የማይዘጋው ክፍል – ትምህርትን ከመቋረጥ የጠበቁ የዓለም ተሞክሮዎች

0
30

የአንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በጦርነት፣ በወረርሽኝ፣ በተፈጥሮ አደጋ  ወይም በድህነት ማዕበል ተገፍቶ ሲዘጋ፤ የሚቆለፉት የክፍል በሮች ብቻ አይደሉም፡፡ የሚሊዮን ሕፃናት ሕልሞች፣ የቤተሰብ ብሩህ ተስፋ እና የአንዲት ሀገር የነገ ህልውና ፈተና ውስጥ ይገባሉ።  የዓለም ሀገራት ታዲያ ትልቅ ትምህርት ሰጥተዋል፤ ትምህርት ቤት ሊዘጋ ይችላል፣ ነገር ግን ትምህርት መቆም የለበትም የሚል ተሞክሮ።

ከኬንያ የሬዲዮ ትምህርት፣ ከሕንድ የዲጂታል መድረኮች፣ ከብራዚል የማኅበራዊ ድጋፍ፣ ከፊንላንድ የቅድመ ድጋፍ ሥርዓት እና ከጃፓን የአደጋ ዝግጅት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ትምህርትን ለማስቀጠል የሚያስፈልገው ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆኑ ቀድሞ የተዘጋጀ ዕቅድ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማኅበራዊ ድጋፍ እና ጠንካራ ፖሊሲ ነው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በመማር በማንኛውም ቀውስ ወቅት ትውልድ ከትምህርት እንዳይለይ የሚያስችል ጠንካራ የትምህርት ቀጣይነት ሥርዓት መገንባት ትችላለች።

ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ወረርሽኝ፣ መፈናቀል፣ ድህነትና የኢኮኖሚ ቀውስ በተማሪዎች የትምህርት ጉዞ ላይ ከፍተኛ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ በተለይ በድሃና በቀውስ ውስጥ ባሉ ሀገራት የትምህርት መቋረጥ የዛሬን ተማሪ ብቻ ሳይሆን የነገውን የሰው ኃይል ግንባታ ይነካል፡፡ ዩኔስኮ እንደሚያስገነዝበው ትምህርት እንደ ቀውስ መከላከያና የማኅበረሰብ መቋቋሚያ አቅም ዋና አካል ሆኖ መታየት አለበት፡፡ ይህም ትምህርት በችግር ጊዜ እንዲቆም ከመፍቀድ ይልቅ ሥርዓቱ ከቀውስ ጋር መላመድ እንዲችል አስቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ ያሳያል፡፡

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም የወሰደችው ትምህርት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የትምህርት ቀጣይነት ጉዳይን ወደ ዓለም አቀፍ የፖሊሲ አጀንዳ አምጥቶታል፡፡ ዩኔስኮ፣ ዩኒሴፍ እና የዓለም ባንክ በወረርሽኙ ወቅት ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ተማሪዎች ዕውቀት ከመገብየት እንዳይርቁ የርቀት ትምህርት ዘዴዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ ያሳየው ሌላ እውነታም ነበር፤ በዲጂታል መማር ብቻውን የሁሉንም ተማሪ ችግር እንደማይፈታ አሳይቶ ነበር፡፡ ኢንተርኔት፣ ስማርት ስልክ፣ ኮምፒዩተር እና ኤሌክትሪክ የሌላቸው ተማሪዎች ከዲጂታል ትምህርት ውጭ ሊቀሩ ይችላሉና ነው፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ ልትወስደው የምትችለው ተሞክሮ የርቀት ትምህርት መንገድን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ የሞባይል መልዕክት፣ የታተሙ የመማሪያ ይዘቶች እና ዲጂታል መድረኮችን በተቀናጀ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሚገባ ጭምር ነው።

