ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ የባህልና የቋንቋዎች ህብረ-ቀለማት ያሸበረቀች የጋራ መኖሪያችን ናት። ይህ ብዝሃነት የውበታችንና የጥንካሬያችን ምንጭ መሆን ሲገባው፣ የታሪክ አጋጣሚዎችና የፖለቲካ ቅራኔዎች በጥርጣሬና በግጭት ጥላ ስር እንዲያልፍ አድርገውታል። በብዙሃን ሀገር ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ልዩነቱን በኃይል ለመፍታት መሞከር ግን ሀገርን ለብጥብጥና ለውድመት ይዳርጋል። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር እነዚህን የዘመናት ቅሬታዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት፣ ሀገርን በጥንካሬና በጽናት የማቆም ታሪካዊ ዕድል ነው፡፡
በብዙሃን ሀገር በምክክር ሀገርን የማጽናት ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ምክክር በዋናነት የመወያየት፣ የመነጋገርና የ«ሰጥቶ መቀበል» ባህልን በማጎልበት አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበትን አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ይፈጥራል። በአንድ የብዙሃን ሀገር ውስጥ በኃይል የበላይነትን ለመጫን መሞከር የአንዱን አሸናፊነት፣ የሌላውን ደግሞ ተሸናፊነት ስለሚያስከትል ለተጨማሪ በቀልና ግጭት መንገድ ይከፍታል። በምክክር ሂደት ግን ሁሉም ወገን እኩል ድምፅና ቦታ ስለሚኖረው፣ የመጨረሻው ውጤት የሁሉንም ፍላጎት ያከበረ ሁሉንም አሸናፊ (Win-Win) የሚሆንበትን መንገድ ያመቻቻል። ይህም ሀገርን ከብጥብጥና ከውድመት ይታደጋል።
በምክክር ሂደት መሠረታውያን እና ሊካተቱ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ሁሉን አቀፍ አካታችነት አንዱ ነው፡፡ የምክክሩ ሂደት ማንኛውንም የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የብሔርና የሃይማኖት ስብጥር ሳይለይ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ የሚያካትት መሆን አለበት። ሌላኛው ግልጽነትና ታማኝነት ነው፡፡ አጀንዳዎችን ከመቅረጽ ጀምሮ እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ያለው ሂደት ለህዝብ ግልጽና እምነት የሚጣልበት ሊሆን ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም የመናገርና የሐሳብ ነፃነት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም ተሳታፊዎች ያመኑበትን ሐሳብ ያለ ምንም ፍርሃት፣ ከጫናና ስጋት ነፃ ሆነው የሚያንፀባርቁበት መድረክ መረጋገጥ አለበት።
በነዚህ ሁሉ ሂደቶች ተመካካሪዎች የሌሎችን ሐሳብ ማክበር፣ ታጋሽና የመፍትሔ አካል የመሆን ጥበብን በማዳበር ውይይትና ምክክር የስልጣኔና የብስለት መገለጫ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ የሌሎችን ሐሳብ ማክበር ማለት በሐሳቡ ሙሉ በሙሉ መስማማት ማለት ሳይሆን፣ የመናገርና የመደመጥ መብትን አምኖ መቀበል ማለት ነው። በምክክር ሂደት ውስጥ የራስን ሐሳብ ብቻ ለማሳመን ከመቸኮል ይልቅ የሌሎችን ስሜትና ቅሬታ በትዕግሥት ማዳመጥ ቀዳሚው ተግባር ነው። የዘመናት ቁስሎችንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ከፍተኛ ትዕግሥትና አስተዋይነት ይጠይቃል። እያንዳንዱ ተሳታፊ የችግሩ ጠቋሚ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሔው አካል ለመሆን የራሱን ፍላጎት ከሀገር ጥቅም ጋር አጣጥሞ የመጓዝ ጥበብ ሊኖረው ይገባል።
በምክክር ሂደት ውስጥ አለመግባባቶችና የሐሳብ ግጭቶች መከሰታቸው አይቀርም። እነዚህን አለመግባባቶችን መፍትሔ ለመስጠትና ለመፍታት የጋራ የሆነውንና ትልቁን የሀገር ስእል በማሰብ በልዩነቶች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የሚያስማሙ ሀገራዊ እሴቶችና የጋራ ጥቅሞች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማሳካት በሰከነ መንፈስ ስሜታዊነትን አስወግዶ በምክንያት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክክር ከጠንካራ አቋሞች በመለስ ሀገርንና ህዝብን የሚያድኑ ሃሳቦችን በማፍለቅ ወደመሀል በመምጣት የመፍትሔ መንገዶችን መስጠትና መቀበል ያስፈልጋል። በምክክር ሂደት ውስጥ የሐሳብ መለያየትና አለመስማማት ማጋጠሙ የተፈጥሮ ሕግ ነው። እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት በመጀመሪያ ደረጃ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ጠላትነት ሳይሆን እንደ ዕድልና ይበልጥ የጠራ ሐሳብ ማፍለቂያ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል። ከአካታችነትና ከሀገር ጥቅም አንጻር መቻቻልን መርህ በማድረግ ቅራኔዎችን ወደ መፍትሔ መቀየር ይቻላል።
ይህ ምክክር ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ይህ ሂደት በሀገራችን በየጊዜው ለሚከሰቱ ብጥብጦችና አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትና የሕግና የሐሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተከፈተ ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። የሐሳብ ልዩነትን እንደ ጠላትነት ሳይሆን እንደ ዕድል በመቁጠር፣ በትዕግሥትና በመከባበር በመወያየት ሀገራችንን ከውድመት ታድገን ለትውልድ የምትመች በጽናት የተገነባች ኢትዮጵያን ማቆየት የሁላችንም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።


