አስፈሪው ተፅዕኖ

0
392

የሰው ልጅ የተፈጥሮ ሀብትን ለዘመናት ሲጠቀም ኖሯል፤ መሬትን ለእርሻ፣ ደኖችን ለግንባታ እና ለእንጨት፣ ወንዞችን ለመስኖ እና ለመጠጥ እና ለኃይል ምንጭነት እንዲሁም ማዕድናትን ለልማት፣ … ተጠቅሟል። ነገር ግን ይህ ጥቅም ከተፈጥሮ አቅም በላይ ሲሆን፣ ደኖች ሲመነጠሩ፣ ከባቢ አየርን የሚያሞቁ ልቀቶች ሲጨምሩና የተፈጥሮ የውሃ መንገዶች ሲደፈኑ፣ ተፈጥሮ ዝም ብላ አትቆይም።

ከባድ ዝናብ፣ የወንዞች ሙላት፣ ጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎች የአየር ንብረት ክስተቶች የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት እየተለወጠ መሆኑን ያሳያሉ። በተለይም የሰው ልጅ በሚያመነጨው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት የዓለም ሙቀት መጨመር ለከባድ ዝናብና ለሌሎች የአየር ክስተቶች ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው።

ስለዚህ የዛሬው ጥያቄ ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ምላሽ እየሰጠች ነውን? የሚለው ብቻ አይደለም፤ “የሰው ልጅ ለተፈጥሮ በሚያደርገው ጫና ላይ ራሱ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው?” የሚለውም ነው። የጎርፍ አደጋዎች እየተበራከቱ በመጡበት ዘመን፣ መፍትሔው ተፈጥሮን መውቀስ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት መፈተሽና አካሄዱን መቀየር ይሆናል።

በኔፓል ውስጥ እ.ኤ.አ ነሐሴ 26 ቀን 2026 የተከሰተው ከፍተኛ ጎርፍ ደግሞ መግቢያችን ላይ ላነሳነው ማሳያ ነው፤ በኔፓል የተከሰተው አደገኛ ጎርፍ በርካታ ሰዎችን ጠራርጎ በመውሰድ እጅግ አሳዛኝ ሰብዓዊ ኪሳራን አድርሷል፤ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን፣ የውኃ አቅርቦት መሠረተ ልማትን እና የቴሌኮሙኒኬሽን መረቦችን  እንዳልነበሩ አድርጓል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ጎርፉ በኑዋኮት፣ ዳዲንግ፣ ራስዋ፣ ጎርካ እና ታናሁን በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ 22 ሺህ አንድ መቶ ሕጻናትን ጨምሮ 65 ሺህ ያህል ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል። የተረፉ ሰዎችን የማፈላለግ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ እስካሁን ከ900 በላይ ሰዎች መሞታቸው እና ከአራት ሺህ 240 በላይ ሰዎች ደግሞ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ (እንደጠፉ) ዘግቧል።

ዘገባው እንዳመላከተው የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ስጋት አሁንም ስላለ በተጎዱት የወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወደ ከፍታ ቦታ እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ሌሎች በዓለም የተመዘገቡ የጎርፍ አደጋዎች

ፓኪስታን – እ.አ.አ በ2022

እ.ኤ.አ. በ2022 ፓኪስታን ከከፋ የጎርፍ አደጋዎች አንዱን አስተናግዳለች። የተባበሩት መንግሥታት ጎርፉ በአገሪቱ በጣም ሰፊ ጉዳት ማስከተሉን ገልጿል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል፤ ቤቶች፣ መንገዶች፣ የጤና እና የእርሻ መሠረተ ልማቶችም ተጎድተዋል።

ጀርመን እና ቤልጂየም – እ.አ.አ በ2021

በ2021 በምዕራብ አውሮፓ ከባድ ዝናብ መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያስታውሳል፤ ይህም በተለይ በጀርመን እና ቤልጂየም ከፍተኛ ጎርፍ አስከትሎ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል።

ሊቢያ – እ.አ.አ በ2023

እ.አ.አ በ2023 በሊቢያ የተከሰተው ዴንኤል የተባለው አውሎ ነፋስ ከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋ አስከትሎ በዴርና ከተማ እጅግ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት አስከትሏል። የግድቦች መፍረስ የጎርፉን አደጋ አባብሶታል።

