የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት አብርሐም ሊንከን “ዛፍ ለመቁረጥ ስድስት ሰዓት ቢሰጠኝ የመጀመሪያዎቹን አራት ሰዓታት መጥረቢያዬን በመሳል አሳልፋለሁ፡፡ ምክንያም በትግበራ ላይ ከምናጠፋው ጊዜ በላይ ለዝግጅትና ለማቀድ የምናወጣው ጊዜ የወደፊቱ ሥራችንን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ይረዳልና” በማለት ለማንኛውም ሥራ ውጤታማነት ቀድሞ በእቅድ መዘጋጀት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ በቢሮ ደረጃ የቢሮ አማካሪ ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ ዕቅድ ዛሬ ላይ ሆኖ ወደ ፊት ሊደረስባቸው የሚታሰቡ ግቦችን ከአሁኑ በማየት እና ወደዚያ ለመድረስ የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ የሚቀየስበት እንዲሁም አስፈላጊውን ሀብት በመመደብ ወደ ተግባር የሚለወጥበት የተቀናጀ ሂደት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በዶመኒካን ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጌይል ማቲውስ (ዶ/ር) ጥናት እንደሚያረጋግጠው ደግሞ ግባቸውን በግልጽ የሚጽፉ ሰዎች ዝም ብለው በአዕምሯቸው ብቻ ከሚያስቡት በላይ ግባቸውን ማሳካት የመቻል እድላቸው 42 ከመቶ ይጨምራል። ዕቅድን በወረቀት ላይ ማስፈር የአዕምሮን ትኩረት ለመሰብሰብ እና የመጀመሪያውን የተግባር እርምጃ ለመውሰድ ትልቅ የሥነ-ልቦና ኀይል አለው።
የእቅድ ማውጣት ዓላማ በመሰረቱ ትርጉም ያላቸው ግቦችን የማስቀመጥ እና እነሱን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመንደፍ ሆን ተብሎ የሚከናወን ሂደት ነው። ሰዎች በየቀኑ በሚከሰቱ ችግሮች ላይ ብቻ ምላሽ በመስጠት ከመኖር ይልቅ፣ ነገሮችን አስቀድሞ በማቀድና በመቆጣጠር እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። እንደ ሥራ፣ ጤና፣ ገንዘብ እና ግንኙነቶች ባሉ የተለያዩ ዘርፎች ግልጽ ዓላማዎችን በመለየት እቅድ ማውጣት እጅግ ሰፊ እና አስፈሪ የሚመስሉ ምኞቶችን ወደ ሚተዳደሩ እና ተግባራዊ ሊሆኑ ወደ ሚችሉ ደረጃዎች ይለውጣቸዋል።
ወጣት ማህሌት ዜና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የዘንድሮ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪ ናት፡፡በየዓመቱ አዲስ ዓመት ሲጀምር ቀድማ እቅድ በማውጣት እንደምትጀምር ተናግራለች፡፡ በብዛት የምታቅደው “ያለፈው ዓመት ድክመቴ ምን ነበር? በማለት ያሰብኋቸውን ጉዳዮች አስተካክዬ እና አሻሽዬ ለመቀጠል በማሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ ምንም ነገር ለማድረግ ስፈልግ ራሴ አደርጋለሁ፣ ጊዜን በአግባቡ እጠቀማለሁ፣ለሰዎች ደስታ ብቻ ብዬ አላግባብ ጊዜዬን አላጠፋም፣ ቀድሜ አደርገዋለሁ ብዬ ያላሰብኩትን ነገር ባጋጣሚ አላደርግም… የሚሉ ሀሳቦችን በፅሑፍ ለአዲስ ዓመት አቅዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ሀሳብ ሳምንት ሳይዘልቅ በድንገት ነገሮችን በስሜታዊነት ያላሰብሁትን ነገር በማድረግ፣ በመግዛት ፣ሰዎች የሆነ ቦታ መሄድ ሲፈልጉ እንኳን ያለምንም ሥራ እንሂድ ካሉኝ አብሮ በመሄድ ጊዜ እና ገንዘቤ ያለምንም ዕቅድ ይባክናል፡፡ በዚህም ምንም ነገር በጀመርሁበት መንገድ ነገሮች ስለማይቀጥሉ ተመልሸ ወደ ነበርሁበት ሕይወት የመመለስ አባዜ በመኖሩ በእቅድ መመራት እንደ ማልችል መገንዘብ ችያለሁ” በማለት ራሷን ትወቅሳለች፡፡
