የኃያላኑ የዋንጫ ሽኩቻ

0
121

የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች አዲስ የውድድር ዘመን ሲጀምሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ቀልብ ከሚሳብባቸው መድረኮች መካከል የስፔን ላሊጋ አንዱ ነው፡፡ የስፔን ክለቦች በአህጉራዊ መድረኮች ያላቸው የታሪክ የበላይነት እና የዓለም ምርጥ ተሰጥኦዎች መዳረሻ መሆናቸው ላሊጋው የተለየ የትኩረት ማዕከል እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲጀመር በሜዳው ላይ የሚታየው ከፍተኛ ፉክክር ብቻ ሳይሆን ሊጉ ያካተታቸው አዳዲስ የእግር ኳስ ኮከቦች፣ ታዋቂ አሰልጣኞች እና የታክቲክ አስተሳሰቦች የውድድር ዘመኑን እጅግ ማራኪ አድርገውታል፡፡

ምንም እንኳ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም ላሊጋው በቴክኒክ የበሰለ፣ ታክቲካዊ ጥልቀት ያለው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በደጋፊዎች ልብ ውስጥ የነገሡ ግዙፍ ክለቦችን የያዘ መድረክ መሆኑ ተወዳጅ እንዲሆን እንዳደረገው የያሆ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ በታክቲክ ረገድ ላሊጋው ከቀደመው ቀዝቃዛ የኳስ ቅብብል ወጥቶ ፍጥነት የተሞላበት፣ ፋታ የሌለው እንቅስቃሴ እና ፈጣን የኳስ ሽግግር እንደምንመለከት ጎል ዶትኮም ጠቁሟል፡፡

የዘንድሮው የዋንጫ ፉክክር እጅግ አስደሳች እና እልህ አስጨራሽ እንደሚሆን ከመክፈቻው ሳምንት ጀምሮ ፍንጮች ታይተዋል፡፡ ሪያል ማድሪድ የውድድር ዘመኑን የጀመረው በዓለም ላይ ካሉ እጅግ አስፈሪ የፊት መስመር ተጫዋቾች ምርጦችን  ይዞ ነው፡፡ እንደ ኪሊያን ምባፔ፣ ቪኒሲየስ ጁኒየር፣ ጁድ ቤሊንግሃም እና ሮድሪ ያሉ ተጫዋቾች በአንድ ቡድን ውስጥ መሰባሰባቸው ለየትኛውም ተጋጣሚ ቡድን ቅዠት እንደሚሆኑ ይጠበቃል ይላል፤ የኤስፒኤን መረጃ፡፡

ታዲያ ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቢው የተመለሱት  አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ዋነኛ ፈተና ይህንን የከዋክብት   ስብስብ ሜዳ ላይ በተገቢው የታክቲክ ሚዛን ማሰለፍ እንደሆነ መረጃው ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ሞሪንሆ የቡድኑን የኋላ እና የመሃል ሜዳ ክፍል ይበልጥ ለማጠናከር እንደ በርናርዶ ሲልቫ፣ ማርክ ኩኩሬላ፣ ያን ዲዮማንዴ፣ ሮድሪ እና ዴንዘል ደምፍሪስን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድናቸውን ይበልጥ ጠንካራ እና ቀጥተኛ አድርገው ገንብተውታል፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት ተከታታይ የውድድር ዘመናት ዋንጫውን በማንሳት የበላይነቱን የያዘው ባርሴሎና በአሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ ስር አዲስ  የማጥቃት ሰልት ይዞ ውድድሩን ጀምሯል፡፡

አንጋፋው አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶውስኪ ክለቡን በይፋ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሀንሲ ፍሊክ እንደ አንቶኒ ጎርደን እና ካሪም አዴዬሚ ያሉ ፈጣን  አጥቂዎችን  አስፈርሟል፡፡

በላማሲያ የወጡትን ድንቆቹን ላሚን ያማል፣ ፓው ኩባርሲ፣ ፔድሪ እና ጋቪን ከራፊንሃ እና ዳኒ ኦልሞ ጋር በማጣመር እጅግ ፈጣን፣ ጫና ፈጣሪ እና እንደ አለት የጠነከር የኋላ ክፍል  አዋቅረዋል፡፡

አትሌቲኮ ማድሪድም ቢሆን አንቷን ግሪዝማን መልቀቁን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ  አዲስ የፊት መስመር እና የኋላ ክፍል ይዞ ቀርቧል፡፡ ምንም እንኳ የአልቫሬዝ ዝውውር ስፔናዊውን አሰልጣኝ ረፍት ቢነሳውም ከባላንጣው እና ከተማ ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ለመፋለም የቡድናቸውን የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረውታል፡፡ ከታላላቆቹ ኃያላን ክለቦች ጀርባ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚደረገው ትንቅንቅም አጓጊ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ በርካታ ክለቦች አዳዲስ አሰልጣኞችን በመሾም የውድድር ዓመቱን መጀመራቸው   ፉክክሩ ከሳምንት ሳምንት ይበልጥ እንዲናፈቅ አድርጎታል፡፡

