በዓላት – የልብ ድልድዮች

0
561

አንዳንድ ቀናት ከቀናት ይለያሉ፤ ሰዓቱን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም ያቀራርባሉ። በዓልም ከእነዚህ ልዩ ወቅቶች አንዱ ነው። የተራራቁ ወዳጆችን ያገናኛል፣ የተረሱ ዝምድናዎችን ያድሳል፣ በአንድ ማዕድ ዙሪያም ልቦችን ያቀራርባል። በዓል ስለዚህ የምግብና የደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ የመተሳሰብ፣ ይቅር የመባባል፣ ፍቅርን የማደስና የሰዎችን ማኅበራዊ ትስስር የማጠናከር ዕድል ነው።

በዓላት በሕይወታችን ውስጥ የሚጫወቱት ማኅበራዊ ሚና ምንድነው? በዓላት ሲታሰቡ ከመደበኛው የህይወት ሂደት በተለዬ የምናደርጋቸው በርካታ ትዝታዎች ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ፡፡ ትውስታዎቹም እንደ ቦታው፣ እንደ ጊዜው ሁኔታው የተለያዩ ስሜቶችን ነው የሚፈጥሩት፡፡

ወቅቱ ደግሞ አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ የምንቀበልበት ነው፤ ወ/ሮ አሰፉ ፍስሃ ደግሞ በበዓል ወቅት ልዩ ትዝታ ካላቸው መካከል አብነት ናቸው፡፡ የበዓል ወቅት ትዝታቸውንም አጋርተውናል፡፡

ወ/ሮ አሰፉ እንደሚገልፁት የበዓል ትልቁ ትዝታ ከቤተሰብ እና ጎረቤት ጋር ማሳለፉ ነው፡፡

በተለይም አዲስ ዓመት እና ፋሲካ ሲሆን በቤት ውስጥ የሚደረገው ዝግጅት ከጎረቤት እና በቅርብም በሩቅም ያለው ቤተሰብ ተሰብስቦ እርድ የሚፈፅሙበት ነው፡፡ በሌላ አካባቢ ያሉ ልጆች ሁሉ ለበዓሉ ተሰባስበው ስለሚመጡ በናፍቆት ነው የሚጠብቁት፡፡

የበዓል ሰሞን ታዲያ ሽር ጉዱ እና የበዓል ማድመቂያ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ የበዓሉ ዕለት ሁሉም ከያለበት ተሰባስቦ የልብ ወግን በማውጋት፣ ከድግሱም በመጋራት በድምቀት ያከብራሉ፡፡ ድግሱን ሲጋሩ ደግሞ “እንዲሁ አይደለም፤ እንደ ወግ ባሕላችን ነው፡፡ መስተንግዶው ከትልቁ ሰው ይጀመራል፤ በጠዋት ዕርድ ሲፈፀም እንኳን የዕድሜ ባለጸጋው መርቆ ነው፡፡ ከዚያም ቡና መጠራራት እና በናፍቆት መጠያየቁ ይቀጥላል” ሲሉ ነው ትዝታቸውን ያካፈሉን፡፡

አሁንም ድረስ የበዓልን ድባብ በናፍቆት እንደሚጠብቁት የነገሩን ወ/ሮ አሰፉ፣ ከቤተሰብ ባለፈ ከጎረቤት ጋር በመጠራራት ማዕድ እና የበዓል ዝግጅቶችን በመጋራት ማሕበራዊ ትስስራቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው ያነሱት፡፡

በአሁናዊ የበዓል አከባበር ግን ቅሬታ እንዳለባቸው ወ/ሮ አሰፉ በትካዜ ውስጥ ሆነው ይናገራሉ፤ ምክንያታቸው ደግሞ ከላይ ያነሷቸው የበዓል ወቅት ትዝታዎች ትዝታ ብቻ እየሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት እየተረሱ በመሆኑ ነው፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አሰፉ የሁለት ልጆች እናት ናቸው፤ አንደኛው ልጃቸው ትዳር መሥርቶ ኑሮውንም በሐዋሳ ከተማ አድርጓል፡፡ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጎረቤትም ጋር ቡና መጠራራቱ፣ ልጆችም መጥተው ከቤተሰብ ጋር በዓልን ማሳለፍ ትተውታል” የሚሉት ወ/ሮ አሰፉ ልጃቸው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለበዓል እንዳልመጣ ተናግረዋል፡፡ በዓልን በጋራ የማሳለፍ ድባቡ ከድሮው በጣም መቀዛቀዙን አንስተዋል፡፡

