የህብረት ጉልበት – ከችግር ወደ መፍትሔ

0
247

“በከተማችን የኑሮ ውድነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፤ ከዚህ ቀደም ከ350 እስከ 500 ብር ስንገዛ የነበረው  አምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዛሬ ላይ ከሁለት ሺህ ብር በላይ ሆኗል፡፡ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ30 እስከ 50 ብር ይሸጥ የነበረው አሁን ላይ ከ130 እስከ 140 ብር ደርሷል። የድሀው የዕለት ጉርስ የነበረው በቆሎ እንኳን  ከሶሥት ሺህ 500 ብር ተነስቶ ሰባት ሺህ 500 ብር መግባቱ እጅግ አሳዛኝ ነው!” በማለት የገበያ ዋጋ ከስንት ተነስቶ ዛሬ ላይ ስንት እንደደረሰ በሀዘኔታ ሀሳባቸውን ያጋሩን አቶ ቢተው መለሰ ናቸው፡፡

አቶ ቢተው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ  ናቸው፡፡ በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ቢተው  ትዳር መስርተው  አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ በኵር ጋዜጣ ከሰሞኑ ኑሮ እንዴት ነው? ስትል በስልክ ላነሳችላቸው ጥያቄ  ከስንት ተነስቶ ስንት እንደደረሰ  ገልፀዋል፡፡

“መንግሥት የሠራተኛውን ደመወዝ በትንሹ ሲጨምር ነጋዴው ግን ያንኑ ሰበብ አድርጎ በእጥፍ ድርብ ዋጋ ይጨምራል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው “እንኳን ሻይ ቡና ሸጦ የሚያድረው እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ቀርቶ ʽየተሻለ ደመወዝ አለኝʽ የሚለው የመንግሥት ሠራተኛም ኑሮን መግፋት አቅቶታል” በማለት ሀሳባቸውን አክለዋል።

የኑሮ ጫናው በምግብ ሸቀጦች ላይ ብቻ አላበቃም የሚሉት አቶ ቢተው፤ የትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይ፣ የውኃ ክፍያ እና የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ተዳምሮ የሠራተኛውን ጫንቃ አጎብጦታል ይላሉ።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት እኚህ ግለሰብ የኑሮን ጫና ለመቋቋም የግል ትምህርት ቤት ክፍያ ስለከበዳቸው ሦስቱን ልጆቻቸውን  ከግል ትምህርት ቤት አስወጥተው በመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲማሩ አድርገዋል። የቤት ኪራይ በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ  ነው። የውኃ ክፍያም ቢሆን በትንሹ 46 ብር ይከፈልበት ከነበረበት ጊዜ አንጻር አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል። በቀጣይ የገበያውን ንረት ያረጋጋሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የሸማቾች ማህበራት በቂ ምርት በተመጣጣይ ዋጋ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።

ምርቶችን ከአምራች አካባቢዎች (ከገበሬው) በቀጥታ በማምጣት ህብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገለግሉ የሸማቾች ማህበራት አሠራራቸው ሊፈተሽ እና ሊስተካከል እንደ ሚገባም ጠይቀዋል፡፡ “በተለይ ነጋዴው ʽየትራንስፖርት ወጪ ጨመረʽ በሚል ምክንያት በነባር እቃ ላይ ሳይቀር እጥፍ ዋጋ ሲጨምር የሚቆጣጠረው አካል የለም፤ ይህ ማብቃት አለበት!” በማለት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በየዕለቱ የሚያሻቅበው  የምግብ ሸቀጦች፣ የቤት ኪራይ፣ የመጓጓዣ  እና የሌሎችም መሰረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናሩ በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እየጎዳ ይገኛል።

የኑሮ ውድነት ዜጎችን ክፉኛ በሚፈትንበት በዚህ ወቅት ገበያን ለማረጋጋት እና የሸማቹን እንባ ለማበስ ከሚጠቀሱት ተቋማት መካከል የኅብረት ሥራ ማህበራት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። እነዚህ ተቋማት ትርፍን ብቻ ከሚያሳድደው የተለመደው የንግድ አሠራር ወጣ ብለው የሸማቹን እንባ ለማበስ እና የአምራቹን ላብ ዋጋ ለማስከበር የተቋቋሙት የኅብረት ሥራ ማህበራት ናቸው። የኅብረት ሥራ ማህበራት በባህሪያቸው የተቋቋሙት ያልተገባ ትርፍ ለማካበት ሳይሆን የአባላቶቻቸውን እና የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት ነው።

