በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉ የስፖርት ዘርፎች መካከል የሚክስድ ማርሻል አርት (ኤም ኤም ኤ) እና ቡጢ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ማርሻል አርት በስህተት የኃይል ጥቃት እንደሆነ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይታሰባል፤ ይሁን እንጂ ራስን መግዛት፣ አክብሮት እና ስነ-ስርዓት የሚያስተምር የስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ ወጣቶች ጊዜያቸውን ወደ ጤናማ ስፖርት እንዲያውሉ በማድረግ ከአልኮል፣ ከጫት፣ ከአደንዛዥ ዕፅ እና ከወንጀል ድርጊቶች ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ለወጣቶች ጠንካራ በራስ መተማመንን፣ የጽናትን እና የሥራ ወኔን ያሰርጻል፡፡
በኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ ስፖርቶች ከፍተኛ የወጣቶችን ትኩረት እና የሕዝብ ተወዳጅነትን እያገኙ መጥተዋል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ የሚዘጋጁ እነዚህ የትንቅንቅ ውድድሮች የስፖርቱን አዲስ ምዕራፍ እያበሰሩት ይገኛሉ፡፡ ይህ እየተስፋፋ የመጣው መድረክ ለሀገራችን ስፖርት እድገት፣ ለኢኮኖሚ መነቃቃት እና ለማህበራዊ ለውጥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
የኢትዮጵያ የቡጢ እና የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርት ታሪክ ረጅም እድሜ ያለው ሲሆን ሀገራችን በተለያዩ የኦሊምፒክ እና የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በርካታ ተወዳዳሪዎችን ማሳተፏን የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል፡፡ እንደ ውሹ፣ ቴኳንዶ፣ ካራቴ እና ጁዶ ያሉ ማርሻል አርትስ ያሉት የስፖርት ዓይነቶችም በኢትዮጵያ ባህል ሆነዋል፤ በርካታ ተከታዮችንም አፍርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ስፖርቶች ለረጅም ጊዜ በተናጠል እና በአማተር ደረጃ ብቻ ተወስነው ነው የቆዩት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የማርሻል አርት ዘርፎችን ወደ አንድ የሚያመጣው የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርት ብቅ ማለት ለነባሮቹ ስፖርቶች አዲስ እድል ፈጥሯል፡፡ በተለይም በስዊት ቦክስ መስራች እና ፕሮሞተር ጌታቸው መለሰ አማካኝነት የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ፍልሚያ ሻምፒዮንሺፕ (ኢቲኤፍሲ) እና እንደ አድዋ ፋይት ናይት ያሉ ታላላቅ የውድድር ምሽቶች በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ውስጥ ያልተለመደ አዲስ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡
በአድዋ ድል መታሰቢያ (ቤተ መዘክር) አዳራሽ ውስጥ ቡጢን፣ የድብልቅ ማርሻል አርት እና ሙአይ ታይን (የታይላንድ ቡጢ) በአንድ መድረክ በማቀናጀት የተካሄዱት እና በስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት የፈጠሩት እንደ ጆኒ እና ንቃተ ህሊና እንዲሁም ሲጠበቅ የነበረው የጆኒ እና የሴዶ ፍልሚያዎች የስፖርቱን ተመልካች ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገውታል፡፡
እነዚህ ውድድሮች ስፖርቱ ከክለብ ልምምድ አልፎ ወደ ትልቅ የመድረክ ትርዒት፣ የገበያ እና የሚዲያ ትኩረት እንዲቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ አሳርፈዋል፡፡ አሁን ላይ የድብልቅ ማርሻል አርት ውድድሮች መዘጋጀታቸው በተናጠል ሲሰለጥኑ ለነበሩ አትሌቶች ሰፊ የመወዳደሪያ መድረክ ከፍቷል፡፡ ይህም ስፖርተኞቹ ሁለንተናዊ ብቃት እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ የሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ሳይንሱን እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት የማርሻል አርት ስፖርተኞች ከሀገር ውስጥ ውድድሮች እና አልፎ አልፎ ከሚገኙ ብሄራዊ ቡድን ውድድሮች ውጭ የረባ የገቢ ምንጭ እና የሙያ እድገት አልነበራቸውም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ፍልሚያ ሻምፒዮንሺፕ እና በተለያዩ አዘጋጆች የተፈጠሩት የቡጢ እና የድብልቅ ማርሻል አርት መድረኮች አትሌቶች ፕሮፌሽናል ሆነው እንዲወዳደሩ፣ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ መንገድ ጠርጓል፡፡ ይህ ሂደት እንደ ዩ ኤፍ ሲ፣ ዋን ሻምፒዮንሺፕ፣ ፒ ኤፍ ኤል እና ብሬቭ ላሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ መድረኮች የሚደርሱ ብቁ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት መሰረት ይጥላል ተብሎ ይገመታል፡፡
የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርት እጅግ ውስብስብ እና ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት ሳይንስ ግንዛቤን እያሳደገው ይገኛል፡፡
ስፖርተኞች ከአካል ብቃት በተጨማሪ የክብደት ቅነሳ ሳይንስን፣ የተመጣጠነ ምግብ አጠቃቀምን እና ከፍተኛ የአእምሮ ዝግጁነትን እንዲላበሱ እያደረጋቸው ነው፡፡ ይህ ታዲያ ዘርፉን ወደ ዘመናዊ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡
የቡጢ እና የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ውድድሮች በኢትዮጵያም መዘጋጀታቸው ለስፖርተኞች፣ ለአሰልጣኞች፣ ለአካል ብቃት ባለሙያዎች፣ ለዳኞች፣ ለደህንነት ሰራተኞች እና ለዝግጅት አስተባባሪዎች ሰፊ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡
የንግድ ተቋማት የውድድሮቹ ስፖንሰር እየሆኑ ነው፤ የቲቪ ስርጭት እና የዲጂታል የሚዲያ መብቶችም አዲስ የገቢ ምንጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ተወዳዳሪዎች እና ተመልካቾች የሆቴል፣ የትራንስፖርት እና የስፖርት ቱሪዝም ዘርፉን ያነቃቁታል ተብሎ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ትታወቃለች፡፡
አሁን እየተስፋፋ የመጣው የቡጢ እና የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርት ሀገሪቱ በሌሎች ስፖርቶችም ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም የሚያሳይ ተጨማሪ እድል ይፈጥራል፤ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የስፖርቱ እድገት ገና በጅምር ላይ በመሆኑ ዘርፉን የሚመራ የተደራጀ ፌዴሬሽን በሚፈለገው ደረጃ አልተቋቋመም፡፡
ይህም ውድድሮች የሚመሩበት ወጥ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋት ክፍተት እንዲፈጠር፣ የዳኞች እና የአዘጋጆች የብቃት ማረጋገጫ መስፈርት እንዳይኖር እንዲሁም በስፖርተኞች ዘንድ ስነ ምግባር እንዳይኖር አድርጎታል፡፡
የድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርቶች ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ በመሆናቸው ጥብቅ የህክምና ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በሀገራችን አሁንም ከውድድር በፊት እና በኋላ የሚደረጉ የጭንቅላት እና የደም ምርመራዎች ውስንነት ይታያል፡፡ በውድድር ወቅት የሚደርሱ አፋጣኝ ጉዳቶችን ለማከም የሚያስችል የሰለጠነ የስፖርት ህክምና ቡድን እጥረት እና ስፖርተኞች ለጉዳት የሚያጋልጥ የተሳሳተ የክብደት ቅነሳ ዘዴዎችን የመጠቀም አደጋም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከውድድር በፊት ስፖርተኞች የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ከስፖርቱ ሕግጋት ያፈነገጠ እና እጅግ ስነምግባር የጎደለው ሊታረም የሚገባው ችግር እንደሆነ ጭምር ታዝቤያለሁ፡፡
አብዛኞቹ የማርሻል አርት ክለቦች ዘመናዊ መዋቅር፣ የቡጢ ቀለበት እና የስፖርት ቁሶች እጥረት እንደሚኖርባቸው የማይደበቅ ሀቅ ነው፡፡
ስፖርቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የድብልቅ ማርሻል አርት እና የፕሮፌሽናል ቡጢ ውድድር ወጥ በሆነ መንገድ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአሰልጣኞች እና የዳኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን ማዘጋጀትም ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡
ስፖርተኞች ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት የተሟላ የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉ እና የህይወት፣ የጉዳት ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው መደረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ለማርሻል አርት ማዕከላት ምቹ ከባቢ መፍጠር ይጠበቅበታል፤ የግል ባለሀብቶች ደግሞ ስፖርቱን እንደ ኢንቨስትመንት አይተው በስፋት ሊገቡበት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት መሰል ውድድሮች መዘጋጀታቸው የወጣቶችን የተደበቀ አቅም የሚያወጡ፣ አዳዲስ የሥራ እድሎችን የሚፈጥሩ እና የስፖርት ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ናቸው፡፡ የሀገራችንን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም ያስገኛሉ፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


