“ሰባቱ  ከዘራ   የማኅበረሰብን እሴት ያከበረ  የሽምግልና ሥርዓት ነው”

0
482

መጋቢ ሰላም አየልኝ ክብረት ይባላሉ፡፡ ተወልደው  ያደጉት በሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደባርቅ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ አሁን ላይ በደባርቅ ከተማ እና በሌሎችም አከባቢዎች በስፋት በሚታወቀው የሰባቱ ከዘራ የባሕል ሽምግልና ዋና ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

መጋቢ ሰላም አየልኝ የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓቱን የተቀላቀሉት በዕድሜያቸው ወጣት በሆኑበት ወቅት ነው፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያት ሆኖ የሚነሳው በንግዱ ዓለም ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር መተዋወቅና መግባባት በመቻላቸው ነው፡፡ ከእንግዳችን ጋር ስለ ሰባቱ ከዘራ የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓትና ሌሎችንም ጉዳዮች እያነሳን ቆይታ አድርገናል፡፡

መልካም ንባብ!

 

የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት ጠቅለል ያለ ጠቀሜታው ምን ይሆን?

በደባርቅ አከባቢ የሚገኘው ሰባቱ ከዘራ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ለረጅም ጊዜ የቆየ የሽምግልናና የዕርቅ ሥርዓት ነው፡፡የአከባቢያችን ማኅበረሰብ በመንግሥት ፍርድ ቤቶች ከመዳኘት ይልቅ የሰባቱን ከዘራ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ያስቀድማል፤ ወደ ባሕል ሽምግልናው የሚመጡት ተካሳሾች (የተጣሉ ሰዎች) ችግሮቻቸው በርከት ያሉ እና መልከ ብዙ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን በኛ መታረቅን ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ በመሆኑ ለዕርቅ እምቢ የሚለን ሰው የለም፡፡

 

ሰባቱ ከዘራ የሚለው ስያሜ እንዴት መጣ?

ስያሜው የመጣው በአንድ ወቅት በደባርቅ ከተማ ውስጥ በተፈጠረ የመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ሰባት ሽማግሌዎች እንደ ሀገራችን የሽማግሌ ወግ መሠረት ሰባታችንም ከዘራችንን ይዘን የሰዎችን ቅሬታ በምንፈታበት ወቅት የተሰጠን ስያሜ ነው፡፡

 

እስኪ የቅሬታውን መንስኤ ይንገሩን?

እኛ ሰባቱ ከዘራዎች የምንባለው ባሕላዊ ሸምጋዮች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የልማት፣ የጸጥታ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እየገባን በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ በአንድ ወቅት በደባርቅ ከተማ ውስጥ አንድ ፎቅ ፈርሶ ለግል ባለ ሃብት (ኢንቨስተር) ቦታው ተሰጠና ባለ ሃብቱ ያንን ፎቅ አፍርሶ በምትኩ ቪላ ቤት ሠራበት፡፡ ይሄንን ጉዳይ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች  ተቃውመው ቅሬታቸውን ለኛ አቀረቡ፡፡

እኛም የሕዝቡን ቅሬታ ይዘን ወደ ቦታው በማቅናት ልማት ማለት ከፎቅ ወደ ተሻለ ፎቅ እንጂ እንዴት ዝቅ ወዳለ ቪላ ቤት ይሆናል?

በማለት ቅሬታችንን አሰማን፡፡  ኢንቨስተሩ ለተሻለ ልማት ብሎ በተቀበለው ቦታ ላይ የተሻለ ነገር ባለመሥራቱ እኛ ሰባት የአከባቢው ሽማግሌዎች ከመንግሥት ጋር በመሆን  የተጀመረው ግንባታ ባለበት እንዲቆም አስደረግን፡፡ ይህ ግንባታ ባለበት መቆሙን የተረዱ የአከባቢው ነዋሪዎች ባለ ሃብቱን ለምን ግንባታውን እንዳቋረጠ ሲጠይቁት ”የሆኑ ሰባት ከዘራ የያዙ ሽማግሌዎች ናቸው፤ ሕዝቡን አስተባብረው ግንባታዬ እንዲቋረጥ ያደረጉት”ሲል መለሰላቸው፡፡

ከዚሁ የባለ ሃብቱ ንግግር ተነስቶም የኛ የሽምግልና ሥርዓት ስያሜ ሰባቱ ከዘራዎች የሚል ሆነ፡፡

 

 

ከእናንተ ከሰባቱ ከዘራዎች የሚቀድም ሽምግልናስ አልነበረም?

ነበረ፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት በደባርቅ የነበሩ ባሕላዊ ሸምጋዮች ራሳቸውን ችለው እንደ ተቋም የሚታዩ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች በአከባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ቅሬታ ይፈጥር የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አለመኖር ወደ ፌዴራል መንግሥት በመሄድ ትምህርት ቤት እንዲከፈት እስከ ማድረግ ደርሰዋል፡፡  እነዚያ የቀደሙ የባሕል ሽማግሌዎች መንግሥትና ሕዝብን ከማቀራረብ ሚናቸው በተጨማሪ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ ግጭቶችንና ቅሬታዎችን ለማርገብ የነበራቸው ሚናም ከፍተኛ ነው፡፡

 

ሰባቱ ከዘራ የሚለው ስያሜ ሲወጣ እርስዎም ነበሩበት?

