“የወደብ አልባነት ዳፋ የእያንዳንዱን ዜጋ ቤት ያንኳኳል”

0
336

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነ – ዜጋና ስነ- ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ሀሳቡ ተስፋ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም በገቨርናንስ ጥናት የትምህርት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ባለሙያ ናቸው። በትኩረት መስካቸውና በስራ ዝንባሌአቸውም በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ በጂኦፖለቲክስ፣ በአፍሪካ ቀንድና በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ እና በተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርት የመስጠትና የምርምር ሥራዎችን የመስራት ሰፊ ልምድ አላቸው።

ከመምህር ሀሳቡ ተስፋ ጋር በምናደርገው ቆይታችን፣ የኢትዮጵያ የወደብ አልባነት ጉዳይ ከብሔራዊ ደህንነትና ምስጢር፣ ከታሪካዊ እውነታዎች፣ ከጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖዎችና ከዜጎች የእለት ተእለት የኑሮ ውድነት ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት በጥልቀት እንዳስሳለን።

በተጨማሪም ሀገራችን የባህር በር ጥያቄዋን በሰጥቶ መቀበል መርህና በሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመመለስ ልትከተላቸው በሚገቡ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ላይ በስፋት የምንወያይ ይሆናል። ከመምህሩ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

መልካም ንባብ!

የባሕር በር ለአንዲት ሀገር የሚኖረውን ጠቀሜታ እና የባሕር በር ማጣት የሚኖረውን ጉዳት ቢያብራሩልን?

የባሕር በር ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ውይይት ርዕስ ብቻ አይደለም፤ የሀገሪቱን ታሪካዊ መብት፣ የብሔራዊ ደህንነት ምስጢር ጥበቃና የዘላቂ ህልውና መረጋገጥን እውን የሚያደርግ የሉዓላዊነታችንና የህልውናችን መሠረት የሆነ ግዙፍ አገራዊ አጀንዳ ነው።

የአንዲት ሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት የሚረጋገጠው ስትራቴጂያዊ መረጃዎቿንና የደህንነት ምስጢሮቿን በጥብቅ የመጠበቅ አቅሟ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ምክንያት ወደ ሀገር የምታስገባቸውም ሆኑ የምታስወጣቸው ስትራቴጂያዊ ቁሳቁሶች፣ ወታደራዊ፣ ቴክኖሎጂያዊና ኢኮኖሚያዊ እቃዎች በሙሉ በሌሎች ጎረቤት ሀገራት የፍተሻ፣ የብርበራና የምርመራ ማዕቀፍ ውስጥ ለማለፍ ይገደዳሉ።

“በሌላ ሀገር ሳሎን የሚያልፍ ሰው የተሰወረ ምስጢር ሊኖረው አይችልም” እንደሚባለው፣ “ምን አለን? ምንስ የለንም?” የሚለው ሀገራዊ ጥንካሬና ስስ ብልታችን ለጠላቶቻችን ጭምር አሳልፎ የመሰጠት ከፍተኛ አደጋ አለው።መረጃዎቻችን ለባላንጣዎች የመሸጥ ስጋታቸው የጎላ በመሆኑ፣ በዲፕሎማሲው ዓለም ትልቅ ዋጋ ያላቸውን “ድንገተኝነትና አይገመቴነት” የመደራደር አቅማችንን ያከስመዋል።

በሌላ በኩል የወደብ አልባነት መራራ ዳፋ ቀጥታ እያንዳንዱ ዜጋ ቤት የሚያንኳኳ ነው። አሁን ለታየው የኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ረጅም የሎጂስቲክስ መስመር በመጠቀማችንና ለጎረቤት ሀገራት የምንከፍለው ከፍተኛ የትራንዚትና የጉምሩክ ክፍያ ነው። ነጋዴው ይህን ወጪ ቀጥታ ወደ ሸማቹ ስለሚያስተላልፈው የወደብ አልባነት የመጀመሪያውና ዋናው ሰለባ እራሱ ዜጋው ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ ምክንያት የሆኑባት ክስተቶችና የቀጠናው ስትራቴጂያዊ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት በታሪካዊ ሁነቶችና በክልላዊ ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች ውስጥ ጥልቅ መሠረት ያለው ነው። በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራት ከዓለም ደሃ ሀገራት ተሰላፊ የሆኑት የፀጋ እጥረት ኖሮባቸው ሳይሆን፣ ፀጋቸውን በጋራ ከመጠቀም ይልቅ አንዳንዶቹ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ በመሆናቸው ነው።

በተለይም ኤርትራና ኢትዮጵያ ያላቸው ታሪካዊ፣ ባህላዊና የህዝብ አንድነት ተሳስረው ከድህነት ለመውጣት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ ኤርትራ ነጻ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻ ከማስፈጸም ይልቅ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆና በመቀጠሏ ሂደቱ ተጎትቷል። የኤርትራ ህዝብ ፍላጎትና ዘላቂ ጥቅም ከኢትዮጵያ ጋር የተዋሃደ ቢሆንም በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ምክንያት ሀገሪቱ ነፃ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዳይኖራት ተደርጋለች።

