የፕላኔታችን የእግር ኳስ መሲህ

0
73

የፊዚክስ ሳይንቲስት ቢሆን እንደ አልበርት አንስታይን፣ ሙዚቃ ቢቀምር እንደ ቢትሆቨን፣ ብዕር ቢያነሳ እንደ ዊሊያም ሼክስፒር፣ የሰው ልጅን አዕምሮ ቢያጠና እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ የረቀቀውን እውነት ይደርስበት ነበር፡፡ በፍልስፍናው ቢራቀቅ ደግሞ እንደ ሶቅራጥስ ጥበብን ያፈልቅ ነበር ይሉታል፡፡ እርሱ ግን የእግር ኳስ ዛር ጠርቶታልና የምንጊዜም የእግር ኳስ መሲህ ሆነ—ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ፡፡

ይህ ስም የእግር ኳስ መጠሪያ ብቻ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ የአካል፣ የአዕምሮ እና የታክቲክ ጥበብ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ፍጹም ሆኖ የተገለጠበት የታሪክ ክስተት ጭምር እንጂ፡፡ ሜሲ በእግሩ የሚሠራው ገድል የባዮሎጂካል ፈተና ድል፣ የስነ-ልቦና ጽናት፣ የቦታ እና የጊዜ ጂኦሜትሪ ትንታኔ እንዲሁም የዘመናት ትጋት ድምር ውጤት ነው፡፡

የተዋጣለት የኳስ ጠቢብ እና ወደር የማይገኝለት የተፈጥሮ ክህሎት ባለቤት ነው፡፡ የፍጹም ቅጣት ምት ስፔሻሊስት፣ ጨራሽ ግብ አነፍናፊ እና ለቡድን ጓደኞቹ ያለቀላቸው ገዳይ ኳሶችን የሚቀብል  የእግር ኳስ ሊቅ ነው፡፡ የተጋጣሚን ቡድን  እንደ ንፋስ እየሾለከ የሚያሸብር ድንቅ ባለተሰጥኦ ነው፡፡ ትውልዱን በተሰጥኦው እና በብቃቱ አስደምሟል፤ አከራክሯል፡፡ የአካላዊ እድገቱን ችግር  በእጥረት እና በጽናት አሸንፎ ከሮዛሪዮ መንደር ወደ ዓለም የእግር ኳስ ንጉሥነት ራሱን አሸጋግሯል፡፡ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ይከተለዋል፡፡ የቁርጠኝነት ተምሳሌት የሆነው ይህ ስም በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ በታላቅ አክብሮት ይነሳል፡፡

ከአርጀንቲናዋ ሮዛሪዮ ተነስቶ በካታሎኒያዋ ባርሴሎና ጎልብቶ በካምፕ ኑ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያንጸባረቀው ሊዮኔል ሜሲ፣ በተፈጥሮ ስጦታው እና ባልተቋረጠ ጥረቱ የብዙዎች ተምሳሌት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ 46 ዋንጫዎችን በማንሳት በታሪክ ብቸኛው እና ቀዳሚው ባለክብረወሰን ለመሆን በቅቷል፡፡ በስፔን ላ ሊጋ፣ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ክብረወሰኖችን በእጁ አስገብቷል። ከአንድ ሺህ 100 በላይ ይፋዊ ጨዋታዎችን በማድረግ ከ850 በላይ ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ከ400 በላይ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ከቡድን ስኬቶቹ ባሻገር ለቁጥር የሚታክቱ የግል ክብሮችን በመጠቅለል ወደር የማይገኝለት ጥበበኛ ነው፡፡ ስምንት የባሎን ዶር፣ ስምንት የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች፣ ስድስት የአውሮፓ የወርቅ ጫማዎች እና ስምንት የስፔን ላ ሊጋ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት (ፒቺቺ) ሽልማቶችን ሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ምርጥ ተጫዋች፣ የዓለም የምንጊዜም ምርጥ ኳስ ቀማሪ (IFFHS Best Playmaker)፣ የኮፓ አሜሪካ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል፡፡ በቡድን ስፖርት ታሪክ ብቸኛው የዓለም የሎሬስ (Laureus) ኮከብ ስፖርተኛ ተብሎ ሁለት ጊዜ መመረጡ የግል ልዕልናው ማሳያ ናቸው፡፡ በተለይም በ2012 እ.አ.አ በአንድ የውድድር ዘመን ብቻ ያስቆጠራቸው 91  ግቦች በጊነስ ድርሳን ላይ የሰፈሩ አስደናቂ ክብረወሰን ናቸው፡፡

