የሐሳብ የበላይነት የሚረጋገጥበት መልካም ዕድል-ምክክር

0
334

ልዩነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መገለጫ ነው፤ ልዩነትን በግጭት ሳይሆን በውይይት መፍታት ደግሞ የሰላማዊ ማህበረሰብ መሠረት ነው። በተለያዩ የዓለም ሀገራት ረጅም ጊዜ የቆዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት የተሞከሩ ሂደቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው።

በተባበሩት መንግሥታት የምክር እና ሰላም ግንባታ ተቋም መረጃ እንደሚያመላክተው ሀገራዊ ምክክር በቀላሉ የሚደረግ  የሀሳብ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ወገኖች ቅሬታቸውንና ስጋታቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቡበት፣ የሌላውን አመለካከት የሚያዳምጡበት እና በጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚሞክሩበት ሂደት ነው።

የደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ኮሎምቢያ እና የሌሎች ሀገራት  ተሞክሮዎች እንደሚያ መላክተው  ምክክር ሰላምን ለማጠናከር፣ በታሪክ የተከማቹ ቅሬታዎችን ለመመርመርና  የወደፊት የጋራ ራዕይ ለመገንባት ያለው  ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ ቢሆንም የእያንዳንዱ ሀገር ታሪክ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ የአንዱን ሀገር ተሞክሮ በቀጥታ ወደ ሌላ ሀገር መተግበር ሳይሆን ከተሞክሮዎቹ ትምህርት መውሰድ ወሳኝ ነው።

ሀገራችንም ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን ለመፍታት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ሥራ ከገባች ሰነባብታለች፤ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው መምከር ከጀመሩም ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በኵር ጋዜጣም ከምክክሩ ቀደም ብሎ የነበሩ ሂደቶችን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘውን ምክክር በተመለከተ በትንታኔ እና በሌሎች አምዶቿ በተከታታይ ስትዘግብ ቆይታለች፤ በዚህ ሳምንት ትንታኔዋም የምክክሩን አሁናዊ ሁኔታ፣ የተሳታፊዎችን እና የባሙያ ምክረ ሐሳብ በማካተት መረጃዎችን አጠናቅራለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ይፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያዊያን እየመከሩ የሚገኙት በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ነው፡፡  በዚህም አራት ሺህ ተመካካሪዎች፣ ስምንት ተመካካሪ ቡድኖች፣ 16 ስልታዊ ቡድኖች፣ 160 አመካካሪዎች፣ 158 ቃለ-ጉባዔ ያዦች፣ 80 የባለሙያዎች ቡድን (Panel of Experts) እና 336 የክልል እና የፌዴራል ተወካዮች እየተተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳስታወቁት  ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ እየተጠናከረ እና ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በምክክሩ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ አለመግባባቶች፣ ክርክሮች እና ስሜታዊነት እንደነበሩ በማንሳት ይህም ተፈጥሯዊ እና በውይይት ሂደት ውስጥ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል። “አሁን ላይ የግል እና የቡድን ሃሳቦችን በመተው ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉ የጋራ ሃሳቦች ወደ መሀል እየመጡ ይገኛሉም” ብለዋል።

“እስካሁን  ድረስ  በአንድም  አጀንዳ  ላይ የተሰጠ  ውሳኔ  የለም፤  ወደ  ፊትም     አይኖርም፡፡ ኮሚሽኑ ውሳኔ የሚያሳልፍ ሳይሆን በሕግ አውጭው፣ ሕግ አሥፈጻሚው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ተባብረው ሀገርን የሚደግፉ የምክር ሃሳቦችን እንዲያዘጋጁ ማገዝ ነው” በማለት የኮሚሽኑን የሥራ ድርሻ እና ኃላፊነት አስገንዝበዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ እንደገለጹት ሂደቱ በተለያዩ ቡድኖች ሀሳቦች እየተንሸራሸሩ፣ መተማመን እየተፈጠረ፣ ቃለጉባዔ እየተያዘ እና እየተሰነደ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። በምክክሩም ኢትዮጵያውያን በነጻነት ተወያይተው የጋራ ርዕይ እንዲቀርጹ እና ካለፉት ችግሮች ተሻግረው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፍቱ ትልቅ መንገድ የሚከፍት ነው።

“ምክክር የሚደረግባቸው ስምንቱም አጀንዳዎች የግድ ውጤት ላይ ሊደርሱ አይችሉም፤ ይልቁንም የሚያድሩ የተወሰኑት አጀንዳዎች  ለቀጣዩ ትውልድ ሊሻገሩ የሚችሉ ይኖራሉ። ምክክር እየተደረገባቸው ካሉ ስምንት አጀንዳዎች መካካል በተወሰኑት ላይ በእርግጠኝነት ጥሩ ምክረ ሀሳብ ይዘን እንቀርባለን” በማለት ፕሮፌሰር መስፍን   አብራርተዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከአራት ሺህ ተሳታፊዎች ጋር የሚደረገው የውይይት ምዕራፍ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በመጨረሻም የተሰበሰቡትን የአራት ሺህ ተሳታፊዎች ሃሳቦችን አጠናቅሮ ለተግባሪ አካላት በማስረከብ ትግበራቸውን የመከታተል ሥራ እንደሚከናወን አስገንዝበዋል።

