አብዛኞቹ ሰዎች ስኬትን የሚያሳድዱት በአንድ ጀግንነት የተሞላ ዝላይ ብቻ ድል ሊደረግ እንደተዘጋጀ ተራራ አድርገው ነው። በአንድ ጀምበር ሁሉንም ነገር መለወጥ እንዳለባቸው ያስባሉ። ንጋት 11:00 ሰዓት ላይ መንቃት፣ በቀን ውስጥ አምስት አዳዲስ ልማዶችን መገንባት፣ ንግድ መጀመር፣ 10 መጻሕፍትን ማንበብ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ማቆም፣ እንዲሁም የሰውነት ቅርፅን ማስተካከል ብለው ያቅዳሉ።
ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወጥመድ ነው፤ ሰዎችን ያደክማል። ለውጥም የማይቻል እንዲመስል ያደርጋል። ምክንያቱም ሕይወትን ሊለውጠው የሚችለው ግዙፍ እና አስደናቂ እርምጃ ብቻ ነው ብለን ስናምን ጥቃቅን የዕለት ተዕለት ጥረቶች ዋጋ ቢስ እንደሆኑ እናስባለን። ይህ ደግሞ ከእውነት የራቀ ነው።
ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የሚገለብጥ አንድ የጃፓናውያን ፍልስፍና አለ። ይህ ፍልስፍና ታላቅነት የሚገኘው በድንገተኛና ከፍተኛ ግፊት ሳይሆን በዝግታና ቋሚ በሆነ ዕድገት ውስጥ እንደሆነ ያስተምራል። በጣም ጥቃቅንና የማይታይ በሚመስል መጠን እንኳን ራሳችንን በየቀኑ ካሻሻልን ሙሉ ሕይወታችን መለወጥ እንደሚችል ያሳያል።
ይህ ፍልስፍና “ካይዘን” ይባላል። ትርጉሙም ለውጥ ለመልካም ነገር ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ከአንድ ዘዴ በላይ የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው፤ ፀጥ ያለ አብዮት ነው። በማነሳሳት (Motivation)፣ በኃይል ወይም በፍጥነት ላይ ሳይሆን በጽናት፣ በቀላልነት እና በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሠረተ የሕይወት አኗኗር ነው።
ይህ አካሄድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓንን መልሶ ለመገንባት ረድቷል። እንደ ቶዮታ ያሉ የተቸገሩ ኩባንያዎችን ወደ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ቀይሯል። በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የኦሊምፒክ አሰልጣኞች የዓለም ሻምፒዮናዎችን ለመገንባት፣ አርቲስቶች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እና ፈላስፎች ይጠቀሙበታል።
ካይዘን ፈጣን ውጤትን ቃል አይገባም፤ ይልቁንም ዘላቂና እውነተኛ ለውጥን ያረጋግጣል። በአቋራጭ መንገድና በአንድ ጀምበር በሚመጣ ስኬት በተጠመደ ዓለም ውስጥ ይህን ጽንሰ-ሀሳብ መረዳት ከባድ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ካይዘን ማለት ማንም ሰው በማያየን ጊዜ በምናደርገው ነገር ላይ ያተኩራል። ምንም ካለመሥራት ይልቅ አንዲት ፑሽ-አፕ ብቻ ለመሥራት ስንወስን፤ አንድ ገጽ ብቻ ስናነብ፤ አንዱን አሉታዊ አስተሳሰብ በአዎንታዊ ስንተካ፤ በፀጥታ ውስጥ ተጨማሪ አንዲት ደቂቃ ስናሳልፍ ሕጉን ተግባራዊ እያደረግነው ነው።
እነዚህ ጥቃቅን ድርጊቶች በጊዜ ሂደት ሲደጋገሙ ዝም ብለው አይደመሩም፤ ይባዛሉ፣ ያድጋሉ፣ ማንነታችንንም ይቀርጹታል።
የካይዘን እውነተኛ ኃይል ይሄው ነው፦ የግል ዕድገትን ከሩጫ ወደ ሥርዓት፣ ከከባድ ሸክም ወደ የተረጋጋ ምት ይቀይረዋል።
ካይዘን ሦስት ዋና ዋና መርሆች አሉት፦
- ቀጣይነት ያለው መሻሻል፦ ፈጽሞ ባለህበት አለመርካት ነው። ይህ ማለት ጭንቀት ውስጥ መግባት ሳይሆን ሁልጊዜ የተሻለ፣ ንጹህና የተረጋጋ መንገድ መፈለግ ነው።
- ሁሉም ሰው ኃላፊ ነው፦ ማሻሻያ ለባለሙያዎች ብቻ የተተወ አይደለም፤ በግል ሕይወትህም ራስህን ለማሻሻል የማንንም ፈቃድ አትፈልግም።