በ17 ዓመታት የባርሴሎና ቆይታውም በ778 ጨዋታዎች 672 ግቦችን አስቆጥሮ 35 ዋንጫዎችን በማንሳት የክለቡ የምንጊዜም ታላቅ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡ እ.አ.አ በ2021 ወደ ፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አምርቶ ሁለት የሊግ ዋንጫዎችን ያሳካ ሲሆን በ2023 ወደ አሜሪካው ኢንተር ማያሚ በማቅናትም ክለቡን ለታሪካዊ የዋንጫ ድሎች አብቅቷል፡፡

የእግር ኳስ ብራናውን ገልጠን ታሪኩን ስንመረምረው የእግር ኳስ መሲሁ ታሪክ የሚጀምረው ሰኔ 24 ቀን 1987 እ.አ.አ ነው፡፡ የእግር ኳሱ ልዑል በአርጀንቲናዋ የኢንዱስትሪ ከተማ በሮዛሪዮ መወለዱን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ያደገው ግን ላስ ሄራስ በተባለችው በድህነቷ በምትታወቀው መንደር ውስጥ ነው፡፡ አባቱ ጆርጌ ሜሲ የፋብሪካ ሠራተኛ የነበረ ሲሆን እናቱ ሴሊያ ኩቺቲኒ ደግሞ የትርፍ ጊዜ የጽዳት ሠራተኛ ነበረች፡፡

በመንደሩ የሚገኙ ታዳጊዎች እግር ኳስ ተጫዋች መሆንን ከድህነት ማምለጫ ብቸኛ መንገዳቸው አድርገው ይመለከቱት ነበር፡፡ ታዲያ ታዳጊው ሌዮኔል ሜሲም እ.አ.አ በ1992 ገና በአምስት ዓመቱ ግራንዶሊ በተባለ የአካባቢው ክለብ ውስጥ መጫወት ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ሲነጻጸር ቁመቱ እጅግ አጭር በመሆኑ እግር ኳስ መክሊቱ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ይነገረው ነበር፡፡ አያቱ ሴሊያ ኦሊቬራ ግን የልጅ ልጃቸውን ድንቅ ክህሎት ተረድተዋልና ተስፋ አስቆራጩን ወሬ አልተቀበሉትም (እስከ ዛሬ ድረስ ግብ ሲያስቆጥር ወደ ሰማይ እጆቹን የሚያነሳው እርሳቸውን ለማሰብ ነው)፡፡ በመጨረሻም ታዳጊው የኒውዌልስ ኦልድ ቦይስን አካዳሚ ተቀላቀለ፡፡

በ10 ዓመቱ ግን ያልተጠበቀ ከባድ ፈተና ገጠመው፡፡ የአካል እድገት ሆርሞን እጥረት እንዳለበት በህክምና ተረጋገጠ፡፡ ይህ ህመም በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ቁመቱ እንዳያድግ እና የእግር ኳስ ህልሙ እንዲቀጭጭ የሚያደርግ ነበር፡፡ በአርጀንቲና በወቅቱ በተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት ቤተሰቡ ወጪውን መሸፈን አልቻለም፤ ኒውዌልስ ክለብም የሜሲን የህክምና ወጪ ለመሸፈን ቃል ቢገባም ቃሉን ማክበር ተስኖት ቀረ፡፡ የልጁ እግር ኳሳዊ ተሰጥኦ የገዘፈ መሆኑን የተረዱት አባቱ ጆርጌ ተስፈኛውን ታዳጊ የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቆራርጦ ካታሎናውያን ቤት እንዲደርስ አደረገው፡፡ በወቅቱ የባርሴሎና የስፖርት ዳይሬክተር የነበረው ካርለስ ሬክሳች የታዳጊውን አስደናቂ ጥበብ በተመለከተበት ቅጽበት ከእጃቸው እንዳያመልጣቸው ወሰነ፡፡ በጥድፊያም በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ታህሳስ 14 ቀን 2000 ዓ.ም በአቅራቢያ በሚገኝ ካፌ ውስጥ ለባርሴሎና ፊርማውን በሶፍት ናፕኪን ላይ እንዲያስቀምጥ ተደረገ፤ ህክምናውንም ተከትሎ ዝነኛውን የላማሲያ አካዳሚ ተቀላቀለ፡፡

በላማሲያ አካዳሚ ጎልብቶ ወደ ዋናው ቡድን ሲያድግ እንደ ሮናልዲንሆ ባሉ ድንቅ ኮከቦች ተከቦ አደገ፡፡ ከዚያም ባርሴሎናን እና ላሊጋውን ወደ ላቀ ምዕራፍ አሸጋገረ፡፡ በስፔን በነበረበት ወቅት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የፈጠሩት የዘመናት ፉክክር የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው የውድድር ምዕራፍ ተደርጎ ተመዝግቧል፡፡

