የመኸር እርሻ ለምግብ ዋስትና!

0
3

የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ፣ የህዝቧ የዕለት ጉርስ ምንጭና የሀገራዊ ሉዓላዊነት መገለጫ ነው። በሀገራችን ከሚመረተው አጠቃላይ የሰብል ምርት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚሸፍነው የመኸር ወቅት ሲሆን፣ ይህ ወቅት የሚጠይቀው ትጋትና ዝግጅት ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ለተያዘው ግብ መሠረት ነው። መጪው የምርት ዘመን የታለመውን የላቀ ምርታማነት እውን እንዲያደርግ ከወዲሁ አጠቃላይ የግብርና ሰንሰለቱን ያማከለ የተቀናጀ ስራ መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቅ ጉዳይ ነው።

አርሶ አደሮች በመጪው ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በአግባቡ ሊያከናውኑ ይገባል። ምርታማነት በዘፈቀደ ሳይሆን በሳይንሳዊና በታቀደ አሰራር የሚገኝ የጥረት ውጤት ነው። መሬትን በተደጋጋሚ በማረስ አፈርን ማለስለስ፣ አረምን ማስወገድ፣ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም እና ለየአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዘሮችን መምረጥ ወሳኝ ተግባራት ናቸው። ከዚህ ጎን ለጎን፣ እንደ ኩታ ገጠም (ክላስተር) ያሉ የግብርና አሰራሮችን ማስፋፋት የግብዓት አጠቃቀምንና የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በሚገባ መጠቀም የምርት መጠንን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።

በክረምት ወቅት ሰብሎች የሚያስፈልጋቸውን ተገቢ እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው። ከመጠን ያለፈ የዝናብ ውሃ ሰብልን እንዳያበላሽና አፈር እንዳይሸረሸር የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን መክፈት፣ አረምን በወቅቱ ማረም እና ሰብሉ አስፈላጊውን ንጥረ-ነገር እንዲያገኝ የተመጣጠነ ማዳበሪያን በወቅቱና በመጠን መጠቀም የዕለት ተዕለት ክትትልን ይጠይቃል። ሰብል በእድገት ምዕራፉ ተገቢውን እንክብካቤ ካላገኘ በስተቀር ከፍተኛ ግብዓት የፈሰሰበት እርሻ የሚጠበቀውን ያህል ምርት ላይሰጥ ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሌላው ጉዳይ የተቀናጀ የጸረ-ተባይና የበሽታ መከላከያ መድሃኒት አጠቃቀም ነው። በሽታና ተባይ ሳይከሰት ቀድሞ መከላከል ዋነኛ መርህ ሊሆን ይገባል። በሽታ ወይም ተባይ ሲከሰት የግብርና ባለሙያዎችን (የልማት ጣቢያ ሠራተኞችን) ምክር በመከተል፣ ትክክለኛውን መድሃኒት በተገቢው መጠን፣ መንገድና ሰዓት መጠቀም ይገባል። ጸረ-ተባይ መድሃኒቶችን ያለጥንቃቄና ያለመጠን መጠቀም የአካባቢ ብክለትን ስለሚያስከትል፣ የተጠቃሚዎችን ጤና ስለሚጎዳ እንዲሁም የተባዮችን የመላመድ አቅም ስለሚጨምር ሙያዊ ጥንቃቄን መከተል ግድ ይላል።

በአማራ ክልል በመጪው የምርት ዘመን  ከአምስት ነጥብ አምስት ሄክታር በላይ ማሳ  በዘር ለመሸፈን በእቅድ ተይዟል፡፡ በዚህም ከሁለት መቶ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት  ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡ የሰብል ምርት በመሰብሰብ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን፣ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋትና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ እንደ ሀገር ትልቅ ግብ ተቀምጧል። ይህንን ሀገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ መንግስት፣ የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የግብዓት አቅራቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ተቀናጅተው መንቀሳቀስ አለባቸው። የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ያለምንም መስተጓጎል ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ማድረግ፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ማጠናከር እና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማሰራጨት ለነገ የሚባል ስራ አይደለም።

በጥቅሉ የመኸር እርሻ ስኬት የሚወሰነው በዛሬው ቅድመ ዝግጅታችን ነው። አርሶ አደሩ ሳይንሳዊ የአስተራረስ ዘዴዎችን ተከትሎ፣ የሰብል እንክብካቤን አጠናክሮና ጸረ-ተባይን በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ማሳ ሲገባ፤ መንግስትና ባለድርሻ አካላት ደግሞ አስፈላጊውን ግብዓትና ድጋፍ በወቅቱ ሲያቀርቡ የምግብ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል። ዛሬ በማሳችን ላይ በምናደርጔ ጥረትና ትጋት የምናመርተው ምርት ነገ ሀገራችንን በራሷ አቅም የምትተማመን እና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ እንድትሆን ያደርጋታል።

በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here