ወጣቱን ማዳመጥ ሀገርን ማዳን ነው!

0
77

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እ.አ.አ በ1999 ባደረው ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ ነሐሴ 6 ቀን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ተብሎ እንዲከበር ውሳኔ  አሳልፏል። የዚህ ዕለት ዋነኛ ዓላማ የወጣቶችን ድምፅ መስማት፣ በውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እና በዓለም ዙሪያ የሚያጋጥሟቸውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች መፍታት ነው።

የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች የሆነ ወጣት ነው። ይህ አሀዝ ኢትዮጵያ ግዙፍ የሰው ኀይል እና አምራች ዜጋ እንዳላት የሚያሳይ የሥነ-ሕዝብ ጸጋ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጸጋ በአግባቡ በሥራ-እድል ፈጠራ፣ በትምህርት እና በፖለቲካዊ ተሳትፎ ካልተመራ የድህነት፣ የሥራ አጥነት እና የሀገራዊ አለመረጋጋት ምንጭ መሆኑ አይቀርም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ እንዲሁም  በኢትዮጵያ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር “ብዝኃ የወጣቶች እውቀት ለጋራ ትልም!” በሚል መሪ መልዕክት ነሐሴ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ታስቦ ውሏል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ወጣቶች በሀገር ግንባታ፣ በሰላም፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሚና ለማጉላት በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑም ተጠቁሟል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ  ሰብለ ዘውዱ እለቱ በዓለምም ሆነ በሀገር አቀፍ  ደረጃ ሲከበር ወጣቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በማስታወስ እና ኃላፊነታቸውን ይበልጥ እንዲወጡ በማሰብ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥሯ   በአምራች  የዕድሜ ክልል  የሚገኘው ወጣት  ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ወ/ሮ ሰብለ ጠቁመዋል፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኀይል  ለሀገሪቱ  ትልቁ ጸጋ እና አቅም ነው። ወጣቱን ያላሳተፈች፣ የወጣቱን ኀይል በአግባቡ ያልተጠቀመች እና ወጣቱን ታሳቢ ያላደረገች ሀገር የትም መድረስ እንደማትችልም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ የነገ ሀገር ተረካቢ መሆኑን ተገንዝቦ ዛሬ ላይ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ኃላፊነት ትከሻው ላይ እንዳለ ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል።

ኃላፊዋ እንደገለጹት ወጣቱ ይህንን ቀን እያከበረ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፊት አውራሪ ሆኖ በመምራት ላይ እያለ ነው። በመላው ሀገሪቱ 17 ዋና ዋና የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ወጣቱ የህብረተሰቡን ክፍል በማስተባበር አቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ሕጻናትን በመርዳት ላይ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው ወጣቱ ኃላፊነቱን ወደ ተግባር እየቀየረ መሆኑን ነው።  የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራው እስከ መጭው መስከረም መጨረሻ  ይቀጥላል፡፡ ይሁን እንጂ  ተግባሩ  በበጋው ወራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ መንግሥትም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ የወጣቱን ጉዳይ የትኩረት ማዕከል አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ። ወጣቱ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አገልጋይ እና የድርሻውን የሚወጣ እንዲሆንም በጋራ መሥራት ግድ ይላል። ለዚህም ሲባል የተለያዩ ተቋማት፣ ሴቶች እና ወጣቶች በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። በተለይም ይህንን መርሃ ግብር በአማረ መልኩ ለማክበር እና የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ ) ላደረገው ያልተቋረጠ አጋርነት እና ድጋፍ በዕለቱ የከበረ ምስጋና አቅርበዋል። ወጣቱ ጊዜውን በሥራ፣ በመልካም ስብዕና፣ አደራን በመቀበል እና አደራን በመወጣት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በበዓሉ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል አስተያይቱን የሰጠን  ሳሙኤል ወርቅነህ አንዱ ነው፡፡ ወጣቶች የሀገር የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ሀገርን ለማስቀጠል እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ መደመጥ እና መደጋገፍ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

ወጣቱ አክሎም “አንዲት ሀገር እድገቷን ለማስቀጠልም ሆነ ወደ ፊት ለማራመድ የተደራጀ  እና  ጠንካራ  ትውልድ   ያስፈልጋታል፡፡

ለዚህ ደግሞ ወጣቶች መሰረታዊ እና የጀርባ አጥንት ናቸው!” በማለት  የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡  አያይዞም የወጣቶች ቀን ሲከበር ከበዓልነቱ ባለፈ ወጣቱ የሚደመጥበት እና ወደ ተግባር የሚገባበት መሆን እንዳለበት አመላክቷል።

በሀገራችን ያለውን የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር በተመለከተ ወጣቱ ሲያብራራ፤ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ የሥራ እድል ፈጠራ መሆኑን አንስቷል። አብዛኛው ወጣት የተቀመጠው ሥራ ጠልቶ ሳይሆን  የመንገድ መጥፋት ችግር እንደሆነ ጠቁሟል፡፡  በቀጣይ መንግሥትም ሆነ ትላልቅ ካምፓኒዎች ይህንን የሰው ኀይል በማደራጀት፣ አቅጣጫ በማሳየት እና ምቹ የሆኑ የሥራ እድሎችን በማመቻቸት ሊያግዙት እንደሚገባ ጠቁሟል።