አትሌቲክ ቢልባኦ የቀድሞውን የዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚችን በመቅጠር በወንድማማቾቹ ኒኮ ዊሊያምስ እና ኢናኪ ዊሊያምስ ፈጣን እንቅስቃሴ ታግዞ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል፡፡ ቪያሪያልም በአዲሱ ወጣት አሰልጣኝ ኢኒጎ ፔሬዝ ስር ገና ከወዲሁ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እግር ኳስ እያሳየን ይገኛል፡፡ ሪያል ሶሲዳድ በአሰልጣኝ ፔሌግሪኖ ማታራዞ እና  ሪያል ቤቲስ  በአንጋፋው ማኑኤል ፔሌግሪኒ እየተመሩ የአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ ለመሆን እንደሚፋለሙ የጎል ዶት ኮም መረጃ አስነብቧል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከወራጅ ቀጣናው ለመትረፍ የሚደረገው ፍልሚያ ልክ እንደ ዋንጫው ፉክክር እጅግ አስፈሪ እና እልህ አስጨራሽ እንደሚሆን በርካታ የስፖርት መገናኛ አውታሮች ከወዲሁ እየጠቆሙ ነው፡፡

ከሁለተኛው ዲቪዚዮን አዲስ ያደጉት እና ወደ ላሊጋው የተመለሱት እንደ ዴፖርቲቮ ላኮሩኛ፣ ራሲንግ ሳንታንዴር እና ማላጋ ያሉ ክለቦች በሊጉ ካለው ከፍተኛ የጨዋታ ፍጥነት እና ጥራት ጋር ለመላመድ ከፍተኛ ፈተና ይገጥማቸዋል ብሎ እንደሚታሰብ መረጃው ያትታል፡፡ እንደ ኤልቼ፣ ራሲንግ ሳንታንዴር እና ራዮ ቫሌካኖ ያሉ ቡድኖችም የመከላከል ድክመታቸው ለውድቀት ያጋልጣቸዋል ሲል መረጃው ይጠቁማል፡፡

በአስተዳደራዊ እና በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኙት  ሌቫንቴ፣  ሲቪያ እና ቫሌንሲያ ያሉ ክለቦች በፍጥነት ካላገገሙ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ከወራጅ ቀጣናው ስጋት ላያመልጡ ይችላሉ ብሎ ማርካ ዘግቧል፡፡

ታዲያ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ኤልቼ፣ ራሲንግ ሳንታንዴር እና ሌቫንቴ ወደ ታችኛው ሊግ የመውረድ  እድላቸው ከፍ ያለ ነው፤ እንደ ጎል ዶት ኮም ግምት፡፡

የሊጉ ጥብቅ ፍትሐዊ የገንዘብ አወጣጥ ደንብ ክለቦች ከገቢያቸው በላይ ወጪ እንዳያደርጉ ገድቧቸዋል፡፡ ይህ ሕግ ክለቦችን ከኪሳራ ቢታደጋቸውም በአውሮፓ የዝውውር ገበያ ላይ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር በእኩል አቅም እንዳይፎካከሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ክለቦች ወደራሳቸው አካዳሚዎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ እና ጠንካራ  ወጣቶችን እንዲያፈሩ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡

የዘንድሮው የስፔን ላሊጋ የዋንጫ ፍልሚያ በሆዜ ሞሪንሆው፣ በሀንሲ ፍሊክ  እና በዲዬጎ ሲሞኔ መካከል አጓጊ ፉክክር እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ሪያል ማድሪድ ባለው የከዋክብት ጥራት ዋንጫውን የማንሳት ከፍተኛ እድል ሲኖረው ባርሴሎና ደግሞ በአዲሱ ታክቲክ ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ ይዘልቃል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡

ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አትሌቲክ ቢልባኦ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታዎችን ይዘው ያጠናቅቃሉ ተብሎ ሲገመት ኤልቼ፣ ራሲንግ ሳንታንዴር እና ሌቫንቴ ደግሞ ወደ ታችኛው ሊግ ይወርዳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

የዘንድሮው የላሊጋ ውድድር በሜዳ ላይ ድንቅ እግር ኳስ፣ በታክቲክ የበሰለ ትዕይንት እና ባልተገመቱ አስገራሚ ውጤቶች የተሞላ ድንቅ የእግር ኳስ የውድድር ዘመን እንደሚሆን ከወዲሁ የማርካ ዘገባ ያስነብባል፡፡

ዘንድሮም ላሊጋው አዳዲስ ታዳጊዎችን ለዓለም እግር ኳስ ለማበርከት እንደማይነጥፍ የጎል ዶትኮም መረጃ ያስነብባል፡፡ ከባለተሰጥኦው ላሚን ያማል በተጨማሪ እንደ አርዳ ጉለር እና ኤንድሪክ ያሉ ወጣቶችም የሊጉ ድምቀት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የላሊጋ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር (ፒቺቺ) ፉክክር በምባፔ፣  በሶርሎት፣ በሉክማን፣ በራፊንሃ እና በቪኒሲየስ መካከል ይደረጋል ሲሉ ብዙዎቹ የስፔን ጋዜጦች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here