ይህን ዓላማ መርህ አድርገው ምርትን በቀጥታ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ በማድረስ እና ፍትሐዊ የዋጋ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ረገድ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በዳንግላ ከተማ የሚገኙ የሸማቾች ማህበራት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። የዳንግላ ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ቡድን መሪ ወ/ሮ አልማዝ ጌታነህ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ በዳንግላ ከተማ በአሁኑ ወቅት የጡረተኞች እና የአንድነት ሸማቾች የተሰኙ ሁለት መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት ይገኛሉ። የማህበራቱ ዋነኛ ዓላማ ገበያን ማረጋጋት እና ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት በማቅረብ እፎይታ መስጠት ነው። የግብርና ምርቶችን ከምሥራቅ ጎጃም እና ከሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ የአርሶ አደር የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ በማስመጣት ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ ቆይቷል።

በሌላ በኩል እንደ ዘይት፣ ስኳር እና የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከአድማስ ዩኒየን፣ ከቡሬ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከጅንአድ (የመንግሥት የንግድ ድርጅት) በማስመጣት ለከተማዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ለአብነትም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤፍ፣ የዘይት እና የስኳር አቅርቦት ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።

ወ/ሮ አልማዝ እንደገለጹት ማህበራቱ እየሰጡት ያለው  አገልግሎት ለማህበሩ አባላት ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የሸማቹን ፍላጎት ማሟላት እንዳልተቻለ ነው የገለጹት። ምክንያቱን ሲያብራሩም “ያለን የካፒታል አቅም አነስተኛ በመሆኑ ምርቶችን በርካሽ ዋጋ ነው የምናቀርበው ብለን አንኮራም። ነገር ግን በግል ነጋዴው ዘንድ ካለው እጅግ የተጋነነ ዋጋ አንጻር ስናየው ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አቅርበን ገበያን ለማረጋጋት እየሞከርን ነው። ነገር ግን የማህበራቱ ዋነኛ ፈተና አነስተኛ ገንዘብ መሆኑ ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል።

ስለሆነም የሸማቾች ማህበራት የገበያውን ፍላጎት በሰፊው ማሟላት እንዲችሉ በቂ በጀት ወሳኝ ነው። ሆኖም ማህበራቱ የሚፈልጉትን ያህል አቅም ገና አልገነቡም። ባለፈው በጀት ዓመት ማህበራቱን ለመደገፍ ሰባት ሚሊዮን ብር በጀት የተጠየቀ ቢሆንም ሊፈቀድ የቻለው ሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር። ይህ የተሰጠው ድጋፍም በሁለቱ ማህበራት ተከፋፍሎ ሥራ ላይ መዋሉን ወ/ሮ አልማዝ አስታውሰዋል፡፡

በጀቱ ከነባራዊው የዋጋ ንረት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠውን የበጀት እና የብድር ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ነዋሪው የማህበራቱ አባል በመሆን፣ አክሲዮን በመግዛት እና የማህበራቱን ካፒታል በማሳደግ የራሱን የኢኮኖሚ ደጀን በራሱ ሊገነባ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሐም ዳኛው ከበኩር ጋዜጣ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የህብረት ሥራ ማኅበራት ዋነኛ ዓላማ ማኅበረሰቡ በተናጠል ሊፈታቸው የማይችላቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች በጋራ በመደራጀት መፍታት ነው። የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ምክንያቶች ዋነኛው የምርት አቅርቦት ሰንሰለት መርዘም እና አላስፈላጊ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ነው ብለዋል። ማኅበራቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቀጥታ ከአምራቹ ጋር ይገናኛሉ። ማህበራቱ ከምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ እና መኮረኒ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ማህበራቱ ከተለመደው ነጋዴ በምን ይለያሉ?” የሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ የአቶ አብርሐም ምላሽ አጭር እና ግልጽ ነው “በዋጋ፣ በጥራት እና በተደራሽነት!”   ብለዋል። ማኅበራቱ የተቋቋሙት ሸማቹን ለመበዝበዝ ሳይሆን አገልግሎት ለመስጠት በመሆኑ ዋጋቸው ከገበያው የቀነሰ እና አቅምን ያገናዘበ ነው።  በጥራት በኩልም ያልተቀላቀለ እና ንጹህ ምርትን ያቀርባሉ፤ በተደራሽነትም ምርቱን አንደኛው አካባቢ ላይ ብቻ ከማከማቸት ይልቅ እጥረት ወዳለባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች በማከፋፈል የገበያ ሚዛንን ይጠብቃሉ።