ተሳታፊዎች ሚኒሥትሮች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የተካተቱበት የሁሉንም ኢትዮጵዊ ስሜት ይዘው የመጡ መሆናቸውን በማንሳት ኮሚሽኑ ሂደቱን በትዕግሥት እና በትሕትና እየመራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎችን(ኤክስፐርቶች) ያሉበት አሠራር ዘርግቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመነጋገር መፍትሔ እየሰጠ መሆኑንም አክለዋል።

የምክክሩ ተሳታዎች እንዳሉት በሀገራቸው በተለያዩ አካባዎች የሚታዩ አለመግባባቶች መሠረታዊው ምክንያት ችግርን በምክክር የመፍታት ልምምድ ባለመዳበሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተከካሄደ የሚገኘው ምክክር ታዲያ ቅራኔዎችን በሐሳብ የበላይነት ለማሸነፍ ታሪካዊ ዕድል ነው። ችግሮችን እና የሀሳብ ልዩነቶችን በአጀንዳነት ሰብስቦ በመወያየት መፍትሔ ለማምጣት ምክክሩ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም ምክክሩ ኢትዮጵያውያንን ያሰባሰበ እና ልዩ ልዩ ሀሳቦች እየተንጸባረቁበት ነው። በዚህም ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን የሚያሻግር ሀሳብ በጋራ እያዋጡ ይገኛሉ። በምክክሩ የማይጠቅሙ ትርክቶችን በመተው አዲስ መሠረት በመጣል ኢትዮጵያን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ መፍትሔ እንደሚያመጣም ነው ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን የሰጡት።

የሃይማኖት ጉዳዮች እና የሰላም ግንባታ አጀንዳዎችን ጨምሮ በአራት አጀንዳዎች ላይ ተመካካሪዎች ባቀረቧቸው ምክረ ሃሳቦቻቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውንም የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። ቡድኖቹ በተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦቻቸው ላይ ተስማማተው በተዘጋጀው ቃለ ጉባዔ ላይ ተፈራርመዋል፡፡ በኮሚሽኑ የአሠራር ሥነ-ዘዴ መሠረት 500 አባላት ያሉት አንድ ቡድን በአንድ አጀንዳ ላይ እየተመካካረ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ በሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ሲመካከሩ የቆዩት እያንዳንዳቸው 500 አባላት ያሏቸው የሥራ ቡድኖችም ተጠናቅረው በቀረቡ የአጀንዳ ምክረ-ሀሳቦች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን በተዘጋጁት የቃለ-ጉባዔ ሰነዶች ላይ በመፈረም ማረጋገጣቸውን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

በመካሄድ ለይ የሚገኘውን ሀገራዊ ምክክር በተመለከተ አሚኮ ያነጋገራቸው በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ምስክር ከተማ “ሀገራዊ ምክክር ልክ እንደ ቤተሰብ በጋራ ችግሮቻቸው ላይ ተመካክረው እንደሚፈቱት ሁሉ በሕዝቦች መካከል ያሉ የዘመናት አለመግባባቶች የሚፈቱበት ትልቅ የሰላም መድረክ ነው” ብለዋል።

መምህሩ እንዳስገነዘቡት የሐሳብ ልዩነት እንደ ዕድል መታየት አለበት። በምክክር ሂደቱ ውስጥ የሚነሱ የሃሳብ መለያየቶች እና ፍጭቶች እንደ መጥፎ አጋጣሚ ሊወሰዱም አይገባም፤  ይልቁንም የሃሳብ ፍጭት ውይይቱ በስሎ የጠራ ሃሳብ እንዲመጣ እና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ትልቅ ዕድል ይሰጣል።

“ፍጭት እና ክርክር ከሌለ ምክክር ራሱ አያስፈልግም ነበር” ያሉት መምህሩ፤ የምክክሩ ዋና ዓላማም በሃሳብ ፍጭት ውስጥ አልፎ የጋራ ሃሳብ ማራመድ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ደግሞ “መከባበር እና መደማመጥ ይነግሳል” ብለዋል።

እንደ መምህር ምስክር ማብራሪያ በሃሳብ መለያየት አለመስማማት ማለት አይደለም፤ ይልቁንም በመቀባበል እና በማስተዋል ወደ ተሻለ ሃሳብ የመሸጋገሪያ መንገድ ነው። ምክክር የውድድር ሳይሆን የጋራ መግባቢያ መድረክ በመሆኑ አሸናፊ እና ተሸናፊ ሳይኖር የሃሳብ የበላይነት ብቻ መረጋገጥ ይገባዋል።

ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሚያራርቁ ይልቅ የሚያቀራርቡ እና የሚያስተሳስሩ በርካታ ጉዳዮች እንዳሏቸው ነው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ያስረዱት።

እንደ አቶ ምስክር ገለጻ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ብዙ ጠላቶች ሚነዙትን ሀሰተኛ መረጃ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ተመካክሮ ሀገር መገንባት እንጂ መደናገር አያስፈልግም። ኅብረተሰቡ መረጃዎችን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫዎች እና ከታማኝ የሚዲያ ተቋማት ብቻ መከታተልም ይገባዋልም።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የአብሮነት እሴት ያላት ሀገር እንደሆነች የጠቀሱት መምህሩ በምክክር ሂደት በመግባባት ለጋራ ሀገር በጽናት መቆም የሁሉንም ዜጋ ድርሻ እንደሚጠይቅ ገለወጸዋል። ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ጊዜን እና ትዕግስትን እንደሚጠይቅ  አስገንዝበዋል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የነሐሴ 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here