ድባቴ “ድኘሬሽን” ያለባቸው ሰዎች በ “ሂፓካምፓስ”የትውስታ እና አካባቢያው ስሜት ምላሽ ሰጪ የአንጐል ክፍል አዲስ የነርቭ ህዋሳት መመረትን እንደሚገታ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኢርቪንግ የህክምና ማዕከል በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የነርቭ ህዋሳት በጽንስ ወቅት ህጻናት ከመወለዳቸው በፊት ነው የሚመረቱት፤ ከተወለዱ በኋላ በጐልማሳነት አዲስ የሚመረቱት ህዋሳት ግን ድብርትን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ህዋሳት እንዳይመረቱ የሚያደርገውን ሞሎኪውላር ሂደትም ለይተው ማወቃቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ ይህም ለችግሩ መድሃኒት ለመፈለግ በር ከፋችነቱን አስምረውበታል፡፡
ቀደም ብሎ በ “ሂፓካምፓስ” ውስጥ “ድኘሬሽን” ወይም ድብርት የነርቭ አስተላላፊ የሆነው የ“ሴሬቶኒን” ዕጥረት የሚያስከትለው በሽታ ነው ተብሎ ይታመን እንደነበር በተቋሙ የዓዕምሮ ኘሮፌሰሯ ማውራ ዱፓንት አስረድተዋል፡፡ የአዲስ ነርቭ ህዋሳት አለመፈጠር የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ከተለዋዋጭ አካባቢያቸው ጋር መላመድ እንደሚቸግራቸውም ነው የጠቆሙት፡፡
ኘሮፌሰር ማውራ ዱፓንት የድባቴ ወይም “ዲኘሬሽን” ዓይነቶች በርካታ መሆናቸውን የተመራማሪዎች ቡድን መሪ ማጠቃለያ ማመላከቱን አስምረውበታል፡፡
የችግሩን መገኛ ቦታ ሳይሆን የህዋሳት መለያን መሰረት በማድረግ የድባቴ ዓይነቶቹን በመለያየት መድሃኒት ማግኘት እንደሚያስችልም ነው ያረጋገጡት- ኘሮፌሰሯ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