- ምንም ዓይነት እርምጃ በጣም ትንሽ አይደለም፦ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው በማይቋረጥ ፍጥነት እንጂ በአንድ ጀምበር በሚደረግ ከባድ ድርጊት አይደለም።
አብዛኞቹ ሰዎች ለመለወጥ የሚሳናቸው ሰነፍ ወይም ደካማ ስለሆኑ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከልክ በላይ ውጤት ስለሚጠብቁ ነው። በየአዲሱ ዓመት በሚገቡ ቃል ኪዳኖች የሚሆነው ይሄው ነው።
ሰዎች መስከረም ወር ላይ “በየቀኑ ጂም እሄዳለሁ፣ ስኳር እተዋለሁ፣ በቀን ለአንድ ሰዓት አሰላስላለሁ፣ መጽሐፍ እጽፋለሁ” ብለው ይነሳሉ። ለጥቂት ቀናት ተነሳሽነቱ ከፍተኛ ቢሆንም የዕለት ተዕለት ኑሮ ጫና ሲመጣ አንዱን ልማድ ያቋርጣሉ፤ ከዚያም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ሙሉ በሙሉ ይተዉታል።
ካይዘን የተለየ አማራጭ ያቀርባል። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ከመሞከር ይልቅ በየቀኑ አንዲት ነገር ብቻ ከትናንቱ በ1% አሻሽል ይላል። ይህ በማንነት ላይ የተመሠረተ ለውጥ ይባላል።
“ማራቶን መሮጥ እፈልጋለሁ” ከማለት ይልቅ “እኔ አጭር ርቀትም ቢሆን በየቀኑ የምሮጥ ሰው ነኝ” ማለት። “50 መጻሕፍት ማንበብ እፈልጋለሁ” ከማለት ይልቅ “እኔ በቀን አንድ ገጽ የማነብ ሰው ነኝ” ማለት።
የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የባህሪ ሳይንቲስት የሆኑት ቢ.ጄ. ፎግ እንደሚሉት አዳዲስ ልማዶችን በጣም ጥቃቅን አድርጎ መጀመር ያስፈልጋል (ለምሳሌ፦ አንዲት ፑሽ-አፕ መሥራት፣ አንድ ጥርስ ብቻ መፋቅ፣ የጽሑፍ ሰነድ መክፈት ብቻ)። ምክንያቱም ከሁሉ የከበደው ነገር መጀመር ነው፤ አንዴ እንቅስቃሴ ከጀመርክ ግስጋሴው ይቀጥላል ይላሉ።
የቀርከሃ ዘር ከተዘራ በኋላ በመጀመሪያው፣ በሁለተኛው፣ በሦስተኛውና በአራተኛው ዓመት ምንም የሚታይ ለውጥ የለም፤ ከመሬት በታች ጠንካራ ሥር ሲዘረጋ ይቆያል። በአምስተኛው ዓመት ግን በስድስት ሳምንታት ውስጥ እስከ 90 ጫማ (27 ሜትር) ይረዝማል፤ ያድጋል። ሰዎች በአንድ ጀምበር የበቀለ ይመስላቸዋል፤ እውነታው ግን ለዓመታት ሳይታይ ሲያድግ ቆይቷል። ልማዶችም ልክ እንደዚሁ ይሠራሉ።
የ1% ሕግ ቀላል ነው፦ በየቀኑ በ1% ብቻ የተሻልክ ከሆንክ፣ ያ ጥቃቅን ለውጥ በጊዜ ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ ይባዛል የሚል ነው። በየቀኑ በ1% ብትሻሻል፣ በአንድ ዓመት መጨረሻ ላይ 37 እጥፍ የተሻልክ ትሆናለህ የሚል ነው።
በቀን 1 ገጽ ማንበብ በዓመት ከ350 ገጽ በላይ (ሙሉ 1 ወይም 2 መጽሐፍት) ነው። በቀን 10 ደቂቃ በእግር መጓዝ በዓመት ከ60 ሰዓታት በላይ ንቁ እንቅስቃሴ ነው።
የዚህ ሕግ አሠራር ቀላል ነው። መገምገም → ማሻሻል → መድገም።
ካይዘን የንግድ ስልት ብቻ ሳይሆን ጥልቅ መንፈሳዊ መሠረት ያለው ፍልስፍና ነው። በዜን ቡድሂዝም አስተምህሮ መሠረት እርካታ የሚገኘው ውጤትን በማሳደድ ሳይሆን አሁን ባለንበት ቅጽበት ሙሉ በሙሉ በመገኘት ውስጥ ነው።
ካይዘን አንድ ጊዜ ተጠቅመን የምንረሳው መሣሪያ ሳይሆን የሕይወት ዘይቤ ነው። ሕይወታችንን በአንድ ጊዜ ለመለወጥ መሮጥ አያስፈልግም፤ ዛሬ የምንኖረውን ዕለት ብቻ እንለውጥ። ዕለቱ ደግሞ ሕይወታችንን ይለውጠዋል።
በጥቃቅኑ እንጀምር፣ በጽናት እንቀጥል፣ በሂደቱም እንመን። ይሄው ነው የካይዘን መንገድ! ይሄው ነው “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” የሚባለው የሀገራችን ጥበብ። ይሄው ነው የ1 በመቶ ዕድገት ሕግ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


