በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ከማካንዚ በስተሰሜን በሚገኝ የውኃ ማጠራቀሚያ ኃይቅ ወይም ግድብ ላይ በሀምሌ ወር አጋማሽ የታየ ደን የለበሰ ደሴት በነሀሴ ወር መግቢያ ከእይታ መሰወሩን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡
የብሪትሽ ኮሎምቢያ የዉኃ ሀብት ቃል አቀባይ ቦብ ጋመር መጀመሪያ አካባቢ የተለቀቁ ምስሎች በ “ኤ አይ” የተቀናበሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢጠረጥሩም በኋላ ላይ ስፋቱ 105,486 ስኩዌር ጫማ የተለካ በደን የተሸፈነ ደሴት ሀምሌ 13/2018 ዓ.ም ወይም /ጁላይ 20/2026/ እ.አ.አ ከሳተላይት በተወሰደ ምስል መታየቱን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ሁለት ሳምንታት ዘግይቶም ቀጣናውን ሲቃኙ ባለሙያዎች የጠፋውን ደሴት ዳግም መመልከት መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ቦብ ጋመር የደሴቱን መጥፋት እና በድጋሚ መታየት አስመልክተው በሰጡት ሙያዊ አስተያየት ደሴቱ ከታቆተው ኃይቅ ዳርቻ ተገንጥሎ የወጣ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ በዳርቻው ይዞት የመጣውን ዓፈር እና በጊዜ ብዛት የሚበሰብሱ ዛፎች እና ቅጠላ ቅጠል ስር እንዲይዝ እያስቻሉት የሀይቁ ውኃ መጠኑ ሲጨምር ዳርቻውን ለቆ መሀል ላይ እየተንሳፈፈ፣ የውኃ ከፍታ መጠኑ ሲቀንስ ከዳርቻው ጋር ተገናኝቶ በመመሳሰል የጠፋ እንደሚመስል ነው በማጠቃለያነት ያስረዱት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 4 ዓ.ም ዕትም


