አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ተስፋ መሰነቁ፣ ግለሰቦችና ተቋማትም አዳዲስ ግቦችን በወረቀት ላይ መዘርዘራቸው የተለመደ ልማድ ነው። ሆኖም ዓመታት እየተፈራረቁ የዕቅድ ሰነዶች ቢከመሩም፣ ወደ መሬት ወርደው በውጤት የሚለወጡት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸው መራር እውነት ነው። የዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከስልታዊ ዕቅዶች እስከ 67 በመቶ የሚደርሱት በወረቀት ላይ ይከሽፋሉ። ችግሩ የማቀድ ፍላጎት ማጣት ሳይሆን፣ በዕቅድና በትግበራ መካከል ያለው ሰፊ “የአፈጻጸም ክፍተት” ነው።
ለብዙ ዕቅዶች ስኬታማ አለመሆን እንደምክንያት ከሚጠቀሰው በርካታ ክፍተቶች አንዱ ዕቅድን ከተጨባጭ አቅም ይልቅ በስሜታዊ ምኞት ላይ መገንባት ነው። የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የጊዜ እና የሰው ኃይል አቅምን ያላገናዘበ ዕቅድ ገና ሲወለድ የሞተ ነው። በሌላ በኩል፣ በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት ተግባርን ከውጤት ጋር ቀላቅለው ሳይለዩ ማቀዳቸውም እንደተጨማሪ ምክንያት ይጠቀሳል። ሁልጊዜም ቢሆን የሚቃቀዱ እቅዶች የተለጠጡ፣ መዳረሻቸው የማይታወቅ፣ ወቅትን ያላገናዘቡ፣ ከመቼ እስከ መቼ ይከናወናል እና ምን ክፍተት ለመሙላት እንዳለሙ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ከመነሻው ካልታወቀ የመፈጸም እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በየጊዜው መደበኛ ሪፖርት ማዘጋጀት በራሱ ግብ አይደለም፤ ሊጠየቅ የሚገባው ዋናው ጥያቄ “እነዚህ ሥራዎች ምን ያህል ተጨባጭ ለውጥ አመጡ?፣ ቀሪውን ስራ እንዴት ባለሁኔታ እስከመቼ እናከናውነው?” የሚለው ነው። በተጨማሪም ግልጽ የተጠያቂነት አሠራር አለመኖር እና ክትትልን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ማዘግየት ስህተቶችን በጊዜ እንዳይታረሙ በማድረግ ዕቅድን ወደ ሰበብነት ይቀይሩታል።
በፈጣን ዕድገት የተሻገሩ ሀገራትም ሆኑ ስኬታማ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያስተምሩን ትልቁ ትምህርት ዕቅድን በሳይንሳዊ ሥርዓት መምራት ነው። አንድ ግለሰብም ሆነ ተቋም ስኬታማ ዕቅድ ለማውጣት ሦስት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ አንዱና ዋነኛው የእቅድመነሻ መሆን ያለበት ነባራዊ ሁኔታን ማወቅ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ውድቀትና ስኬት በመነሳት ትክክለኛውን ውስጣዊ አቅም በመመርመር፤ ግቦችን በማስቀመጥና እቅዶች የሚለኩና እንዲሁም በስሜታዊነት ያልታቀደና ሃሳብ ብቻ ሆኖ የማይቀር እንዲሁም መስራት የሚቻል መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ባሻገር የታለመው ግብ ከሚጠይቀው በጀትና የፈጻሚ አቅም ጋር መቶ በመቶ መናበቡን ማረጋገጥና እቅዱን ለማሳካት ያለንን ሃብት ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡
አንድ ትልቅ ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን በጊዜና በመጠን መከፍፈል አለበት፡፡ አንድ ዓመታዊ ግብ እንዳለ ወደ ትግበራ አይገባም፤ ይልቁንም ወደ አራት ሩብ ዓመታት፣ ከዚያም ወደ ወርሃዊ እና ሳምንታዊ የተግባር ምዕራፎ መከፋፈል ይኖርበታል። የብዙ እቅዶቻችን ችግሮች በዓመቱ መጨረሻ በጥድፊያ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ለመከወን መሞከር ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ ክትትሉ የዓመቱን መጨረሻ ሳይጠብቅ በየሳምንቱ እና በየወሩ አፈጻጸሙን በየጊዜው መገምገምና መከታተል ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ፣ አዲስ ዓመት አዲስ ቀን ብቻ ሳይሆን አዲስ የአስተሳሰብና የአሠራር ምዕራፍ መሆን አለበት። ዕቅድ የለውጥ መነሻ እንጂ መድረሻ አይደለም። ግልጽ ተጠያቂነት እና ተከታታይ የክትትል ሥርዓት ያልታከለበት ዕቅድ የቀን ቅዠት ብቻ ሆኖ ይቀራል። በመሆኑም ወደ አዲሱ ዓመት ስንሻገር ከባዶ የተስፋ ቃላት ወጥተን ወደ ተጨባጭ፣ በተግባር ወደ ሚለካና ውጤት ወደሚያመጣ የአፈጻጸም ባህል ልንሸጋገር ይገባል።
በኲር የጳጉሜ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


