የሁላ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ጥብቅ ቀጣና በእስራኤል በገሊላ ክልል በላይኛው ቀጣና ነው የሚገኘው፡፡ ቀጣናው እስከ 1950ዎቹ እ.አ.አ ረግረጋማው ዝቅ ያለ ስፍራ የወባ ትንኝ መፈልፈያ ሆኗል በሚል እንዲደርቅ ተደርጐ ነበር፡፡ ከእለት እለትም በረግረጋማው ስፍራ ዙሪያውን ኗሪዎች ሰፍረው በእርሻ ስራ ሲተዳደሩበት ቆይተዋል፡፡
በ1990ዎቹ መግቢያም ዳግም ሸለቆው ውኃ አቁሮ ሊያገግም ችሏል፡፡ በቀጣናው ኗሪዎች መስፈራቸውን እና ተፈጥራዊው ሸለቆ መታረሱን የሞገቱ የአገሬው ተወላጆች ህብረት እና ድምፃቸው መሰማቱ የተፈጥሮ ሀብት ቁጥጥር ድርጅት እንዲመሰረት ፈር ቀዷል፡፡
ዳግም ያገገመው 350 ሄክታር በተለካው ውኃ ባቋተው የሁላ ሸለቆ መካከለኛ ስፍራ በመኽር እና ፀደይ ወቅቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓእዋፍ – ክሬን፣ ፔሌካን፣ ኮርማንት እና ኤግሬትን ጨምሮ የበርካታ ዝርያዎች መናኽሪያ ሆኗል፡፡
ከእፅዋት በኃይቁ ዳርቻ እና ረግረጋማ ቀጣና “ፓፒረስ” እና “ዋተርሊሊ” የውኃ ላይ ተሳቢ አበባማ ሀረግ የጐብኚን ዓይን የሚስቡ ጌጥ ሆነው ይስተዋላሉ፡፡
በአካል ግዝፈት ካላቸው የዱር እንስሳት የዱር አሳማ፣ የውኃ ዳር ጐሽ እንዲሁም በአጥር ተከልለው የሚጠበቁ “ፋሎ ዲር” ከፋርስ ወደ ቀጣናው እንዲለምዱ የተደረጉ የአጋዘን ዝርያዎች መኖራቸውም ነው የተጠቀሰው- በድረገፆች፡፡
በጥብቅ ቀጣናውም በ2006 እ.አ.አ የጐብኚዎች ማእከል ተከፍቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጐብኚዎች ተዟዙረው የሚቃኙበት ሰገነት እና ተንሳፋፊ ድልድይ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ከተሰሩት አበይት ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቱሪስት እስራኤል ድረ ገጽ፣ ኢኤን ፓርክ ዶት ኦርግ፣ ማይ እስራኤል ጋይድ ድረ ገጽን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


