የውህደቱ ምስጢር ምን ይገልጥ ይሆን?

0
176

የገበሬው ጉልበት እና ሀብት ተበታትኖ፣ ቁጥራቸው የበዛ ነገር ግን አቅማቸው የደከመ የኅብረት ሥራ ማህበራት የነገሱበት ጊዜ እያከተመ ይመስላል። በዘመናዊ ግብርና የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአማራ ክልል የተጀመረው የኅብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም (የለውጥ) እና የውህደት ሥራ አስደሳች ፍሬ ማፍራት ጀምሯል።

በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የአርሶ አደሩን የግብዓት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለመው ግዙፉ “አንድነት የዘር ብዜት እና ግብይት ኅብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን” በይፋ ተመስርቷል። በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው የክልሉ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የሁለቱ ዩኒየኖች ውህደትም የዚሁ ሪፎርም አካል እንደሆነም ተጠቅሷል።

ዩኒየኑ የተመሰረተው በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው “ጉና” እና በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው “እድገት ለአንድነት” የዘር ብዜት እና ግብይት ዩኒየኖችን ወደ አንድ ጠንካራ ተቋም በማምጣት ነው። በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የማዋሀድ መርሃ-ግብር ላይ የገጠር ክላስተር ተቋማት አስተባባሪ፣ የግብርና ቢሮ እና የኅብረት ሥራ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ አባል አርሶ አደሮች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የ‘እድገት ለአንድነት’ እና ‘ጉና’ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኖች በይፋ መዋሀዳቸው ተበስሯል።

የእድገት በአንድነት የዘር ብዜት እና ግብይት የኅብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደሴ ተረፈ  ለበኩር እንደተናገሩት ዩኒየኑ የተመሰረተው በ331 ሚሊዮን 792 ሺህ 43 ብር መነሻ ካፒታል ነው። የውህደቱ ዓላማም የሁለቱን ዩኒየኖች የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ፣ የምርት እና የግብይት አቅም በማቀናጀት የዘር ብዜት እና ግብይት ሥራዎችን በተሻለ አቅም ለማከናወን፣ ለአባላት የተሻለ አገልግሎት እና የገበያ እድል መፍጠር እንዲሁም የዩኒየኑን ዘላቂነት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

የሁለቱ ዩኒየኖች ውህደት ተጠናቆ “አንድነት የዘር ብዜት እና ግብይት ኀብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን ምስረታ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።

የአዲሱ ዩኒየን ምስረታ በዘር ብዜት እና ግብይት ዘርፍ የተሰማሩ ኅብረት ሥራ ማህበራትን አቅም በማቀናጀት፣ የምርጥ ዘር እና የግብርና ግብዓት አቅርቦትን በብዛት፣ በጥራት እና በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል። በውይይቱም በክልሉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የዘር አምራች ኅብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።

በስምንት ዞኖች እና በአራት የከተማ አስተዳደሮች ላይ አደረጃጀቱን የዘረጋው ይህ አዲሱ “አንድነት ዩኒየን”፤ 51 መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራትን በአባልነት መያዙን የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል። 250 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ ፋብሪካ፣ ከስድስት በላይ የዘር ማከማቻ ዘመናዊ መጋዘኖች፣ ሦስት ዘመናዊ የዘር ማበጠሪያ ማሽኖች፣ የተሟላ የዘር ጥራት ማረጋገጫ ላቦራቶሪ እንዲሁም የጭነት መኪኖች እና ሁለት ትራክተሮች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ዋና ጽሕፈት ቤቱን በክልሉ ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር ከተማ ያደረገው አንድነት ዩኒየን፤ ለጊዜው በቡሬ እና በደብረ ታቦር ከተሞች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቷል ነው ያሉት። በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሁሉም ዞኖች ቅርንጫፎቹን በማስፋፋት ለአርሶ አደሩ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት አቅዷል።

በተጨማሪም ዩኒየኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የዘር ግብይት ሰንሰለቱን ለማሳለጥ አርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት የሚያገኝበትን መንገድ ከማመቻቸት ባለፈ በባሕር ዳር ከተማ ዘመናዊ መጋዘን እና የተለያዩ ግንባታዎችን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።

አንድነት ዘር ብዜት እና ግብይት ኀብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን የቁጥጥር ሰብሳቢው አቶ ጋሹ አየነው  ለበኩር ጋዜጣ እንደገለጹት፤ “እድገት ለአንድነት” የዘር ብዜት እና ግብይት ዩኒየን በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰፊ የዘር ብዜት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዋናነት የበቆሎ እና የስንዴ ምርጥ ዘሮችን የሚያባዛ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ በተሻለ አሰራር የባቄላ ምርጥ ዘርን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማህበሩ አባላቱን በባለቤትነት ስሜት ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ እየሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ ጋሹ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራትም ሆኑ ግለሰብ አባል አርሶ አደሮች በማህበሩ ባላቸው የተሳትፎ ልክ በየዓመቱ የትርፍ ክፍፍል እያገኙ እንደሚገኙም አብራርተዋል። በዘርፉ የተሻለ አሰራርን በመዘርጋት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ዩኒየኖች በተናጠል በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ጤናማ ያልሆነ የገበያ ሽሚያ እና የዘር አቅርቦት መደራረብ ይስተዋል እንደነበር አቶ ጋሻው ጠቁመዋል። በመሆኑም የሁለቱ ዩኒየኖች ውህደት ይህንን ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል።

በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው በዚህ የውህደት መርሃ- ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር ተቋማት አስተባባሪ   ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት ውህደቱ የተበታተነ አቅምን ወደ አንድ ትልቅ የኢኮኖሚ ጉልበት የመቀየር እርምጃ ነው።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ በበቆሎ ላይ ብቻ ተወሰኖ የነበረውን የምርጥ ዘር ብዜት አሁን ወደ ሌሎች የሰብል ዓይነቶች ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። አዲሱ “አንድነት የዘር ብዜት ዩኒዮን” ለክልሉ አርሶ አደር ዘር ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክልሎችም ጭምር የማቅረብ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል። ውህደቱ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር በማኅበረሰቡ መካከል ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርን እና አንድነትን  የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ ውህደት ፈጠሩ ተብሎ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን ይህ ዩኒየን በጣም ጠንካራ ሆኖ ለክልላችንም ብሎም ለሀገር ዘር የማምረት ሥራ ይጠበቅበታል።

ዶክተር ድረስ አክለውም የተበታተነውን አቅም በማሰባሰብ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ተቋም መፍጠር የግብርናውን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ  ወሳኝ  እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ ጥረት የሀገራችንን የምርት እና ምርታማነት ዕድገት በማፋጠን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መሠረት የሚጥል በመሆኑ የክልሉ የገጠር ክላስተር እና የግብርና ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማህበር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ በበኩላቸዉ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በክልሉ በርካታ ማኅበራት ቢኖሩም በአብዛኞቹ ዘንድ የአቅም ማነስ፣ የካፒታል እጥረት እና አባላትን በአግባቡ ያለመጥቀም ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የኅብረት ሥራ ማህበራትን አሰራር እና አደረጃጀት ለመለወጥ ተበታትነው የነበሩ አቅሞችን እና ሐብቶችን ወደ አንድ በማምጣት ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የኅብረት ሥራ ማህበራትን ለመፍጠር ኮሚሽኑ ሲሠራ መቆቱን  አስታውቀዋል። በተለይም አርሶ አደሮች ጥራት ያለው የግብርና ግብዓት በወቅቱ እና በቅርበት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል። በአርሶ አደሮች እና በሸማቹ መካከል የሚቆሙ አላስፈላጊ ደላሎችን በማስወገድ እና ምርቶችን ከአምራቹ በቀጥታ በመረከብ ለሸማቹ ማቅረብ ያስችላል።

አዲሱ “አንድነት የዘር ብዜት ዩኒየን” ከ331 ሚሊዮን ብር በላይ መነሻ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ የገባ መሆኑን ያስረዱት ኮሚሽነር ጌትነት የምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ ጎንደር፣ የምሥራቅ ጎጃም እንዲሁም የማዕከላዊ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖችን ያካተተ ሰፊ የአገልግሎት አድማስ ይኖረዋል ነዉ ያሉት፡፡ ይህ ውህደት ዩኒየኖቹ ያላቸውን የሀብት፣ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅም በማቀናጀት አርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር  በወቅቱ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የግብርና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ የላቀ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል።

ኮሚሽነሩ የዞን አመራሮች፣ የግብርና ቢሮ እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት (ATI) ላደረጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ “ውህደት ሀይል ነው” ያሉት ኮሚሽነር ጌትነት ይህ ጅማሮ ሌሎች የኅብረት ሥራ ማህበራትም ከጥቃቅን ፍላጎት ወጥተው ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ተቋምነት እንዲሸጋገሩ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ይህ የሁለት ትላልቅ ዩኒየኖች ውህደት በክልሉ አልፎም በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘር ብዜት እና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

“አንድነት” ዘር ብዜት እና ግብይት ኀብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን የሁለቱን ዞኖች አቅም በማቀናጀት የአባል መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራትን በማጠናከር ብቻ ሳይወሰን በክልሉ ያለውን የዘር እጥረት በመቅረፍ የዘር ብዜትን የማስፋፋት እና የምርት ግብይትን የማሻሻል አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

 

ዜና

በባሕር ዳር ከተማ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት አሠራሩን በቴክኖሎጂ በማዘመን የሕብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዉ አቶ አብርሃም ወርቁ ለበኩር እንደተናገሩት ተቋሙ በዚህ ዓመት የሕብረተሰቡን ችግሮች በጥራት፣ በብዛት እና ፈጣን በሆነ መንገድ ለመፍታት የለውጥ ሥራዎችን አከናውኗል።

ቀደም ሲል ለብልሹ አሠራር እና ለጉቦ የተጋለጠውን ኋላቀር አሠራር በማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አሠራር ተዘርግቶ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። በዚህም ባለፉት ዐሥር ዓመታት ሊሠሩ ያልቻሉ ሥራዎችን አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ማጠናቀቅ ተችሏል።

በተለይም በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል፤ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ የጸጥታ አካላትን እና ጡረተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመኖሪያ ቤት የኅብረት ሥራ ማህበራትን የማደራጀት ሥራ ማከናወኑ በስኬት አንስተዋል።

ጽሕፈት ቤቱ ላከናወናቸው ችግር ፈች ተግባራት ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማህበራት የግምገማ እና ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ላይ ከፍተኛ ዕውቅና እና ምስጋና ተበርክቶለታል።

 

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here