ይግባኝ

0
43

ማንኛውም ሰው ያለውን ችግር ወደ ፍርድ ቤት አቅርቦ ዳኝነት ሲጠይቅ ፍርድ ቤት አስፈላጊውን መረጃ ሰብስቦ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ከፍርዱ  በኋላ ደግሞ በሚሰጠው ውሳኔ  ሰዎች ቅሬታ ካደረባቸው አቤት የሚሉበት የተዋረድ የይግባኝ ሥርዓት አለ፡፡

ይህን በተመለከተ የሕግ ባለሙያዋን ወ/ሮ ትዕግስት ጣሰውን አነጋግረናል፤ የይግባኝ ሥርዓት መዘርጋቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሱት የሕግ ባለሙያዋ ይግባኝ በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግጋት የተዘረጋ መብት እንደሆነ ነው የሚገልፁት፡፡

ይግባኝ ማለት በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ጉዳዩን ባየው ፍርድ ቤት በተሰጠ ፍርድ /ውሳኔ/ ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው ወገን ቅሬታውን ይግባኝ እንዲቀበል በሕግ ለተመለከተው ከፍ ላለው ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ነው፤ ይህም የተሰጠውን ፍርድ፣ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ እንዲሰረዝ፣ እንዲሻሻል፣ እንዲሻር የሚጠየቅበት ሥርዓት ነው። ጉዳዩ ደግሞ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320 (1) የተመለከተ እንደሆነ ባለሙያዋ ይገልፃሉ፡፡

ይግባኝ መቼ ይባላል?

እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ማብራሪያ ይግባኝ የሚቀርበው የሥር (የታችኛው) ፍርድ ቤት የቀረበለትን ጉዳይ መርምሮ በሚሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ላይ እንደሆነ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320 ንኡስ አንቀፅ (1) ተደንግጓል፡፡

የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320 ንኡስ አንቀፅ (2) እና (3) መሠረት ጊዚያዊነት ባላቸው ትዕዛዞች ላይ ማለትም ቀጠሮ ሲወሰን ወይም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ወይም የጠበቃን እርዳታ ስለማግኘት ወይም ከጠበቃ ጋር ስለመቅረብ ወይም የዳኝነት ሳይከፈል በነፃ ለመክሰስ በሚቀርብ ጥያቄ ላይ በሚሰጠው ትዕዛዝ ይግባኝ መቅረብ የሚችለው በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በአንድ ላይ ነው፤ ነጥሎ ይግባኝ ማቅረብ አይፈቀድም፡፡

ሆኖም በልዩ ሁኔታ ማለትም ማንም ሰው እንዲታሰር ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ወይም በእጅ ያለን ንብረት ለሌላ ወገን እንዲተላለፍ በተሰጠ ትዕዛዝ እንዲሁም ያላግባብ ታስሪያለሁ ይግባኝ ይታይልኝ ሲል የቀረበ አቤቱታ ተቀባይነትን ሲያጣ ይግባኝ ሊቀርብ ይችላል።

የፍትሐብሔር ይግባኝ

የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 327 የይግባኝ ማመልከቻ ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት ደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት የይግባኝ ማመልከቻ ይግባኝ የቀረበበትን ፍርድ ቤት ስምና የሚያስችልበትን ቦታ፣ የይግባኝ ባዩና የመልስ ሰጪው ስምና አድራሻ፣ ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት ስም፣ ፍርዱ የተወሰነበትን ቀንና የመዝገብ ቁጥር፣ ለይግባኙ ምክንያት የሆኑ ነገሮች፣ በይግባኙ እንዲታረም የሚፈለገውን የነገር ዝርዝርና የሚጠይቀው ዳኝነት ዓይነት መካተት አለበት፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 323 (2) መሠረት ይግባኝ የሚቀርበው ይግባኝ የሚባልበት ጉዳይ ላይ ውሳኔ በተሰጠ በ60 (ስልሳ) ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ይግባኝ በ60 ቀን ውስጥ ያልቀረበ ከሆነ ይግባኝ ባይ ይግባኝ የማቅረብ መብቱን ያጣል፡፡

በሌላ በኩል የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ያለፈበት ሰው ይግባኙን በጊዜው ለማቅረብ ያልቻለበትን በቂ ምክንያት ከማስረጃዎች ጋር አያይዞ የፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚችል በሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 325 ተደንግጓል። ይህ የፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም ይግባኙን በመለሰው በ10 ቀናት ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡

በቂ ምክንያት ለሚለው በሕጉ የተሰጠ ዝርዝር ነገር የሌለ በመሆኑ የምክንያቱ በቂነት እንደየሁኔታው በፍርድ ቤቱ የሚመዘን ይሆናል፡፡

ሆኖም አመልካቹ ይግባኙን በጊዜ ያላቀረበው በአመልካቹ ጠበቃ ወይም ነገረ ፈጅ ወይም በወኪሉ አለመቅረብ ምክንያት ከሆነ በቂ ምክንያት ተብሎ አይወሰድም፤ የይግባኝ መዝገብ እንዲከፈትም አይፈቀድም፡፡ ይህም በሥርዓት ሕግ ቁጥር 326 ንኡስ አንቀፅ (2) ተደንግጓል፡፡

ይግባኝ ከቀረበ በኋላ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ነገሩ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የሚያቀርቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ የሰጠበትን የመዝገብ ግልባጭ መርምሮ ፍርዱ ጉድለት የሌለበት መሆኑን ከተረዳ መልስ ሰጪውን ሳይጠራ ይግባኙን ዘግቶ አቤት ባዩን ሊያሰናብት ይችላል፡፡

