የሰው ልጅ በታሪኩ ከተጋፈጣቸው እጅግ አጥፊ እና ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ ክስተቶች መካከል አንዷ በእጅ መዳፍ የምትሸፈነው የወባ ትንኝ ነች። ይህቺ ደቃቃ ፍጡር የዓለም ሕዝብ የጤና ችግር እንደሆነች ዘመናትን አስቆጥራለች፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ240 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ሲያዙ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ከእነዚህ የወባ ተጠቂዎች ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ አህጉር ይኖራሉ፡፡ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት ተጎጂዎች ደግሞ አቅመ-ደካሞች ሕፃናት እና ነፍሰ ጡሮች ናቸው።
በኢትዮጵያም በተለይም በአማራ ክልል ወባ ለዘመናት የበርካቶች ሕይወት የተቀጠፈበት እና የምጣኔ ሀብት ማነቆ ሆኖ የዘለቀ ችግር ነው። አሁንም በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች መልኩን እየቀየረ ማኅበረሰቡን መፈታተኑን አላቆመም። ወባ በሳይንስ የሚታወቅ፣ መከላከያው እና መድኃኒቱ በእጃችን ያለ በሽታ ሆኖ ሳለ ዛሬም ድረስ እንደ ወረርሽኝ የሚቀጥለው በዕውቀት ማነስ ሳይሆን በቁርጠኝነት ክፍተት ነው። በመሆኑም ከዚህ ችግር ለመውጣት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የመንግሥትና የፖሊሲ አውጪዎች ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ማኅበረሰቡም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ በመኖሪያ አካባቢ የሚገኙ ውኃ ያቆሩ ጉድጓዶችን፣ ረግረጋማ ሥፍራዎችን እና የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን በየጊዜው ማድረቅ እንዲሁም ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡ በኬሚካል የተነከሩ አጎበሮችን ሳያሰልሱ ዘወትር ማታ መጠቀም፣ ለሕፃናት እንዲሁም ለነፍሰ ጡሮች ቅድሚያ መስጠትም ያስፈልጋል። ከዚህ ባሻገር ማንኛውም የትኩሳትና የማንቀጥቀጥ ስሜት ሲሰማ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ፣ የታዘዘን መድኃኒት ባአግባቡ እስከ መጨረሻው መውሰድ የመድኃኒት መላመድን ለመከላከል ወሳኝ ነው።
ወባ የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ቀውስ ውጤት ነው፡፡ ድህነት፣ ግጭት እና ደካማ የኑሮ ሁኔታ የወባ በሽታ እንዳይጠፋና እንደ አዲስ እንዲቀሰቀስ አባባሽ መሆናቸው የማይካድ እውነት ነው። የተመጣጠነ ምግብ አለመብላትና በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም እንዲሁም ምቹ ባልሆነ ቦታ መኖር ሌላኛው አባባሽ ምክንያት ነው፡፡ በግጭትና ባለመረጋጋት እንዲሁም በጦርነትና ወቅት የጤና ተቋማት ይወድማሉ ወይም አገልግሎት ያቆማሉ፤ የመድኃኒትና የአጎበር ሥርጭት ይቋረጣል። ማኅበረሰቡ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በሜዳ፣ በጫካ ወይም በተጨናነቁ መጠለያዎች ውስጥ ሲኖር ለትንኝ ንክሻ በቀላሉ ይጋለጣል። የቤት ውስጥ ኬሚካል ርጭትና የትንኝ መራቢያ ማድረቅ ሥራዎች በጸጥታ እጦት ምክንያት ይቆማሉ። ስለሆነም ለምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ለፖለቲካና ማኅበራዊ ሕይወት መረጋጋት መሥራት ወባን በመከላከል ረገድ ሁነኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በአንድ ወቅት አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ የነበረባቸው ቢሆንም፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በተከናወነ የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመኖሪያ ቤት መሻሻል እና የመድኃኒት አጠቃቀም በሽታውን መከላከልና ማጥፋት ችለዋል። በቅርብ ዓመታትም እንደ ቻይና፣ ስሪላንካ፣ አልጄሪያ፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ኬፕ ቨርዴ በዓለም ጤና ድርጅት «ከወባ ነፃ» የሚል ይፋዊ ማረጋገጫ አግኝተዋል። እነዚህ ሀገራት ወባን ያጠፉት ድንገት ሳይሆን በጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ በሰላም ግንባታ እና በጤና ሥርዓት ጥንካሬ ነው። ስለሆነም እነዚህ ሀገራት ወባን ሊያጠፉ የቻሉት እንዴት ነው? ብሎ መጠየቅና የእነሱን ፈለግ መከተል ያስፈልጋል፡፡
ወባን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል በጤና ጣቢያ ውስጥ መድኃኒት በማደል ብቻ ሊሳካ አይችልም። ሰላምን ማስፈን፣ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት እና የመሠረተ-ልማት ደረጃ ማሻሻል፣ ድህነትን መቀነስ እና ጠንካራ የጤና ሥርዓት መገንባት ከወባ መከላከያ ኬሚካሎች እኩል ወሳኝ ናቸው። በአጠቃላይ፣ የወባ ሥርጭትን ለመግታት ጊዜያዊ የእሳት ማጥፋት ሥራ በቂ አይደለም። መንግሥት በፖሊሲ እና በግብዓት፣ የጤና ተቋማት ወደ ማኅበረሰቡ በዘለቀ አገልግሎት፣ ኅብረተሰቡ ደግሞ በነቃ ተሳትፎና ኃላፊነት ሲተሳሰሩ ብቻ በሽታውን በዘላቂነት መከላከል ይቻላል።
በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