መስፍን ፈቃደ (ዶ/ር)  በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት (ፎክሎር) መምህር፣ ተመራማሪና ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፤ እንደ እርሳቸው ገለጻ በዓላት ሲባሉ የቀን መቁጠሪያ ምልክቶች ብቻ አይደሉም። በዓላት በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የማሕበረሰቡን ውህደት የሚያጠናክሩ ታላላቅ ማሕበራዊ ዕሴቶች ናቸው። ይህም ሲባል በዓላት ማሕበረሰቡ እንዲዋደድ፣ እንዲተሳሰር እና አንድ ማሕበራዊ ዕሴት እንዲገነባ የሚያደርጉ መድረኮች በመሆናቸው ነው።

በዓላት በዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ የተራራቁ ሰዎችን፣ ዘመድ አዝማዶችን እና ወዳጆችን በአንድ ማዕድ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው፤ በሥራና በተለያዩ ማሕበራዊ ምክንያቶች ተራርቀው የቆዩ ሰዎች በዓላትን መሠረት በማድረግ ማሕበራዊ ትስስራቸውን ያጠናክራሉ።

ባሕላዊና ታሪካዊ ዕሴትን ማስቀጠል ደግሞ ምሁሩ ያነሱት ሌላው የበዓላት አስተዋጽኦ ነው፤ ዶክተር መስፍን እንዳስገነዘቡት በዓላት የአንድን ማሕበረሰብ ማንነት፣ ዕምነት፣ ባሕልና ወግ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። ልጆች በማሕበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ወጎች እየተመለከቱ በማደጋቸው፣ ነገ እነሱ ሲተኩ ያንን ዕሴት ከቤተሰቦቻቸው ይወርሳሉ።

ሌላው የበዓላት አበርክቶ የጋራ ደስታና እፎይታ መፍጠር የምንችልባቸው መድረኮች መሆናቸው ነው፡፡ በዓላት ሲከበሩ ማሕበራዊ ጫናዎችንና ድካሞችን በመተው የማሕበረሰቡ አባላት በጋራ የሚያርፉበት እና ደስታቸውን የሚጋሩበት ትልቅ መድረክ ነው። ለአብነትም አዲስ ዓመት፣ ፋሲካ፣ መስቀል፣ መውሊድ እና ሌሎችም በዓላት ሲመጡ ሰዎች ተሰባስበው የልባቸውን እየተወያዩ የሚያሳልፉበት የጋራ መድረክን ይፈጥራሉ።

ዶ/ር መስፍን የኢትዮጵያ በዓላት ውበታቸው ያለው በቡድንና በጋራ አከባበር ላይ ስለተመሠረተ እንደሆነ ያነሳሉ። በበዓላት ወቅት የሚታየው መስተጋብር የጋራ ዝግጅት እና የደቦ ባሕል፣ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ ቤትን ማጽዳት፣ እህል ማስፈጨት እና ጠላ መጥመቅ እና ዕርድን ጨምሮ ሌሎች የበዓል ዝግጅቶች ላይ ሁሉም ይተባበራል።

“ያለ ጎረቤት በዓል አይደመቅም” የሚለው በተግባር የሚገለጥ ዘመናትን የተሸገረ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ነው፤ ይህ ደግሞ ለበዓል ከተዘጋጀው ምግብ እና መጠጥ በመለዋወጥ ደስታን መጋራት እና ያለውን ነገር መርቆ መካፈል፣ አረጋውያንን እና የታመሙ ጎረቤቶችን መጠየቅ፣ በሀገር ሽማግሌዎች መመረቅ የወቅቱ መገለጫ እና የባሕላችን ዋነኛ አካል ስለመሆኑ ነው ዶክተር መስፍን ያስገነዘቡት።

“ይህ ዓይነቱ የጋራ መስተጋብር ስነ-ልቦናዊ እና ማሕበራዊ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው” የሚሉት ምሁሩ “ይህም የብቸኝነት ስሜትን በማስወገድ ግለሰቦች ተንከባካቢና አሳቢ ወገን እንዳላቸው ሲሰማቸው የአዕምሮ እፎይታና የደህንነት ስሜት ያገኛሉ። የጋራ ሳቅ፣ ጨዋታ እና ደስታ የዕለት ተዕለት ውጥረትንና የአዕምሮ ጭንቀትን ያቃልላል” ነው ያሉት።

