የዓለም ስጋት ወይስ በረከት?

0
13

ዘመኑ አ.አ.አ 1945 ነው፤ ይህ ወቅት ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ የማይታሰብ የሚመስለው ነገር እውን የሆነበት፣ አንዲት ቦምብ የአንድን ከተማ ሙሉ ነገር በቅጽበት እንዳልነበር ያደረገበት ክስተት ነው። ይህ የተከናወነው ደግሞ ጃፓን ውስጥ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ነው።

ይህ ክስተት ዓለም ኒውክሌር ማለት የጦርነት መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሕልውናን የሚፈትን ኃይል መሆኑን የተረዳችበት ነው።

ዛሬ ግን ኒውክሌር የሚለው ቃል በቦምብ ብቻ አይገለጽም። የኒውክሌር ኃይል በኤሌክትሪክ ምርት፣ በሕክምና፣ በምርምርና በኢንዱስትሪ ውስጥ ሰፊ ጥቅም አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ኒውክሌር መሣሪያ ያላቸው ሀገራት የደህንነትና የዓለም ፖለቲካ ሚዛንን በእጃቸው ለማቆየት እየተወዳደሩ ናቸው።

ኒውክሌር ምንድን ነው?

ኒውክሌር  ማለት በአቶም ማዕከል ወይም ኒውክለስ ውስጥ የሚገኝ ኃይል ወይም ከዚሁ ማዕከል መከፈልና መጋጠም የሚመነጭ እጅግ ከፍተኛ የኃይል መጠን ነው። ቦምቡ ዩራኒየም የተባለ ማዕድንን በመጠቀም ንጹህ እና ከፍተኛ ኃይል ይፈጥራል።

በሌላ በኩል የኒውክሌር መሣሪያ (ቦምብ)  ደግሞ በውስጡ ባለው የአቶም መሰንጠቅ ወይም መጋጠም  ሂደት አማካኝነት ከፍተኛ ፍንዳታና ውድመት የሚያስከትል የጦር መሣሪያ ነው። ስለዚህ የኒውክሌር ቦንብ ማለት የአንድን አቶም ኒውኩለስ በማጣበቅ ወይም በመለያየት የሚፈጠር ቦንብ ነው።

የኒውክሌር ታሪክ

በዓለማችን ኃያላን ሀገራት መካከል የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ፉክክር የተጀመረው በ1930 ዓ.ም ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ኬይዘር ዊሊያም ተቋም ውስጥ ኦቶማን ሆን እና ዶር ፈሪትዝ ሰቲርስማን የተባሉ ሳይንቲስቶች የአቶምን ቅንጣት በተሳካ ሁኔታ መነጠል በመቻላቸው ነው፡፡

ጥቂት ቆይቶ ሊሴ ሜይትነር እና ኦቶ ሃን የአተም ቅንጣትን የመፈርከስ የተሳካ ሥራ ወደ ኒውክሌር ማብላላት ደረጃ ማደጉን ይፋ አደረጉ። እንደ ሂስትሪ ዶት ኮም መረጃ በአቶሚክ ጉዳይ ላይ የሚሠሩት ታላላቅ አዕምሮዎች አይሁዶች እና ጀርመኖች ነበሩ። በወቅቱ የጀርመኑ መሪ የሂትለር ፀረ ሴማዊነት አመለካከት ጀርመን ውስጥ የነበሩትን እነዚህን ብሩህ አዕምሮዎች ገፍቶ ወደ አሜሪካ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል።

ተሳዳጅ ሳይንቲስቶቹም ጉዳዩን አውሮፓን በዓይነ ቁራኛ ይከታተል ለነበረው የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም አሳወቁት። የዚህ ዕውቀት ባለቤት በመሆኗ ጀርመን የኒውክሌር ቦምብ በመሥራት የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች የሚል ፍራቻ በመላው ዓለም ነግሶ ነበር።

ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን ከእነዚህ ስደተኞች አንዱ ነበርና የዚህን ግኝት ሚና ሙሉ በሙሉ ያውቅ ነበር:: ምክንያቱም የአቶም ቅንጣት ያለውን ምስጢራዊ አቅም ለዘመናዊው ዓለም የገለጠ የመጀመሪያው ሰው እርሱ ነበርና። እናም እርሱ ነበር ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጉዳዩን ያሳወቀው። አሜሪካ ከጀርመን ቀድማ ቦምቡን መሥራት እንዳለባት በፅኑ አሳስቦ እንደነበር የመረጃ ምንጩ ያወሳል።