አዎ፡፡ በወቅቱ ከሰባቱ ሽማግሌዎች በዕድሜ ትንሹ ሽማግሌ እኔ ነበርኩኝ፤ አሁን የተወሰኑት ሽማግሌዎች በዕድሜ ምክንያት ወደ ማይቀርበት ሄደዋል፡፡ በነሱ ቦታ ሌሎች ተተክተው ሰባቱ ከዘራዎች አሁንም በደባርቅ ውስጥ በእጅጉ የሚታወቅ የባሕላዊ ሽምግልና ሆኖ ቀጥሏል፡፡

 

ከሰባቱ ከዘራ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ እስኪ ጥቂቶቹን ይግለጹልን?

ሰባቱ ከዘራ በዋናነት ከሚሠራቸው የዕርቅና የሽምግልና ሥራዎች በተጨማሪ ለአከባቢው ሰላምና ልማትም አበክሮ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ባንድ ወቅት አንድ ግለሰብ የሱ ይዞታ የሆነ ቦታ ለሆስፒታል መሥሪያነት ተፈልጎ ቦታዬን አለቅም ብሎ አስቸግሮ ነበር፤ እኛ ግን በተሰጠን ጸጋና ጥበብ ተጠቅመን ሰውዬውን በማሳመን በዚያ ቦታ   ላይ  ሆስፒታል  እንዲገነባ  ማድረግ ችለናል፡፡ ለቴሌ  እና ለደባርቅ ዩኒቨርሲቲ መገንቢያነት ቦታ እንዲመቻች ያደረገውም ሰባቱ ከዘራ ነው፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡም ሰባቱ ከዘራ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

 

ሰባቱ ከዘራ ከደባርቅ ውጪስ ይታወቅ ይሆን?

አሁን ላይ ሰባቱ ከዘራ በዞን፣ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ በዞናችን ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የሚካሄዱ የእርስ በርስ መገዳደሎች እና ዝርፊያዎችን ለማስቆምም ሰባቱ ከዘራ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ሰባቱ ከዘራ የራሱን ሕግ እና ደንቦች አውጥቶ የትራፊክ አደጋ ሲደርስ፣ በዕለታዊ ግጭት ወቅት፣ አስቦ እና ሆን ብሎ አደጋ በሚያደርስ ሰው ላይ እና በሌሎችም ነገሮች ላይ ወጥ የሆኑ የሽምግልና ሥራዎችን እንሠራለን፡፡

አሁን ላይ በጸጥታ ችግር ምክንያት እንደበፊቱ ከወረዳዎች ጋር ተናብበንና ተጋግዘን መሥራት ባንችልም ሰባቱ ከዘራዎች ግን ወጥ የሆነ አሠራሮችን ያበጀ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በበዳዮች ላይ የሚተላለፈው የቅጣት እና የካሣ ክፍያም ወጥ እና ተመሳሳይ ነው፡፡ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሰው መግደል፣  ወንጀለኛን የሚያግዝ እና የሚደብቅ ሰው ከሚጣልበት የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ በእድር፣ በሰንበቴና በመሳሰሉት ነገሮች  ላይ  እንዳይሳተፍ  እገዳ    ይደረግበታል፡፡

ሰባቱ ከዘራ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እንዴት ይገለጻል?

ሰባቱ ከዘራ የመንግሥት የፍትሕ ሥርዓትን ከማገዝም አልፎ በራሱ በማኅበረሰቡ በጣም ተቀባይነት ያገኘ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በመንግሥታዊው ፍርድ ቤት ፍትሕ ላይ ቅሬታ ሲያድርባቸው ወደኛ መምጣት ይፈልጋሉ፤ እኛ ግን የራሳችን የሆነ ጽሕፈት ቤት ወይም ቢሮ ስለሌለን አገልግሎታችንን የሚፈልጉ ሰዎች በመጉላላት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሰባቱ ከዘራ የማያምን የማኅበረሰብ ክፍል የለም፡፡ እኛም ወጣቶችን ወደ  ራሳችን  በመቀላቀል  የሽምግልና     ሥርዓቱን እንዲያስቀጥሉ እያለማመድናቸው እንገኛለን፡፡

 

ስለ ባሕላዊ ሽምግልና ጠቀሜታ የመጨረሻ መልዕክት ካለዎት?

የአማራ ክልል ሕዝብ ዘመዶቹን ለመጠየቅ የመንገድ ርቀት የማይገድበው፣ እንግዳ በአከባቢው ሲያልፍ ጎትቶ አስገብቶ የሚያበላ፣ ሰው በአውድማ አጠገብ ሲያልፍ ተገድዶ እህል ውኃ የሚቀምስበት፣ በሠርጉና በማኅበሩ ሰው ካልበላለት ደስ የማይለው ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡

ይህ ሕዝብ አሁን ላይ የሚያደርገው የእርስ በርስ መጠፋፋት ከእሱነቱና ከባሕሉ በጣም የወጣ ነው፡፡ በርካታ ባሕላዊ የሽምግልናና የዕርቅ ሥርዓቶች ባሉባት ሀገራችን ውስጥ የዚህ ዓይነት  መጎደዳት በጣም  እያሳመመን         ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም የባሕል ሽማግሌዎችና አስታራቂዎች የበለጠ ኃላፊነት ተሰምቶን ልንሠራ ይገባል፡፡

 

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here