በአንፃሩ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን የተቀበለ እንደሆነ ይግባኙ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ መልስ ሰጪው እንዲቀርብ መጥሪያውንና የይግባኝ ማመልከቻውን ግልባጭ ይልክለታል፡፡ በቀነ ቀጠሮው ሳይቀርብ ቢቀር ይግባኙ በሌለበት የሚሰማ መሆኑን በመጥሪያው ላይ ያስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለጉዳዩ እልባት እስከሚሰጥ ድረስ የሥር ፍርድ ቤት ፍርድ አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ሊያዝ እንደሚችል በሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 332 ላይ ተደንግጓል፡፡ ይህ የሚሆነውም ይግባኝ ከመታየቱ በፊት ፍርድ ቢፈፀም ከፍ ያለ ጉዳት የሚደርስ መሆኑ ሲታመን፣ ፍርድ እንዲታገድ የቀረበው ማመልከቻ ሳይዘገይ የቀረበ ሲሆን እና አልመካቹ ስለ ፍርድ አፈፃፀም በቂ ገንዘብ ወይም በቂ መያዣ ማስቀመጡ ሲረጋገጥ እንደሆነ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 335 ተደንግጓል፡፡

በተመሳሳይ የይግባኝ ክርክር ሂደት በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩን ባየው ፍርድ ቤት ያልተነሳ አዲስ ክርክር በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አንስቶ ለመከራከር እንደማይቻልም በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 329 (1) ተደንግጓል፡፡

ተጨማሪ ማስረጃን በሚመለከት ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አዲስ ማስረጃ ማቅረብ አይፈቀድም፡፡ በልዩ ሁኔታ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 345 መሠረት ይግባኝ የቀረበበትን ክርክር የፈረደው ፍርድ ቤት መቀበል የነበረበትን ማስረጃ ያለበቂ ምክንያት ሳይቀበል ከቀረ ወይም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት ወይም ተገቢ መስሎ በታየው በማናቸዉም ምክንያት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብና እንዲሰማ መፍቀድ ይችላል። ፍርድ ቤቱ መሰል ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ማስረጃው እንዲቀርብ የተደረገበትን ምክንያት በመዝገቡ ላይ ማስፈር ጠበቅበታል፡፡

ይግባኙን ለመስማት በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ክርክሩ በሚሰማበት ጊዜ ይግባኝ ባዩ ያቀረበውን ይግባኝ የሚደገፍበትን ነገር ለማስረዳት አስቀድሞ ክርክሩን ይጀምራል፡፡ ይግባኝ ባዩ ላሰማው ክርክር መልስ ሰጪው የመከላከያ መልሱን ይሰጣል፡፡ ቀጥሎም መልስ ሰጪው ላቀረበው መከላከያ ይግባኝ ባዩ መልስ መስጠት ይችላል፡፡

በመጨረሻም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና እንደ አስፈላጊነቱም ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የወሰነውን ፍርድ ቤት መዝገብ ከመረመረ በኋላ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በውሳኔውም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ሊያፀና፣ ሊያሻሽል፣ ሊሽር ወይም የበታች ፍርድ ቤት መያዝ ያለበትን ጭብጥ ሳይዝ ወይም ፍሬ ነገሩን ሳይመረምር ቀርቶ ከሆነ የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ጭብጥ ይዞ ወይም መመርመር ያለበትን ፍሬ ነገር ለይቶ እንዲመረምር በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 343 መሠረት ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት መልሶ ሊልክ ይችላል፡፡

የወንጀል ጉዳይ ይግባኝ

ባለሙያዋ ወ/ሮ ትዕግስት ያብራሩት ሌላው ጉዳይ የወንጀል ይግባኝን በተመለከተ ነው፤ እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ የወንጀል ጉዳይ ይግባኝ ክርክር የሚደረገው የወንጀል ተጎጂን በመወከል በዐቃቤ ሕግ እና ወንጀል በመፈፀም በተጠረጠረ ተከሳሽ መካከል ነው፡፡

ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሽ ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል። ይህም ቅሬታ በተከሳሽ የሚቀርብ ከሆነ የተወሰነብኝ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተገቢ አይደለም ወይም የተላለፈብኝ ቅጣት ተገቢ አይደለም ወይም ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ሊቀርብ ይችላል፤ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ ተከሳሽ በነፃ በመለቀቁ ወይም ዝቅተኛ ቅጣት በመወሰኑ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ማለት ይችላል። እንዲሁም ከሳሽም ይሁን ተከሳሻ የዋስትና መፈቀድ ወይም መከልከል ላይ፣ የዋስትና መጠን መብዛት ወይም ማነስ ላይ ይግባኝ ሊሉ ይችላሉ።

ይግባኝ ማለት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 184 በተደነገገው መሠረት ቀጠሮ መስጠት ወይም አለመስጠት (ሥነ – ሥርዓት ሕግ ቁጥር 94) ወይም ስለሚቀርብ መቃወሚያ (ሥነ – ሥርዓት ሕግ ቁጥር 131) ወይም ማስረጃን ስለ መቀበል ወይም ስላለመቀበል (ሥነ – ሥርዓት ሕግ ቁጥር 146) ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ማለት አይቻልም።

የሕግ አንቀጽ

ዋና ዋና የይግባኝ ሕግ አንቀጾች

  • የይግባኝ መብት: በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት ማንኛውም ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ቅር የተሰኘ አካል ከፍ ላለ ፍርድ ቤት የማንነት እና የውሳኔ ይግባኝ የመጠየቅ መብት አለው።
  • የይግባኝ ጊዜ: በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320 መሠረት ይግባኝ የሚቀርብበት የተወሰነ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል።
  • የይግባኝ ማስፈቀጃ: በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 323 መሠረት ይግባኝ ሊቀርብባቸው የሚገቡ ውሳኔዎች እና ማስፈቀጃ የሚጠይቁ ጉዳዮች ይገለፃሉ።

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here