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሩዝቬልት ቦምቡን በቀዳሚነት ለመገንባት እሽቅድምድሙን ጀመሩት። በማንሃተን ደሴት ውስጥ በከፍተኛ ምስጢር ቦምቡ እንዲገነባም ትዕዛዝ ሰጡ። በሜጀር ጄኔራል ሌስሊ ግሩቭስ የሚመራ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ታይቶ የማይታወቅ ሳይንሳዊ ምርምር ‘የማንሃታን ፕሮጀክት’ን ቦምቡን የመገንባት ሥራውን በከፍተኛ ምስጢር እንዲያከናውን ኃላፊነት ሰጡ።

አድቫንስድ ስተዲ ኤንድ ስፔስ የተሰኘው ተቋም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ከአሜሪካ ጋር ፉክክር ውስጥ የገባችው የመጀመሪያዋ ሀገር ጀርመን በቀዩ ጦር በግንቦት ወር 1937 ዓ.ም ተሸነፈች፤ በዚህም ምክንያት ሁሉም የኒውክሌር ማብላያ ተቋሞቿ እንዲወድሙ ሆነ፡፡

በዚሁ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ፉክክሩን በመጀመሪያው ሂደት በውጥን አስቀረው። ቢሆንም ከአድማስ ባሻገር አዲስ ጠላት በመሆን ኮሚኒስቷ ሶቪየት ሕብረት (የአሁኗ ሩሲያ) ብቅ አለች። የኮሚኒዝም መስፋፋት የፈጠረው ፍርሃት የአቶሚክ ቦምብ ግንባታውን በአስደንጋጭ ፍጥነት አፋፋመው።

ከጀርመን መፈረካከስ በኋላ ኮሚኒስቷ ሶቪየት ሕብረት አሜሪካን እና የምዕራቡን ዓለም ታላቅ ተገዳዳሪ ኃይል ሆነች። የምዕራባውያን አጋሮች አንዳች የኮሚኒዝምን ጉዞ የሚያስቆም የማያዳግም የጦር መሣሪያ መሠራት እንደሚገባ ተገንዝበው እንደነበር ድረ ገጹ አስታውሷል።

ከመነሻው ለጀርመን ታስቦ የተነደፈው እና በጃፓን ላይ የተሞከረው የኒውክሌር መሣሪያ በኋላ ለኮሚኒስቷ ሶቪየት ሕብረት ጥቅም ላይ ዋለ። አሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረትመረ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በርዕዮት ዓለም ልዩነት በባላንጣነት መተያየት መጀመራቸው ወደ ጦር መሣሪያ ፉክክር አስገብቷቸዋል።

የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጅማሮ

የካፒታሊዝም እና ኮሚኒዩዝም መራኮት የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት አስከትሎ ኮሪያን ወደ ካፒታሊስት ደቡብ ኮሪያና ኮሚኒስት ሰሜን ኮሪያነት ለሁለት ሰንጥቋታል። ይህም ሁለቱ ኮሪያዎች አሁንም ድረስ በባላንጣነት እንዲተያዩ እንዳደረጋቸው ሂስትሪ ዶት ኮም አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን በትኩረት የተንቀሳቀሰችውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ነው መረጃው የሚያስገነዝበው፤ ከኃያላኑ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር የመታጠቅ ጉዞ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የተጀመረ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዙሪያዋ ካለው ዓለም ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ሰሜን ኮሪያ ለደህንነቷ ዋስትና ኒውክሌር ላይ ዐይኗን እንድትጥል ምክንያት ሆኗል።

ሶቪየት ሕብረት የሰሜን ኮሪያ ተመራማሪዎችን እና ኢንጂነሮችን በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ላይ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረጓ የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ዕድገት መነሻ እንደሆነም ይነገራል። ኮሚኒስት ሰሜን ኮሪያ ከሶቪየት ሕብረት እ.አ.አ በ1950ዎቹ መጀመሪያ አንድ የወዳጅነት ስምምነት አደረጉ። ስምምነቱ ለሰሜን ኮሪያ መሠረታዊ የኒውክሌር ስልጠናን እና ቴክኖሎጂን የሚያቀርብ ነበር።

ስምምነቱን ተከትሎም ሶቪየት ሕብረት መሠረታዊ የኒውክሌር ቁሶችን ለሰሜን ኮሪያ መሸጥ እና ማቅረቧን ቀጠለች። እ.አ.አ በ1950ዎቹ መጨረሻ ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር የማበልጸግ ሙከራዋን በዮንግብዮን ማዕከል ጀመረች። እ.አ.አ በ1960 ዎቹ እና 70ዎቹ ከሶቪየት ሕብረት እና ቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እገዛን ብትጠይቅም ኃያላኑ ጥያቄዋን ውድቅ አደረጉባት። ይሁን እንጂ የኒውክሌር ጉዞዋን አላስተጓጎለውም።