ኬንያ፦ ሬዲዮን እንደ የመማሪያ አማራጭ መጠቀም

ኬንያ ከከተማ ውጭ ያሉ እና የዲጂታል መሣሪያ ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ የሆነ ተማሪዎችን ለመድረስ ሬዲዮን ከትምህርት ጋር የማገናኘት ልምድ አላት፡፡ በኮቪድ-19 ወቅትም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ትምህርት ከሌሎች የርቀት ትምህርት ዘዴዎች ጋር ተጠቅማለች፡፡ይህ ለኢትዮጵያ በቀጥታ የሚስማማ ተሞክሮ ነው፡፡ በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ኢንተርኔት ተደራሽነት ቢገድብም ሬዲዮ ለብዙ ቤተሰቦች ተደራሽ ነው፡፡ በየደረጃው የተዘጋጀ የሬዲዮ ትምህርት፣ የማዳመጫ መመሪያና የተማሪ ልምምድ በአንድ ላይ ከተዘጋጀ በቀውስ ጊዜ የትምህርት ማቆያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል፡፡

ሕንድ፦ ብዙ የመማሪያ መንገዶችን ማቀናጀት

ሕንድ በከፍተኛ የተማሪ ብዛትና በተለያየ የዲጂታል ተደራሽነት ሁኔታ ምክንያት በኮቪድ-19 ወቅት ከመስመር ላይ መማር በተጨማሪ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ እና የታተሙ የትምህርት ቁሳቁሶችን ተጠቅማለች፡፡

የሕንድ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ የሚያሳየው ትልቁ ነጥብ የመማሪያ መንገዱን በአንድ ቴክኖሎጂ ላይ አለመገደብን ነው፡፡ በከተማ ያለ ተማሪ በዲጂታል መድረክ በሩቅ አካባቢ ያለ ተማሪ ደግሞ በሬዲዮ ወይም በታተመ መጽሐፍ ሊማሩ ይችላል፡፡ ዋናው ግብ ቴክኖሎጂው ሳይሆን ተማሪው ከመማር እንዳይርቅ ማድረግ ነው፡፡

ኡጋንዳ፦ ትምህርትን ከማኅበራዊ ድጋፍ ጋር ማገናኘት

በኡጋንዳ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት መቋረጥ ከድህነት፣ ከምግብ እጥረት፣ ከሕፃናት ጉልበት ሥራ እና ከልጃገረዶች የቤተሰብ ጫና ጋር የተያያዘ መሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተገልጿል። ስለዚህ ትምህርትን ከማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ጋር ማገናኘት ወሳኝ ሆኗል።

የዓለም ባንክ እና ዩኒሴፍ በተለያዩ ሀገራት የትምህርት ቤት ምገባ፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና ሌሎች ማኅበራዊ ጥበቃዎች ተማሪዎችን በትምህርት ለማቆየት እንደሚያግዙ ያሳያሉ።

ለኢትዮጵያም ይህ ተሞክሮ በተለይ የድህነት አደጋ ለከፍተኛ የትምህርት ማቋረጥ ሊያጋልጣቸው የሚችሉ ተማሪዎች ላይ ሊተገበር ይችላል። የትምህርት ቤት ምገባ፣ የመጻሕፍትና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እና በጣም ለተጋለጡ ቤተሰቦች የማኅበራዊ ጥበቃ ድጋፍ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ልጆችን ለማቆየት ይረዳል።

ብራዚል፦ ለድሃ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ

ብራዚል በተለይ በሁኔታዊ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሞቿ ትታወቃለች። እንደ ቦልሳ ፋሚሊያ ያሉ ፕሮግራሞች የቤተሰብ ድህነትን ለመቀነስ ከትምህርትና ከጤና ጋር የተያያዙ መስፈርቶችን አካተዋል።

ይህ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ የሚያሳየው የትምህርት ማቋረጥን በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ መፍታት አስቸጋሪ መሆኑን ነው። የቤተሰብ ገቢ ከተማሪው የትምህርት ቆይታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ከሆነ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲዎችን ከትምህርት ፖሊሲ ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል።

ፊንላንድ፦ ተማሪዎችን ቀድሞ መለየትና መደገፍ

ፊንላንድ በትምህርት ሥርዓቷ የተማሪዎችን የመማር ችግር በቀድሞ መለየትና የተለየ ድጋፍ መስጠት ላይ ትኩረት ካደረጉ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች። ተማሪው ከትምህርቱ ከወደቀ ወይም ከቀረ በኋላ ብቻ ሳይሆን ችግሩ ከመባባሱ በፊት ድጋፍ እንዲያገኝ የሚያስችል አቀራረብ አላት።