በዓመቱ መጀመሪያ ባወጡት እቅድ መሠረት የሚጓዙ ሰዎች ውጤታማ ይሆናሉ ብላ እንደምታምን የምትገልፀው ማህሌት ለዚህ ውጤት ለመብቃት ግን ባወጡት እቅድ የመመራት ልምድ ቀጣይነት የሚኖረው ገና ከወጣትነት ጀምሮ ማሳደግ ሲቻል እንደሆነ ታምናለች፡፡
ማሕሌት እንደ አለፉት ዓመታት በ2019 አዲስ ዓመት ዋናው ዕቅዷም በዘፈቀደ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በዕቀድ ብቻ በመመራት አቋሟን ላለመቀያየር እና ላለማቋረጥ አስባለች፡፡ “ሰዎች አስቀድመው ዕቅድን የሚያቅዱ ከሆነ ታዲያ ዕቅዶቹ ለመተግበር ለምን ይቸገራሉ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባል?” በማለትም ያለፉት ዕቅዶቿ ሳይሳኩ የቀሩበትን ምላሽ ትሻለች፡፡
ዶ/ር ሙሉቀን እንደሚገልፁት በርካታ እቅዶች በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ሳይሳኩ የሚቀሩባቸው ምክንያቶች በዋነኝነት ከእቅድ ዝግጅት፣ ከሀብት ድልድል እና ከአፈጻጸም ክፍተቶች ጋር የተያያዙ ናቸው።
አንድ እቅድ ከመነደፉ በፊት ውስጣዊ አቅምን (ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን) እንዲሁም ውጫዊ ሁኔታዎችን (መልካም እድሎችን፣ ተግዳሮቶችን እና ስጋቶችን በጥልቀት መፈተሽ የግድ ይላል። እነዚህን ያላገናዘበ እቅድ ከመጀመሪያው ውድቀት የተጻፈበት ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ
ተጨባጭ ያልሆነ የግብ ቀረጻ
(አቅምንና ነባራዊ ሁኔታን) ያላገናዘበ፣ በቀላሉ ሊደረስበት የማይችል ምናባዊ ግብ ማስቀመጥ እቅዱ ሳይሳካ እንዲቀር ያደርጋል። ብዙዎች እቅድ ማውጣትን በራሱ እንደ ግብ የመቁጠርና ሰነዱ ከተዘጋጀ በኋላ ጥለው የመርሳት (የሼልፍ ሲሳይ የማድረግ) ዝንባሌ ይታይባቸዋል።
ማንኛውም ግብ ስኬታማ እንዲሆን ጊዜን፣ የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይልን፣ ተቋማዊ ዝግጁነትን እንዲሁም በቂ የፋይናንስ አቅምን ይጠይቃል።እነዚህ ሀብቶች ሳይሟሉ ሲቀሩ እቅዶች ይደናቀፋሉ። የክትትል፣የድጋፍ እና የአፈጻጸም ክፍተቶች የተቀመጠውን ሥራ በተገቢው ሰዓትና ጥራት አለማስፈጸም፣ የአመራሩና የፈጻሚው የትኩረት ማነስ፣ በየደረጃው ደግሞ ክፍተቶችን እየሞሉ የሚሄዱበት ተከታታይ ድጋፍና ክትትል አለመኖር ለእቅዶች አለመሳካት ትልቅ ምክንያት ነው።
በሌላ በኩል በሃርቫርድ ዩንቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው እውነተኛው ዓለም ብዙውን ጊዜ በአዳዲስ ክስተቶች እና ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ይናወጣል፤ ይህም ዕቅዶች እንዲከሽፉ ያደርጋል። ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ፣ መረጃዎችን ብንጠቀም እና ዕቅዶችን በጥንቃቄ ብናዘጋጅም ያልተጠበቁ ሁኔታዎች መከሰታቸው አይቀርም። ለውጤታማ የዕቅድ አመራር እና ዕቅድ ዝግጅት፣ የዓለማችንን ተፈጥሯዊ ያልተጠበቀ ሁኔታ መረዳት ወሳኝ ነው።
