እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው በየቀኑ አምስት ስኒ እና በላይ ቡና የሚጠጡ ሴቶች ዝቅተኛ የአጥንት ውስጥ “ሚንራል” ጥግግት እንደሚስተዋልባቸው እና በጤናቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጸ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በአውስትራሊያ የፍሊንደርስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አስር ሺህ በሚደርሱ ዕድሜያቸው 65 እና በላይ በሆናቸው ሴቶች ላይ የናሙና ምርምር አካሂደዋል፡፡ በተጨማሪም ከዓለማችን ተጠቃሽ የጤና ችግር በሆነው “ኦስቲኦፖሮሲስ” ከ50 ዓመት እድሜ በላይ በሆናቸው በሚሊዬን ለሚቆጠሩ ሴቶች ቡና እና ሻይ መጠጣት ለአጥንት መስነፍ እና መሰበር እንደሚዳርግ ለማረጋገጥ ቀደም ብሎ ለተደረገ ምርምር የተሰበሰበ መረጃን በግብአትነት ተጠቅመውበታል፡፡
በዩኒቨርስቲው ተባባሪ ኘሮፌሰር ኢኑሊዩ በየእለቱ ሁለት እና ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት በአጥንት ጤና ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ አነስተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ በተቃራኒው በየእለቱ አምስት ስኒ እና በላይ የሚጠጡ ሴቶች ግን በአጥንት ግንባታ እና ለ (ካልሲዬም) አጥንት ስሪት ዋነኛው ንጥረ ነገርን መመጠጥ ሊያደናቅፍ እንደሚችል ነው ያሰመሩበት፡፡
ከምርምሩ የተገኙ እውነታዎችን መሰረት አድርገውም ተባባሪ ኘሮፌሰሩ ሻይ አዛውትሮ መጠጣት በኋለኛው ማለትም በአዛውንትነት እድሜ ላይ የአጥንት ጤናን ሊደግፍ እንደሚችል ጠቁመው ቡናን አብዝቶ መጠጣት ግን ጐጂ መሆኑን በመግለፅ ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019ዓ.ም ዕትም


