የኦሞ ወንዝ የታችኛው ሸለቆ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ነው የሚገኘው፡፡ ሸለቆው ቀደምት የሰው ልጅ ቅሪተ አካላት መገኛ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ ታዋቂነትን አግኝቷል፡፡ ግኝቱ ለሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ጥናት ጠቀሜታው የጐላ መሆኑም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተረጋግጧል፡፡
የሸለቆው ስፋት 165 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለከቷል፡፡ በቀጣናው ለዘመናት የተከማቸው ደለል በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ የቅሪት አካላት የጥናት ማእከል ሆኗል፤ የኮንስ እና ፌጄጅ ፓሊዮንቶሎጂካል የምርምር ቦታዎችንም አካቶ ይዟል፡፡ በምርምር ጣቢያው በአፍሪካ የ“ሆሞሳፒያን” የሰው ልጅ ቀደምት አመጣጥን የሚያመላክቱ ቅሪት አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኦሞ የታችኛው ሸለቆ ጥንታዊ የዝግመተ ለውጥ ሂደትን የሚያሳዩ፣ ከአንድ ሚሊዬን እስከ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዬን ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቅሪት አካል መገኛ፤ ለተገኙትም በመለኪያነት የሚያገለግል መስፈሪያ መሆኑን ነው ድረ ገፆች ያስነበቡት፡፡
በኦሞ የታችኛው ሸለቆ ቦዲ፣ ዳሰነች፣ ካራ፣ ሙጉጂ ፣ሙርሲ፣ ኒያንጋቶም እና ሀመር የተሰኙ ጐሣዎች ይኖራሉ፡፡ የነዋሪዎቹ ቁጥር ሁለት መቶ ሺህ ይሆናል ተብሎም ተገምቷል- በድረ ገጹ፡፡
የቀደምት ኗሪዎቹ መተዳደሪያ ዋነኛው ከብት ርባታ ሲሆን የእንስሳቱን ደም እና ወተት ለምግብነት በማዋልም ይታወቃሉ፡፡ በቀጣናው ከተገኙ ቀደምት የሰው ዘር ቅሪት ሉሲ እና አርዲ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ወደ ቀጣናው ለመጓጓዝ አነስተኛ የግል አውሮኘላን አሊያም በጥርጊያ መንገድ በተሽከርካሪ መጓዝን ግድ ይላል፡፡
በኦሞ የታችኛው ሸለቆ እንደ ጊቤ ቁጥር ሦስት ያሉ ግዙፍ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆናቸው እና መሬቱ ለሰፋፊ እርሻ ልማት በሊዝ መሰጠቱ በህልውናው ጥላ ማጥላቱ ነው የተሰመረበት፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ደብሊው ኤች ሲ ዩኔስኮ ዶት ኦርግ፤ ሎካልሚትራቭል ፣አፍሪካን ወርልድ ሄሪቴጅ ሳይት ዶት ኦርግ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