ይህ ክስተት ከባድ ዝናብ ብቻ ሳይሆን የመሠረተ ልማት ጥገና፣ የአደጋ ማስጠንቀቂያና የከተማ ዝግጁነት እንዴት የጉዳቱን መጠን እንደሚወስኑ ያሳዬ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት፣ የዓለም ሙቀት መጠን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሆኗል፤ ይህም እጅግ አደገኛ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል።

ሪፖርቱ እንዳመላከተው የሙቀት መጠኑ ጭማሪ ቀደም ከነበረው በአንድ ነጥብ ስምንት ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ብሎ ይታያል፣ ይህም በፓሪስ ስምምነት ከተቀመጠው የሙቀት መጠን ወደ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ መገደብ ከሚለው ግብ በላይ ነው። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር እንደሚኖር አመላካች ናቸው።

ይህን ተከትሎ ታዲያ አደጋዎች እና ተፅዕኖዎች በየዓመቱ እየተባባሱ ነው። ከፍተኛ የአየር ንብረት መዛባት፣ የስነ-ምህዳር መጥፋት እና የአነስተኛ ደሴት ታዳጊ ሀገራት እና ዝቅተኛ የባሕር ዳርቻ ከተሞች መስጠም ደግሞ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች መካከል ይጠቀሳሉ፤ በሰው ጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በውኃ አቅርቦት፣ በተፈጥሮ፣ በከተሞች፣ በመሠረተ ልማት እና በኢኮኖሚዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስም ነው ሪፖርቱ ያስጠነቀቀው።

ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚኖር ያስጠነቀቀው ሪፖርቱ ችግሮቹም የበረዶ ሽፋኖች በከፍተኛ ፍጥነት መቅለጥ እና አለመረጋጋት፣ በአማዞን አካባቢ የዝናብ መዛባት እና በአትላንቲክ አካባቢ ሞቃታማ ውኃ ወደ ሰሜን እና ቀዝቃዛ ውኃ ወደ ደቡብ የሚያንቀሳቅሰው የጅረቶች ሥርዓት መስተጓጎልን ያካትታሉ፡፡ የአማዞን ደን የዓለም የአየር ንብረትን በመጠበቅ ባለው ጉልህ ሚና የዓለም ሳንባ እንደሚባል ልብ ይሏል።

ተፅዕኖዎቹም አንዳንዶቹ በድንገት ሊፈጠሩ ሲችሉ ሌሎች ደግሞ በጊዜ ሂደት ይከሰታሉ።

በፓሪሱ ስምምነት ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች መቆየት ግብ መሠረት እ.አ.አ ከ2026 ጀምሮ ያለው አጠቃላይ የልቀት መጠን ከ130 ቢሊዮን ቶን CO2 መብለጥ አይችልም። የአሁኑ የልቀት መጠን ግን በዓመት 40 ቢሊዮን ቶን ደርሷል፤ አሁንም እየጨመረ በመምጣቱ ገደቡ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ይጣሳል።

“ለዐሥርት ዓመታት ሳይንሳዊ ማስጠንቀቂያዎች እና ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ የአየር ንብረት መዛባትን ለመቀነስ ያለው ደካማ ቁርጠኝነት የልቀት ቅነሳ አላመጣም” ብለዋል በድርጅቱ የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል የሥራ ቡድን መሪ ዴብራ ሮበርትስ።

መወሰድ የሚገባቸው መፍትሔዎች

ጎርፍን ሙሉ በሙሉ ማስቆም አይቻልም። ነገር ግን አደጋውን መቀነስ ይቻላል። የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ደግሞ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ማስጠንቀቂያው በጊዜው ከደረሰ፣ ሰዎች ከአደጋው አካባቢ ሊለቁ፣ ንብረታቸውን ሊያስጠብቁ እና የሰውን ሕይወት ሊታደግ ይችላል።

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚጠቁመው የከተማ ፍሳሽና የውኃ ማስወገጃ በፈጣን ዕድገት ላይ ያሉ ከተሞች በቂ የዝናብ ውኃ ማስወገጃ ካላቸው የጎርፍ አደጋን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይቻላል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ያነሳው የ“ስፖንጅ ከተማ” የሚለውን ሐሳብ ነው፤ ለዚም ቻይና በተለያዩ ከተሞቿ እያደረገች ያለውን ውጤታማ ተሞክሮ ያነሳል፤ ዓላማውም ዝናብ ሲዘንብ ውኃውን በፍጥነት ወደ ወንዝ ከመላክ ይልቅ እንዲያስገባ፣ እንዲያከማችና በቀስታ እንዲያስወጣ ከተማዎችን ማዘጋጀት ነው።

እርጥበት አዘል መሬቶችን መጠበቅ፣ ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠት፣ የወንዝ ዳርቻዎችን መጠበቅና የተፈጥሮ የውኃ መያዣ ቦታዎችን ማስቀጠል ደግሞ የጎርፍ አደጋን ለመቆጣጠር የተዘረዘሩ መፍትሔዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ምን መማር ትችላለች?

ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የጎርፍ አደጋን ትጋፈጣለች። የከባድ ዝናብ፣ የወንዞች ሙላት፣ የከተሞች ፈጣን መስፋፋትና የውኃ ማስወገጃ ችግሮች አደጋውን ሊያባብሱ ይችላሉ።

ስለዚህ መፍትሔው ጎርፍ ከመጣ በኋላ ሰዎችን ለማዳን መሯሯጥ ብቻ ሳይሆን አደጋው ከመከሰቱ በፊት መዘጋጀት እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው።

ለዚህ ደግሞ የአደጋ ካርታዎችን ማዘጋጀት፣ በጎርፍ ሊጠቃ በሚችል ቦታ ላይ ግንባታን መቆጣጠር፣ የከተማ ፍሳሽ መስመሮችን ማሻሻል፣ የወንዞችን ዳርቻ መጠበቅ እና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን ማጠናከር ወሳኝ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደተናገሩት፣ በዚህ ክረምት የታዩት ከፍተኛ ሙቀት፣ አውዳሚ የእሳት ቃጠሎዎች እና ገዳይ ጎርፎች ወደፊት ሊከሰቱ ስለሚችሉ ከባድ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው። “ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እየጨመረ የሚገኘውን የሙቀት መጠን በተቻለ መጠን አነስተኛ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ እንዲቆይ ማድረግ አለብን። ይህ ደግሞ ከወትሮው የበለጠ ከፍተኛ የሆነ ቁርጠኝነትን እና ጥረትን ይጠይቃል” ብለዋል።

ይህ አካሄድ፣ ወደ ‘ዜሮ ልቀት’ (net-zero) በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ሚቴንን ጨምሮ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀቶችን በአፋጣኝ እና በተከታታይ በመቀነስ ከፍተኛውን የሙቀት መጠን መጨመር ይገድባል። እንዲሁም፣ በጥንቃቄ በሚተዳደር የካርቦን ዳይኦክሳይድ ማስወገድ (ከከባቢ አየር ካርቦንን በማስወገድ በደን ልማት ወይም በሌሎች መንገዶች ማከማቸት) ስልትን በመተግበር የሙቀት መጠንን ዝቅ ያደርጋል።

በተመሳሳይ ይህን አካሄድ መከተል ማሕበረሰቦች እና ኢኮኖሚዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርሱባቸው ወቅታዊ እንዲሁም ለሚጠበቁ እና ለማይጠበቁ ተፅዕኖዎች ያላቸውን ተጋላጭነት የሚቀንሱ የማላመድ እርምጃዎችን ያካትታል።

በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አደጋዎችንና ተፅዕኖዎችን ይቀንሳል፣ የማላመድ ሥራን በማቅለል ወጪን ይቀንሳል፣ የሙቀት መጠኑን የመቀነስ ዕድልንም ያሰፋል። የፕሮግራሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን “በአየር ንብረት ላይ የምናደረገውን ዘመቻ የምናጠናክርበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉም ነው ዓለም አቀፍ ጥሪ ያስተላለፉት።

የጎርፍ አደጋ የዛሬ ብቻ ችግር አይደለም፤ የነገም ፈተና ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ዝናብን በብዙ አካባቢዎች እያባባሰ በመሆኑ ሀገራት ከአደጋው በኋላ ምላሽ ከመስጠት ወደ አደጋን ቀድሞ መከላከልና መላመድ መሸጋገር ይኖርባቸዋል።

በመጨረሻም ጎርፍን ለማስቆም ከተፈጥሮ ጋር መወዳደር ሳይሆን ውኃው የት እንደሚሄድ ቀድሞ ማወቅ፣ ሰዎችን ቀድሞ ማስጠንቀቅና ከተሞችን አደጋን እንዲቋቋሙ ማድረግ (መገንባት) መፍትሔ ነው።

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጳጉሜ 2  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here