የወጣቶች ቀን መከበሩ ዋና ግብ መልካም እና ቅን አሳቢ ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን የሚያምነው ሳሙኤል፤ ሁሉም አካል ኃላፊነቱን በመውሰድ ከወጣቱ ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግና የወጣቱን አቅም በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጭ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ  ወጣት ረድኤት አጉማስ ናት። ረድኤት በበዓሉ ዕለት እንደተናገረችው “የወጣቶች ቀን መከበሩ ለወጣቶች ሰፊ እድልን ይዞ መጥቷል። ቀኑ መከበሩ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምናሰማበት፣ በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች የምናነሳበት እና ለእነዚህ ችግሮች ምን መፍትሔ መፍጠር እንችላለን? የሚለውን በጋራ የምንወያይበት ትልቅ መድረክ ነው “ ስትል የዕለቱን ትርጉም አብራርታለች።

ወጣቶች ባላቸው እውቀት እና አቅም ለምሳሌ በጤናው ዘርፍም ሆነ በሌሎች መስኮች በጎ ፈቃደኛ ሆነው ቢያገለግሉ ለራሳቸውም ትልቅ የሕይወት ልምድ ያገኙበታል፡፡ ይህ ደግሞ እርስ በእርስ ልምድ የሚለዋወጡበት መንገድ  መሆኑንም ጠቁማለች።

ረድኤት በዚሁ መድረክ ዩኒሴፍ ዩ-ሪፖርትን (UNICEF U-Report) ወክላ የተገኘች ሲሆን ተቋሙ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ አላስፈላጊ ከሆኑ ቦታዎች ርቀው እውቀት በሚገበዩባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ፤ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እና አውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና ለተሻለ እድል እንዲዘጋጁ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጻለች።

“ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ወጣቶች የወደፊቱ ጊዜ ብቻ ሳይሆኑ ‘የዛሬም’ ኀይል ናቸው። ዛሬ ላይ ጠንክረን ከሠራን የነገውን ጊዜ የመቀየር ሰፊ እድል አለን። ስለዚህ ሁላችንም ተባብረን አካባቢያችንን እና ሀገራችንን እንቀይር!” ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

በተመሳሳይ አስተያየቷን የሰጠችን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ብሩክታይት ደግአረገ ናት፡፡ “ወጣቶች ዝም ብለው ለራሳቸው ሕይወት ብቻ የሚኖሩ ሳይሆን ማህበረሰባቸውን የሚጠቅሙ ጉልበት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ለማሳየት ቀኑ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ  ወጣቶች  በሀገራቸው ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ረገድ በዓሉ የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን የሚገነዘብበት ነው“ በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።

ወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ያነሳችው ብሩክታይት፤ ወደፊት ካሁኑ በተሻለ ወጣቶችን በማሰባሰብ እና ፍላጎታቸውን የማዳመጥ እድል መፍጠር እንደሚገባ አሳስባለች። በተለይም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወጣቱን ሊያሳትፉ የሚችሉ አሠራሮችን እና ያልተመቹ ሁኔታዎችን በማስተካከል በጋራ እንዲደራጁና እንዲሠሩ ጠይቃለች። ይህ መሆኑ ወጣቱ ሁልጊዜም በሥራ ላይ ንቁ ሆኖ እንዲቆይ የራሱን ዝንባሌ እና ፍላጎት እንዲለይ እንዲሁም ለህብረተሰቡ ያለውን ጠቀሜታ በተግባር እንዲያሳይ ያስችለዋል።

እንዲህ ያሉ መድረኮች በየዓመቱ መዘጋጀታቸው ወጣቶች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ እና አብረው በመሥራት የተሻለ እድል እንዲፈጥሩ ትልቅ አጋጣሚ እንደሚከፍትም ወጣቷ ተናግራለች። ይህን እድል ያላገኙ ሌሎች ወጣቶችም ሐሳባቸውን የሚያካፍሉበት ሰፊ መድረክ ቢመቻችላቸው የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል እምነቷን ገልጻለች።

ዓለማችን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እያደገች መምጣቷን ተከትሎ ወጣቶች ስማርት ስልኮችን እና ኢንተርኔትን በመጠቀም ድምፃቸውን የሚያሰሙበትን መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዩኒሴፍ ወጣቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሀሳብ የሚያካፍሉበት፣ ድምፃቸውን የሚያሰሙበት፣ መብት እና ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቁበት እንዲሁም ትክክለኛ መረጃዎችን በቀላሉ የሚያገኙበት ዩ-ሪፖርት የተሰኘ ዓለም አቀፍ የዲጂታል መድረክ ማዘጋጀቱ በመድረኩ ተጠቅሷል።

አባባል

አንተ ጠንክረህ በዝምታ ስትሠራ፣ ስኬትህ ጮኾ ይናገራል“ -ፍራንክ ኦሽን

“በሕይወትህ ከዚህ በፊት ያልነበረህ አዲስ ነገር ለማግኘት ከፈለግህ አዲስ ሠርተኸው የማታውቀውን ሥራ ለመሥራት መፍቀድ ይኖርብሀል“ -ቶማስ ጄፈርሰን

“በምድር ላይ ትልቁ አስደሳች ነገር ሰዎች ʽአትችልምʽ ያሉህን ሠርተህ ማሳየትህ ነው“ -ዋልተር ባግሆት

“ወንዝ ድንጋይ ቦርቡሮ የሚገባው ኀይለኛ ስለሆነ ሳይሆን ያለማቋረጥ ስለሚፈስ ነው፡፡“ -ጂም ዋትኪንስ

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here