የሜሲ የሜዳ ላይ ስነ ምግባር አጃኢብ ያሰኛል፡፡ ተከላካዮች በጭካኔ ጥፋት ቢሰሩበትም ላለመውደቅ እስከመጨረሻው ይታገላል፡፡ ከሜዳ ውጭ ያለው ህይወቱም ፍጹም የተረጋጋ እና ከፓፓራዚዎች የራቀ ነው፡፡ ገና በአምስት ዓመቱ የተዋወቃትን የልጅነት ፍቅሩን አንቶኔላ ሮኩዞን በትዳር አጣምሮ የሦስት ወንዶች ልጆች (ቲያጎ፣ ማቴኦ እና ቺሮ) አባት ሆኖ በትህትና እየኖረ ይገኛል፡፡ ሜሲ ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎችም የብዙ ሚሊዮኖችን ሕይወት የቀየረ ታላቅ ሰብዕና አለው፡፡ እ.አ.አ በ2007 የሊዮ ሜሲ ፋውንዴሽንን በማቋቋም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ህጻናት የትምህርት እና የጤና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከ2010 ጀምሮ የዩኒሴፍ (UNICEF) የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሲሆን በባርሴሎና ለሚገኘው ግዙፉ የህጻናት ካንሰር ማዕከል ግንባታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ በማሰባሰብ እና በግሉ በመለገስ አሻራውን አኑሯል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያም በኢንስታግራም ብቻ ከ500 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን የዓለም ዋንጫን ካነሳ በኋላ ያጋራው ፎቶ ከ75 ሚሊዮን በላይ መውደድ (Likes) በታሪክ ወደር የማይገኝለት ክብረወሰን ሆኖ ተቀምጧል፡፡

የሜሲን ታላቅነት ለመዘከር በትውልድ ከተማው ሮዛሪዮ እና በቦነስ አይረስ በርካታ ሐውልቶችና ግዙፍ የግድግዳ ላይ ሥዕሎች ተሰርተውለታል፤ የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበርም (AFA) በኤዜዛ የሚገኘውን ብሔራዊ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል “ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ” በሚል በስሙ ሰይሞታል፡፡

የሜሲ የህይወት ትልቁ ገድል ግን የተጻፈው በሀገሩ አርጀንቲና ማሊያ ነው፡፡ በ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ቢያገኝም፣ በዋናው ቡድን ለዓመታት በፍጻሜ ጨዋታዎች በደረሱበት የልብ ስብራቶች ሳቢያ ተስፋ ቆርጦ ሀገሩን ማገልገል አቁሞ የነበረ ቢሆንም፣ በመላው ህዝብ ልመና ተመልሶ መጣ፡፡ የትዕግስቱም ዋጋ በክብር ተከፈለ። እ.አ.አ በ2021 የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን በማንሳት የሀገሩን የ28 ዓመታት ድርቅ አስወገደ፤ በ2022 እ.አ.አ ደግሞ የፊናሊሲማ እና የኳታር ዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን ሆነ፡፡ በኳታር በሁሉም ዙሮች ግብ ያስቆጠረ እና ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች (Golden Ball) የተባለ በታሪክ ብቸኛ ተጫዋች ሆነ፡፡

በ2024ም ሁለተኛውን ተከታታይ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ በማንሳት ሁሉንም ማዕረጎች ያሟላ ብቸኛ የእግር ኳስ ንጉሥ ሆነ፡፡ ይህ ጉዞው በቅርቡ ፍጻሜውን አግኝቷል። ሊዮኔል ሜሲ ከ21 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ከብሔራዊ ቡድኑ መሰናበቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎም በመላ ሀገሪቱ በሚደረጉ ማናቸውም ይፋዊ ግጥሚያዎች በ10ኛው ደቂቃ ጨዋታ ቆሞ መላው ስታዲየም ለቁጥር 10 ማሊያው ባለቤት የ60 ሴኮንድ የክብር ጭብጨባ አበርክቶለታል፡፡

የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበርም እርሱ ለለበሰው ታሪካዊ 10 ቁጥር መለያው ከእንግዲህ ማንም እንዳይለብሰው ለዘላለም በክብር አስቀምጦለታል፡፡ አዎን! ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ ተራ ተጫዋች አልነበረም፤ ሜዳውን እንደ ሸራ፣ ኳሷን እንደ ቀለማት ተጠቅሞ የሰው ልጆችን መንፈስ ያደሰ፣ እግር ኳስን ወደ ጥበብ ያሸጋገረ የፕላኔታችን የእግር ኳስ መሲህ እንጂ!፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 4  ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here