በተጨማሪም የአፍሪካ ቀንድ እጅግ ከፍተኛ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ፉክክር የሚካሄድበት ቀጠና በመሆኑ፣ የዓለም ሀያላን ሀገራትና የባህር ኃይሎች ኃይላቸውን በማስፈር ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ በጅቡቲ ውስጥ እርስ በእርስ ባላንጣ የሆኑ በርካታ የውጭ ኃይሎች የጦር ሰፈራቸውን መስርተዋል። በእነዚህ ባላንጣ ሀገራት መካከል ግጭት ቢፈጠር ቀድማ የምትዳውና የውጭ መውጫ በሩን የምታጣዉ ኢትዮጵያ ናት።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪክ፣ ከፖለቲካ፣ ከደኅንነትና ከዕድገት አንጻር እንዴት ይታያል?

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከነዚህ አራቱም አቅጣጫዎች ፅኑ መሠረት ያለውና የማይደራደሩበት የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡

ከታሪክ አንጻር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1940ዎቹ መጨረሻ የተከናወኑ ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች እንኳ የኤርትራን ጉዳይ ሲወስኑ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት እንዲሁም የቀጠናውን ዘላቂ ሰላም ያማከለ ነበር። ኢትዮጵያን የመሰለች ግዙፍ ሀገር በወደብ አልባነት ታስራ እንድትቀጥል ማድረግ ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም በጎ አበርክቶ የለውም።

ከፖለቲካና ደኅንነት አንጻር ስንመለከተዉ የወደብ አልባነት አደጋ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በተግባር የታየ ነው፤ ኤርትራ የኢትዮጵያን ግዛት ለሁለት ዓመታት ተቆጣጥራ ለመቆየት የቻለችበት አንዱ ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ አማራጭ የመውጫ መስመሮችን እስከምታዘጋጅ ድረስ በገጠማት የሎጂስቲክስ መስተጓጎል ምክንያት ነው። ከኛው ከሀገር የተቀነሰች፣ በወታደራዊመ ሆነ በኢኮኖሚያዊ አቅም አነስተኛ የሆነችው ኤርትራ እንኳ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ደፍራ ለመቆየት የቻለችው በዚሁ የመስመር መዘጋት ሳቢያ ነው።

የባሕር በር ማጣት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ምህዳር ያፍነዋል። በመሆኑም የባሕር በር ማግኘት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገር ሆኖ የመቀጠልና የመንበርከክ ወይም የመጥፋት ወሳኝ አጀንዳ በመሆኑ በአገር ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ እንዲመለስላት ልትከተላቸው የሚገቡ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ምንድናቸው?

ኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ያሏት ሆና ሳለ፣ ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነትና አብሮ ማደግ ስትል “ሰጥቶ መቀበል” መርህን የተከተለ ሰላማዊ የመፍትሔ ሀሳብ አቅርባለች።

ኢትዮጵያ የባሕር በርን በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ፍላጎት ማሳየቷ እጅግ የሚደነቅ፣ ቅቡልነት ያለውና የበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ነው። ይህም አካሄድ ክልላዊ የኢኮኖሚ ውህደትና ዘላቂ ወዳጅነትን የሚያመጣ ሰላማዊ መንገድ ነው። የቀጠናው ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም የሚረጋገጠውና ድህነት  የሚሸነፈው በሴራ፣ በብቸኝነትና በበዛ ውጥረት ሳይሆን በጋራ ልማት፣ በሰጥቶ መቀበልና በጠበቀ የኢኮኖሚ ትስስር ብቻ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም የዚሁ ፍትሃዊ፣ ታሪካዊና ዘላቂ የቀጣናው ህልውና ማረጋገጫ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል።

ሊነሱ ይገባል የሚሏቸው ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ይኖራሉ?

ዋናውና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የህዝባችንን የጋራ ህልምና አንድነት የተመለከተው ነው። የባህር በር ጥያቄ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ የአንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ህልምና ጥያቄ ሊሆን ይገባዋል።

ዜጎች ከሀገር ህልውና በታች ባሉ ልዩ ልዩ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳ በሀገር ደህንነትና ዘላቂ ህልውና ላይ ግን በምንም መልኩ የልዩነት መስመር ሊሰመር አይገባም። በሁሉም መስፈርቶች የወደብ ባለቤት መሆን የሚያስገኘው ትርፍ እያንዳንዱ ዜጋ ቤት የሚደርስ በመሆኑ፣ በዚህ አገራዊ አጀንዳ ላይ ሁሉም ዜጋ በአንድ ምልከታና ትልም ውስጥ ሊፈስ ይገባዋል ባይ ነኝ።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ሀሳቡ ተስፋ ስለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን።

ጥሪያችንን በማክበር የበኩር እንግዳ ስለሆኑ ከልብ እናመሰግናለን!

እኔም በዚህ ወቅታዊና ወሳኝ አገራዊ አጀንዳ ላይ ተገኝቼ ሀሳብ እንድሰጥ እንግዳ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!።

(ደጀኔ በቀለ )

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here