የበዓላት ወቅት ሲቃረብ የዋጋ ንረት ማገርሸቱ የተለመደ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ የኅብረት ሥራ ማህበራቱ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት። ለዘመን መለወጫ በዓል ገበያውን ለማረጋጋት ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳን ጨምሮ ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርት እንዲሁም ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንድስትሪ ምርት፣  የምግብ ዘይት፣ ፓስታ እና መኮረኒን ለሸማቹ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

መንግሥት የማህበራቱን ሚና በመረዳት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር ለሸማቾች የህብረት ሥራ ማኅበራት መድቧል። ይህ በጀት ማኅበራቱ አቅማቸውን አጎልብተው በሰፊው ወደ ገበያ እንዲገቡ እና ሸማቹን እንዲታደጉ ትልቅ ጉልበት ሆኗቸዋል።

የኑሮ ውድነት በአንድ ጀንበር የሚፈታ ባይሆንም የኅብረት ሥራ ማህበራት እያደረጉት ያለው ጥረት ግን ተስፋ ሰጪ ነው። መንግሥት፣ አምራቹ እና ሸማቹ እጅ ለእጅ ተያይዘው እነዚህን ማህበራት ካጠናከሯቸው የገበያ መረጋጋትን ከማምጣት ባለፈ የሀገርን ኢኮኖሚ በጽኑ አለት ላይ መገንባት ይቻላል ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል።

የገበያ ዋጋ መናር ችግርን ለአብነት አዊ ብሔረሰብ አስተዳደርን አነሳን እንጅ የክልሉ፤ አለፍ ሲልም የሀገሪቱ ሆኗል፡፡ በጉዳዩ የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት አማረ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከ560 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች እንዲሁም ከስምንት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች በማህበራቱ በኩል ወደ ገበያ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት የማህበራቱ ዋነኛ ተልዕኮ የአባላቱን እና የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህም ሲባል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ የዕለት ተዕለት ፍጆታቸውን እንዲያገኙ ሌት ተቀን እየተሠራ ይገኛል። ማህበራቱ የተቋቋሙበትን የሕዝብ አለኝታነት መንፈስ ወደ ጎን በመተው ልክ እንደ ተራ ነጋዴ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ የሚስገበገቡ፣ ምርት በመደበቅ እና በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ኮሚሽነር ጌትነት በግልጽ አስምረውበታል።

“ከዓላማ ውጭ ዝም ብሎ ነጋዴ የሚመስል፣ አልፎ አልፎ የሚታይ ነገር አለ” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አንዳንዶቹ ማህበራት አባላትን ከማገልገል ይልቅ ገበያን በማዛባት የችግሩ አካል ሲሆኑ መገኘታቸውን ጠቁመዋል። ይህ ድርጊት ማህበራቱ ከተመሰረቱበት “ለሕዝብ መቆም” ከሚለው መርህ ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው።አሁን ላይ ጥብቅ የቁጥጥር እና የማስተካከያ ርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ነው ያሉት። ምርት ደብቀው በተገኙ ማህበራት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ አጠቃላይ አሠራሩን የሚያዘምኑ እና ክፍተቶችን የሚደፍኑ መመሪያዎች እየተሻሻሉ መሆኑም  ተገልጿል።

በተለይም ሸማች ማህበራት ዋነኛ ተልዕኳቸው ገበያን ማረጋጋት መሆኑን ተገንዝበው በቂ ምርት በማቅረብ እና ከነጋዴዉ በተሻለ (በቅናሽ) ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው። በተጨማሪም የማህበራቱ ሠራተኞች በሙሉ አቅማቸው እና በሥራ ሰዓታቸው ተገኝተው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የአሠራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

መረጃ

 

 

የህብረት ሥራ ማኅበራት ዋና ዋና ሚናዎች ፦

  • የገበያ ትስስር መፍጠር እና ደላላን (ህገ – ወጥ አዘዋዋሪን) ማስቀረት
  • የግብዓት አቅርቦት እና ምርታማነትን ማሳደግ
  • የፋይናንስ አቅርቦት (የቁጠባና ብድር አገልግሎት)
  • የሸማቾችን መብት ማስጠበቅ እና የኑሮ ውድነትን ማቃለል
  • የሥራ ዕድል ፈጠራ
  • ማህበራዊ ትስስርን እና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር  የሚሉት    ይገኙበታል፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር  የነሐሴ  25  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here