በዓላት ቅሬታዎችንና ቂምን ማስቀረት መቻላቸው ሌላው ተጠቃሽ ማሕበራዊ ፋይዳቸው ነው፤ በሃገራችን ባሕል በዓል ይቅርታ የሚደረግበት ወቅት በመሆኑ የተኮራረፉ ሰዎች በሽማግሌዎች አማካኝነት ይታረቃሉ፤ ይቅር ይባባላሉ፡፡ በተጨማሪም ለደካሞችና አቅም ለሌላቸው ወገኖች ዋስትና በመስጠት ማሕበራዊ ፍትሕን እና አብሮነትን ያጠናክራሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓላትን በጋራ የማክበር ባሕል ቀንሷል፤ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? በማት ለምሁሩ ጠይቀናቸዋል፡፡ ለዚህም ዶ/ር መስፍን ፈቃደ የከተሜነትን መስፋፋት በዋና ምክንያትነት ያነሳሉ፤ የከተማ ህይወት እና የሥራ ውጥረት የሰዎችን ነፃ ጊዜ በማጥበቡ ማሕበራዊ ግንኙነትን አላልቶታል። የኑሮ ሁኔታ እና የቦታ አለመመቸት ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

በአሁኑ ወቅት በርካቶች በራቸውን ዘግተው በዓላትን ከራሳቸው እና ከቤተሰብ ጋር ብቻ ታጥረው እንደሚያከብሩ በማንሳት የኢኮኖሚ ጫና እና የኑሮ ውድነትም አባባሽ ምክንያት ስለመሆኑ አክለዋል፡፡ ይህም በዓላትን ሰዎች የግል ህይወታቸው ላይ ብቻ እንዲታጠሩ በማድረግ ከሌሎች ጋር ለማክበር መሰባሰብን እንዲፈሩ አድርጓቸዋል።

“ከጊዜው መዘመን ጋር ተያይዞ የቴክኖሎጂ እና የማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ሌላው ችግር ነው” የሚሉት ዶ/ር መስፍን ሰዎች በአካል ተገናኝተው ከመጠያየቅ ይልቅ በስልክ፣ በጽሑፍ መልዕክት ወይም በማሕበራዊ ሚዲያ ብቻ በመገደባቸው መራራቅን አስፋፍቷል።

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ተሰባስበው ታዲያ የግለኝነት ባሕልን በማስፋፋት ማሕበራዊ ዕሴቶች እንዲሸረሸሩ አድርገዋል፤ ይህም የአብሮነት ስሜትን በማጥፋት ለግል ፍላጎት ብቻ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል።

ዶ/ር መስፍን እንደሚገልፁት የግለኝነት ባሕል ሲስፋፋና ማሕበራዊ ትስስር ሲላላ ሰዎች ለብቸኝነት እና ለከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት ይዳረጋሉ፣ ማሕበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ስሜትም ይጠፋል፣ የአዕምሮ ጭንቀት እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ራስን የማጥፋት አደጋንም ሊያስከትል ይችላል።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም ይህንን ነው የሚያሳዩት፤ የሩቅ ምሥራቋ ሀገር ጃፓን ደግሞ ማሳያ መሆኗን ምሁሩ ያነሳሉ፡፡ በሀገሪቱ የሚታየው የግለኝነት ስሜት የትዳር አጋር የመምረጥ ፍላጎት እንዲጠፋ፣ ትዳር ሰመሠርቱ ደግሞ ተስማምቶ አለመቀጠል እና የትውልድ መቋረጥን የመሳሰሉ ከባድ ማሕበራዊ ቀውሶችን እያስከተለ ይገኛል።

የበዓላት ፋይዳ በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ከሆነ ታዲያ የቀደም መልካም መገለጫዎች ለመመለስ ምን ማድረግ ይገባል? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር መስፍን ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ “የሚዲያና የባሕል ተቋማት የጋራ አከባበር ያላቸውን ስነ-ልቦናዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታዎች በማጉላት ግንዛቤ መፍጠር ጊዜው ሳይረፍድ  መሥራት አለባቸው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ከብክነት የጸዳ የበዓል አከባበርን ማበረታታት ይገባቸዋል፤ በዓል ማክበር ማለት ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንዳልሆነ፣ በትንሽ ነገር በፍቅርና በደስታ አብሮ መሆን እንደሚቻል ማስተማርም ያስፈልጋል።

በተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በማዋሃድ ችግረኞችን ማዕድ በማጋራት እና አረጋውያንን በመጠየቅ ትርጉም ያለው አከባበር እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

እነዚህን ዕሴቶችን ለታዳጊዎች ማስተላለፍ፣ በቤተሰብና በትምህርት ቤት ደረጃ ልጆች የበዓላትን ማሕበራዊ ፋይዳ እንዲረዱና በተግባር እንዲለማመዱ በማድረግ የቆየውን ዕሴት ለቀጣዩ ትውልድ ማቆየት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

 

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጳጉሜ 2  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here