የአዲሱ ዓመት መባቻ—እንቁጣጣሽ—በደረሰ ቁጥር ለልጆች የሚፈጥረው ደስታና ተስፋ ልዩ ነው። መስከረም ሲጠባ አበቦች ያብባሉ፤ ምድሩ በለመለመ አረንጓዴ ይሸፈናል፤ አየሩም በዕጣንና በአዲስ ተስፋ ሽታ ይሞላል። በዚህ ደስ የሚል ወቅት የ11 ዓመቷ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ያብስራ ክንዲሁን ልብም ልክ እንደ መስከረም አበቦች በአዲስ ህልም እና ሀሳብ ያብባል።
ለተማሪ ያብስራ እንቁጣጣሽ አዲስ ልብስ እና ጣፋጭ ምግብ ብቻ አይደለም። ለእሷ የእንቁጣጣሽ ጠዋት የነጻነት፣ የደስታ እና የትልቅ ህልም መግቢያ በር ነው። ጠዋት ላይ ከአበቦች የተሰራውን የአበባ ጉንጉን በአንገቷ አድርጋ ከጓደኞቿ ጋር “አበባ አየሁሽ” እያለች ቤት ለቤት ስትዘፍን፣ በ11 ዓመት የልጅነት አእምሮዋ ውስጥ በርካታ ሀሳቦች ይመላለሳሉ።
የመጀመሪያው እና ትልቁ ሀሳቧ የትምህርት አዲሱ ምዕራፍ ነው። ያብስራ በእንቁጣጣሽ ወቅት “በቀጣዩ ዓመት በአምስተኛ ክፍል ትምህርቴ በተሻለ ትጋት አጠናለሁ፤ ከክፍሌ አንደኛ ደረጃ እወጣለሁ፤ ወላጆቼንም ያደረጉልኝን ድካም በውጤቴ ካሳ እከፍላለሁ” ብላ ታስባለች። አዲሱ ዓመት አዲስ ደብተር እና እስክሪብቶ ይዞ እንደሚመጣ ሁሉ ለአእምሮዋም አዲስ እውቀት እና ብስለት ይዞ እንደሚመጣ ሙሉ በሙሉ ታምናለች።
በተጨማሪም ያብስራ ስለ ቤተሰብ እና ማህበራዊ ፍቅር ታስባለች። ቤተሰቦቿ ተሰብስበው አብረው ሲስቁ እና ሲጫወቱ ስታይ በዓለም ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ ሰላምና ፍቅር ትልቁ ሀብት መሆኑን ትረዳለች። “በአዲሱ ዓመት ሁሉም ህፃናት እንደ እኔ ደስተኛ ቢሆኑ፣ የተራቡት ቢያገኙ፣ የታመሙት ቢፈወሱ” የሚል መልካም ምኞት በትንሿ ልቧ ውስጥ ይመላለሳል።
ያብስራ ክንዲሁን በእንቁጣጣሽ ዕለት ወደፊት ምን መሆን እንደምትፈልግ ታስባለች። ሀገሯንና ወላጆቿን የምታስጠራ ታላቅ ሰው የመሆን ህልሟ በዚህ ቀን ይበልጥ ያበራል።
እንደ ያብስራ ሁሉ እያንዳንዱ ልጅ በእንቁጣጣሽ ዕለት የሚያስበው ስለ አዲስ ጅምር፣ ስለ ተስፋ እና ስለ ብሩህ እድል ነው። እንቁጣጣሽ የልጆች የመልካም ህልም ማጎልመሻ እና የአዲስ ህይወት መነሻ መስኮት ነው።
ተረት
ቁራውና ያጌጠው ጭቃ
በአንድ ወቅት በጫካ ውስጥ የሚኖር አንድ ጥቁር ቁራ ነበረ። ቁራው በራሱ ጥቁር ቀለም አይደሰትም ነበር፤ የሌሎችን አእዋፍ ያማረና የሚያብረቀርቅ ቀለም እያየ በምቀኝነት ይቆዝም ነበር።
አንድ ቀን ከከባድ ዝናብ በኋላ፣ ቁራው ከመሬት ላይ ወፍራም የሚያብረቀርቅ ጭቃ አየ። ጭቃው በፀሐይ ጨረር ሲመታ እንደ ወርቅ ያበራ ነበር። ቁራውም በሀሳቡ፣ “በዚህ ጭቃ ሰውነቴን ብቀባው ሁሉም አእዋፍ ውበቴን አድንቀው የአእዋፍ ንጉሥ ያደርጉኛል” ብሎ አሰበ።
ወዲያውኑ በጭቃው ውስጥ ተንከባሎ ክንፎቹን፣ ደረቱን እና ጭንቅላቱን በሙሉ ተቀባ። ጭቃው በሰውነቱ ላይ ሲደርቅ እጅግ ውብ እና የሚያብረቀርቅ መስሎ ታየው። ከዚያም ወደ ሌሎች አእዋፍ ዘንድ ሄዶ በኩራት “እኔ አሁን ከእናንተ በላይ ውብ ነኝ፤ ስለዚህ ንጉሣችሁ ልሆን ይገባል!” አላቸው።
አእዋፉም በውበቱ ተደንቀው ሊሰግዱለት ሲሉ ድንገት ደመና ጠቁሮ ከባድ ዝናብ ጣለ። ዝናቡ ቁራው ላይ ሲያርፍ በሰውነቱ ላይ ያለው ጭቃ ተጥቦ መሬት ላይ ወደቀ። ቁራውም እንደገና የቀደመ ጥቁር ቀለሙ ተመልሶ ታየ። ሌሎች አእዋፍ ማታለሉን ሲረዱ በሳቅ ተቀበሉት፤ እሱም በሀፍረት ወደ ጫካው ጥግ ፈረጠጠ። የተረቱ ምስጢር የሰው ልጅ ሰው ሰራሽ እና ጊዜያዊ ውጫዊ ጌጥ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ማንነቱን እና እውነተኛ ባህሪውን አክብሮ መኖር አለበት። የማስመሰል ውበት በትንሽ ፈተና አየር ላይ ይበናል።
ምንጭ፡- የኤሶፕ ተረቶች
ሞክሩ
- አይን እያለው የማያይ?
- የዓለማችን ትልቁ ጥቅጥቅ ደን ማን ይባላል?
- ግቢውን ይዞራል መሄድ ግን አይችልም?
መልስ
- እንጀራ
- አማዞን
- አጥር
ነገር በምሳሌ
-የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል ፡- አንድ ሰው ችግር ውስጥ ሲወድቅ ተፎካካሪና ነቃፊው እንደሚበዛ ያሳያል።
-“ጉዞ በሺህ ማይል የሚጀመረው በአንዲት እርምጃ ነው” (የቻይና አባባል)፡- ማንኛውም ትልቅ ግብ ወይም ስኬት የሚጀመረው ከትንሽ የመጀመሪያ ጥረት ነው፡፡
-የሰው ወርቅ አያደምቅ፡- በሰው ሀብትና ስኬት ከመመካት የራስን ነገር በጥረት ማሳደግ እንደሚሻል ያሳያል።።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


