ለልብ ህመም መጋለጥን የሚቀንሰው

0
37

በየእለቱ ከ60 እስከ 100 ግራም በሚደርስ መጠን ካልተፈተገ ስንዴ፣ አጃ፣ ቡናማ ሩዝ እና ገብስን ከመሣሰሉ ጥራጥሬዎች የተዘጋጀ ምግብን መመገብ የልብ እና የደም ማስተላለፊያ ስሮች የህመም ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

የአውሮፓ የልብ ህክምና ማህበር 6529 ሰዎችን ከየአህጉራቱ ካሉ ሀገራት በናሙና ጥናት አሳትፏል፡፡ በተጨማሪም 87 የህክምና ሙከራ ውጤቶችን ተንትኖ ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎችን መመገብ ከሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የወገብ መጠን መስተካከል፣የደም ግፊት፣ የኮሊስትሮል እና  የደም ውስጥ የስኳር  መጠንን ማሻሻሉን አረጋግጧል፡፡

ምርምሩ የተመራው በኢሪን ታብሪዝ የህክምና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በዶክተር ሄልዳ ቱቲኒች ነው፡፡ ተመራማሪዋ ቀደም ብለው በተካሄዱ የምርምር ስራዎች ካለተፈተጉ ጥራጥሬዎች የሚሰሩ ምግቦችን መመገብ ጠቀሜታው የጐላ መሆኑ ቢታወቅም መጠኑ በውል አለመመላከቱን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በየእለቱ ከ4 እስከ 6 ጊዜ ከ60 እስከ 100 ግራም የተለካ ካልተፈተገ ጥራጥሬ የተሰሩ ምግቦችን መውሰድ ተገቢ እና የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው ያረጋገጡት- ተመራማሪዋ፡፡

ከሁሉም በላይ የልብ እና የደም ቧንቧ ህመም የተጋላጭነት መንስኤዎችን በመግታት ጤናማነትን ለማረጋገጥ  የ“ሆል ግሬይን” ካልተፈተጉ ጥራጥሬዎች የተዘጋጁ ምግቦችን መመገብ በአንፃራዊነት ቀላል፣ ተደራሽ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ መሆኑም ነው የተሰመረበት፡፡

በመጨረሻም ከሙሉ ጥራጥሬ ወይም ካልተፈተገ እህል የተዘጋጀ ምግብን በአንድ ጊዜ አብዝቶ ከመመገብ ከእለት እለት መጠኑን እየጨመሩ መመገብ የልብ እና የደም ስር የህመም መንስኤዎችን መቀነስ እንደሚያስችል ነው- በድረ ገፆች ለንባብ የበቃው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here