ጥናቱ ግለሰቦች ጠንካራ የሕይወት እቅድ ማውጣት እና በዛ መመራት ከቻሉ የሚሄዱበትን አቅጣጫ፣ የሚኖሩለት ዓላማን እና መዋቅራዊ ቅርፅ ይሰጣቸዋል፤ ከረቂቅ ምኞት ወደ ተጨባጭ እውነታ የሚያሸጋግር ድልድይ ሆኖም ያገለግላል። ሳይንሳዊ መርህን ተከትሎ የተነደፈ እቅድ ከሌለ የሰው ልጅ ጥረት ብዙውን ጊዜ ያለ ግብ ወደሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይበተናል፡፡ ይህም የረጅም ጊዜ ስኬቶችን ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በግለሰብ ደረጃ የሚታቀዱ እቅዶች የግለሰቡን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው። የሕይወት እቅድ ማውጣት ቁልፍ ጥቅሞች በግልጽነት እና በትኩረት የተደራጀ የእቅድ ውሳኔዎችን በማድረግ ሂደት የሚፈጠረውን ድካም ያስወግዳል። በየቀኑ፣ በየሳምንቱ ወይም በየዓመቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ማወቅ ደግሞ ውስን የሆነውን ጊዜ እና ጉልበት ከፍተኛ ዋጋ ወደ ሚያመጡ ተግባራት ለመምራት ይረዳል።
ጆን ሌኖን የተባለ ምሁር “ሕይወት ማለት አንተ ሌላ ዕቅድ በማውጣት ላይ ሳለህ የሚከሰተው ነገር ነው። ዕቅድ ስናወጣ የሕይወትን ያልተጠበቁ ሁነቶችና ተለዋዋጭ ባህሪያት ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። ይሄ ሲሆን እቅድ ማውጣት ማለት የወደፊቱን ጊዜ እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ አስቀድሞ መተንበይ ማለት እንዳልሆነ እንድንረዳ ያደርገናል፤ ዕቅድ ለግል እድገት ሆን ተብሎ የተነደፈ ማዕቀፍ መፍጠር ማለት ነው። ግልጽ አቅጣጫን ከተለዋዋጭ አፈጻጸም ጋር በማጣመር፣ ግለሰቦች የሕይወትን ውስብስብ ነገሮች በዓላማ እና በተከታታይነት መጋፈጥ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል።
ለዛ
- “ለማቀድ ከተሳነህ ለመውደቅ እየታቀድክ ነው። ዕቅድ አልባነት በራሱ ወደ ውድቀት የሚያመራ ውሳኔ መሆኑን ያመላክታል፤ ስኬት በድንገት የሚመጣ ሳይሆን በቅድመ-ዝግጅት የሚገነባ መሆኑን ያጎላል።” ቤንጃሚን ፍራንክሊን
- “ያለ ዕቅድ የተቀመጠ ግብ ምኞት ብቻ ነው። ዓላማ ወይም ህልም ብቻውን ፍሬ አያፈራም፤ ህልምን ወደ እውነታ ለመቀየር ግልጽ የሆነ የትግበራ መንገድ (ዕቅድ) ያስፈልጋል።” አን ቶውን ሴንት–ኤክዙፔሪ
- “ማቀድ ማለት ወደ ፊት የሚከሰተውን ነገር አሁን ላይ የማምጫ መንገድ ነው፤ በዚህም አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ ትችላለህ።”
አላን ሐይክ
- “ዕቅድ ማለት ወደፊት ምን እንደምናደርግ መወሰን ሳይሆን ነገ የተሻለ እንዲሆን ዛሬ ምን ማድረግ እንዳለብን መወሰን ነው።” ፒተር ድረከር
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