እ.አ.አ በ1985 ሰሜን ኮሪያ ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ተስማሚ የሆነ ነዳጅን በማምረት ዩራኒየምን ለማጣራት የሚያስችል ፋብሪካን በዮንግቢዮን ገንብታ አጠናቀቀች። በዚያው ዓመት ኒውክሌርን ያለ ማስፋፋት ስምምነትን መቀበሏን አስታወቀች።

ሰሜን ኮሪያ ግን ሁለተኛውን የኒውክሌር ማብላያ ግንባታዋን ቀጠለች። ኒውክሌርን ያለማስፋፋት ስምምነቱን በፈረመች በአራት ዓመቱ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር መሳሪያ ዕቅድ እንዳላት ጠንካራ የሳታላይት መረጃ ምስል አለኝ ስትል ከሰሰቻት። በሰሜን ኮሪያ ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ዕቅድ አላት የሚሉ ወቀሳዎችም ተጀመሩ።

ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ዕቅዷን ለማሳደግ የሶቪየት ተመራማሪዎችን ለመቅጠር ብታስብም ዕቅዱን የሰማችው ሶቪየት ሕብረት የራሷን ተመራማሪዎች አሰረች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሜን ኮሪያ ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጄንሲ ሪፖርት አቀረበች። ይሁንና ሪፖርቷ ከዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጄንሲ ትንተና ጋር የሚቃረን ሆኖ ተገኘ። ይህን ተከትሎም ሰሜን ኮሪያ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ተቆጣጣሪዎች የኒውክሌር ማብላያ ቁስ ማጠራቀሚያዎችን እንዳያገኙ በመከልከል ኒውክሌር ካለማስፋፋት ስምምነቱ መውጣቷን እ.አ.አ በ1985 ይፋ አደረገች።

በዚያው ዓመት የመጀመሪያውን ኖዶንግ-1 የተሰኘ የሚሳኤል ሙከራዋን አደረገች። በጃፓን ባሕር ብዮይ ላይ ዒላማውን ያደረገው ሙከራው የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎች ለኢራን እንዲሸጡ በር ከፍቷል። በመጀመሪያው የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ሰንግ የተጀመረው የኒውክሌር ጉዞ ከህልፈታቸው በኋላም በልጃቸው ኪም ጆንግ ኡን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አድቫንስድ ስተዲ ኤንድ ስፔስ የተሰኘው ተቋም በድረ ገጹ እንዳስነበበው አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የመሬት ስር ኒውክሌር የማብላላት ተግባር በሳታላይት መረጃዎች በመታገዝ ከማጋለጥ ባለፈ ጠንከር ያሉ ማዕቀቦችን ጥላለች፤ ሰሜን ኮሪያ ግን አሻፈረኝ በማለት አውዳሚ የሆነው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት ጉዞዋን ቀጥላለች። በግልጽም ሙከራዎችን ታደርጋለች። አሁን ላይ እስከ 50 የሚደርሱ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንዳሏትም ይነገራል።

የኒውክሌር ሙከራዎች ስጋት

በዓለም ዙሪያ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የተካሄዱ የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራዎች ቢያንስ አራት ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡ ኖርዌይ የሰዎች እርዳታ ኤጄንሲ (NPA) እ.አ.አ በ2022 ባወጣው ሪፖርት፣ የኒውክሌር ሙከራዎች ያስከተሉት ጠባሳ ዛሬም ድረስ በሰው ልጅና በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ መሆኑን አጋልጧል።

እ.አ.አ ከ1945 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙሪያ ከሁለት ሺህ 400 በላይ የኒውክሌር መሣሪያዎች ተሞክረዋል (ተፈትነዋል)። ይህም በሰውነት ውስጥ የዘረመል (ዲ ኤን ኤ) ለውጥን በማምጣት ለካንሰር፣ ለልብ ሕመም እና ለተለያዩ በዘር ለሚተላለፉ የጤና ዕክሎች ምክንያት ሆኗል።

እ.ኤ.አ እስከ 1980 ድረስ የተደረጉ የከባቢ አየር ሙከራዎች ብቻ ለተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን የካንሰር ሞቶች ምክንያት እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት የኒውክሌር መሣሪያ አላቸው ተብለው የሚታወቁት ዘጠኝ አገራት (ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ፓኪስታን፣ ሕንድ፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ) ናቸው፤ ይን እንጂ እ.አ.አ ከ1990ዎቹ ወዲህ የኒውክሌር ሙከራ የምታደርገው ሰሜን ኮሪያ ብቻ መሆኗን አድቫንስድ ስተዲ ኤንድ ስፔስ አስታውቋል።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 25   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here