቢዎቿ ከግንቦት ወር መጀመሪያ አንስቶ ምንም አይነት ከባድ አውሎ ንፋስ አላስተናገዱም። የኢትዮጵያ ለም የደጋማ አካባቢዎችም ባለፉት አራት ዓሥርት ዓመታት እጅግ ደረቅ የበጋ ወቅቶችን አሳልፈዋል። እንዲሁም ህንድ ከ1901 ጀምሮ ዘመናዊ የዝናብ መረጃ መመዝገብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አምስተኛውን እጅግ ደረቅ የሆነ የሰኔ ወር አሳልፋለች።

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ (ሳንታ ባርባራ) የአየር ንብረት አደጋዎች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ክሪስ ፈንክ (ዶ/ር)፣ “ይህ የኤል ኒኖ ተጽዕኖ በይፋ መጀመሩን የሚያሳይ ጥሩ ምልክት ነው” ብለዋል።

እነዚህ በተግባር የሚታዩ ውጤቶች በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ የሚከሰቱትን ለውጦች መጠን ያንፀባርቃሉ፤ ኤል ኒኖ የሚፈጠረው ያልተለመደ ሙቀት ያለው ውኃ በዚያ አካባቢ ሲከማች ነው። እነዚህ ክስተቶች ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት የሚከሰቱ ሲሆን፣ ለሺህ ዓመታት ሲከሰቱ የቆዩ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዋዠቆች መንስኤ ሆነዋል። ነገር ግን የዘንድሮው ክስተት ባለፉት 80 ዓመታት ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ ጠንካራው ሊሆን እንደሚችል ነው የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ያስጠነቀቀው።

ሳይንቲስቶች በሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የኤል ኒኖ ክስተቶች ይበልጥ ጠንካራ እና ተደጋጋሚ የመሆን ዕድላቸው እየጨመረ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።

ኤል ኒኖ ሁሉንም ቦታ በተመሳሳይ መንገድ አይመታም። በምሥራቅ አፍሪካ፣ ከሶማሊያ እስከ ታንዛኒያ፣ ከመጠን በላይ ዝናብ ያስከትላል። የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የመንገዶች መዘጋት (በጎርፍ)፣ የክሊኒኮች እና የትምህርት ቤቶች መቋረጥ ከሚከተሉ ችግሮች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።

ከዛምቢያ እስከ ደቡብ አፍሪካ እና ከናሚቢያ እስከ ሞዛምቢክ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ተቃራኒው ይሆናል ማለት ነው፤ በቂ ዝናብ አለመኖር፣  የሰብሎች መበላሸት፣ የውኃ ምንጮች መድረቅ እና የግጦሽ መሬቶች መጥፋት ይከሰታል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የጉዳት ሰለባ ከሆኑ ሀገራት መካከል ማላዊ አንዷናት፤ በማላዊ የምትኖረው ማርታ ካሉምቢ፣ ልጇ በምግብ እጥረት ምክንያት ሆስፒታል የገባች ሲሆን፣ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሰብሎች በመበላሸታቸው ለቤተሰቧ እና በዙሪያዋ ላሉ ሁሉ ምንም ምግብ እንዳላስቀረላቸው ተናግራለች።

“ልጄ ሁልጊዜ ታለቅስ ነበር። ዶክተሮች በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃየች እንደሆነ ነግረውኛል። ልጄ ልትሞት እንደምትችል ፈርቼ ነበር። ሁኔታው በጣም ያሳዝናል” ብላለች፤ ችግሩ ረሃብ ብቻ አይደለም የምትለው ነዋሪወ በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት የውኃ አቅርቦቶች መበከል፣ ይህም የኮሌራ እና የሌሎች የውሃ ወለድ በሽታዎች ወረርሽኝን እና ወባን እንደሚያባብስ ተናግራለች። ከዚህ በተጫማሪም ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ለዘለቄታው ይፈናቀላሉ ብላለች።

በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ዓለማችን ከባድ ችግር ውስጥ መግባቷን በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል፤ እንደ ድርጅቱ መረጃ በየዓመቱ ሰዎች ሁለት ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ ቆሻሻ ይጥላሉ። ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የውኃ አቅርቦትን ከመዝጋት አንስቶ አፈርን እስከ መበከል ድረስ ለአካባቢ ጉዳት መንስኤ ይሆናል፡፡

ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው ደግሞ አካባቢን የመጠበቅ ተግባር ሁሉም በትክክል ሲወጣ እንደሆነ አሳስቧል፤ በተለይም ከፍተኛውን ድርሻ  የሚይዙትን የነዳጅ መኪናዎችን በኤሌክትሪክ በመቀየር ብክለትን መቀነስ እና በአግባቡ ባልተወገደ ቆሻሻ ምክንያት የተበከለ መሬት እና ውኃ በሰዎች፣ በእንስሳትና በእፅዋት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት መገንዘብ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው።

ሰዎች  የሚያስፈልጋቸውን ብቻ መጠቀም፤ እንዲሁም አንድን ነገር መጣል ሲኖርባቸው በትክክለኛው መንገድ ማስወገድ እንደሚገባ፣ ፓርኮችን፣ ወንዞችን፣ የባሕር ዳርቻዎችን እና ሌሎች አካባቢዎችን የማጽዳት ሥራዎች ላይ ሁሉም መሳተፍ ይገባዋል፡፡

ሌላው መፍትሄ ደግሞ  በመኖሪያ አቅራቢያ ወይም በአካባቢው ሀገር በቀል አትክልቶችን መትከል መዳበር እንዳለበት ተጠቁሟል፤ እፅዋት፣ እንስሳት እና ነፍሳት እርስ በርስ የተያያዘ ህልውና አላቸው። አብዛኛዎቹ ነፍሳት ተወላጅ ያልሆኑ ተክሎችን አይመገቡም፤ ይህም ማለት ወፎች እና ሌሎች ዝርያዎች የምግብ ምንጫቸውን ያጣሉ ማለት ነው። በዚህም የተነሳ ብዝኃ ሕይወት ይጎዳል። አንድ ነጠላ ዛፍ ወይም ቁጥቋጦ እንኳን ለተለያዩ ፍጥረታት መሸሸጊያ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ዛፎችን የመትከል ልምድ መዳበሩ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ዓይነተኛ መፍትሔ ነው፡፡

ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን እና ሌሎች ጎጂ ኬሚካሎችን ከመጠቀም መቆጠብም የችግሩ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ነው ድርጅቱ የጠቆመው።

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here