ይህ ለኢትዮጵያ በተለይ የሚጠቅመው የተማሪ መቅረትን በመከታተል ነው። ተማሪው ተደጋጋሚ መቅረት ከጀመረ ትምህርት ቤቱ እና ወላጆቹ በጋራ ምክንያቱን በመለየት ድጋፍ ቢያደርጉ ብዙ ተማሪዎች ከማቋረጥ ሊድኑ ይችላሉ።

ለኢትዮጵያ የሚወሰደው ተሞክሮ

የእነዚህ ሀገራት ተሞክሮ ሲታይ ለኢትዮጵያ አንድ ቀጥተኛ መፍትሔ ከሌሎች ሀገራት መቅዳት ሳይሆን ተሞክሮዎቹን ከሀገሪቱ ሁኔታ ጋር ማስማማት ነው፤ ከኬንያ ሬዲዮን እንደ ተደራሽ የመማሪያ መሣሪያ መጠቀም፣ ከሕንድ ብዙ የመማሪያ መንገዶችን ማቀናጀት፣ ከብራዚል የማኅበራዊ ጥበቃን ከትምህርት ጋር ማገናኘት፣ ከፊንላንድ የተማሪ ችግርን ቀድሞ መለየት እና መደገፍ የሚሉትን መውሰድ ይገባል።

ይህ ሁሉ በአንድ የተቀናጀ የትምህርት ቀጣይነት ፖሊሲ ውስጥ ሊገባ ይገባል። የትምህርት ቤት መዘጋት ቢያጋጥም ተማሪው በምን መንገድ ይማራል? መምህሩ እንዴት ይደግፋል? የትምህርት ቁሳቁስ እንዴት ይደርሳል? የተፈናቀለ ተማሪ እንዴት በፍጥነት በአዲስ ትምህርት ቤት ይመዘገባል? የድሃ ቤተሰብ ልጅ በኢኮኖሚ ምክንያት እንዳያቋርጥ ምን ይደረጋል? የሚሉ ጥያቄዎች አስቀድመው መልስ ሊያገኙ ይገባል።

የትምህርት ቀጣይነት የሀገር ቀጣይነት ነው፤ ትምህርትን እንዳይቋረጥ ማድረግ ትምህርት ቤቶችን ክፍት ከማድረግ የበለጠ ሰፊ ጉዳይ ነው። ተማሪው ምግብ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ፣ ደህንነት፣ የስነ-ልቦና ድጋፍና ብቁ መምህር እንዲያገኝ ማድረግም የዚሁ አካል ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የትምህርት ቀጣይነትን እንደ ቀውስ ጊዜ የሚወሰድ የአስቸኳይ እርምጃ ብቻ ሳይሆን እንደ ቋሚ የትምህርት ፖሊሲ ልትመለከተው ይገባል። የትምህርት ቤት መዘጋት ሲከሰት የሚነሳው “እንዴት እንከፍተው?” የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን “ትምህርት ቤቱ ቢዘጋም ትምህርቱን እንዴት እናስቀጥል?” የሚለውም መሆን አለበት።

ትምህርት በቀውስ ጊዜ ከተቋረጠ ትውልድ ይጎዳል፤ በቀውስ ጊዜም ከቀጠለ ግን ሀገር የሰው ኃይሏን ለመጠበቅ የተሻለ ዕድል ታገኛለች። የዓለም ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

    መረጃ

 

በጦርነት፣ በበሽታ፣ በድርቅና በሌሎች ችግሮች ወቅት ትምህርት እንዳይቋረጥ የተለያዩ አማራጮችን የተጠቀሙ ሀገራት ተሞክሮ፦
ዩክሬን – በጦርነት ወቅት ትምህርት በኦንላይንና በተቀላቀለ ሥርዓት እንዲቀጥል አድርጋለች፤ ለተማሪዎችም የዲጂታል ትምህርት ሀብቶች ተዘጋጅተዋል።
ሶሪያ – በጦርነት ምክንያት ትምህርት ቤቶች በሚዘጉባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ የመማሪያ ማዕከላትና ተለዋጭ የትምህርት ዘዴዎች ተጠቅመዋል።
ባንግላዴሽ – በጎርፍና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ጊዜ ተንቀሳቃሽ/ጊዜያዊ የመማሪያ ማዕከላትን በመጠቀም ትምህርትን ቀጥላለች።
ኬንያ – በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የሞባይል፣ የሬዲዮ ትምህርትና የማህበረሰብ የመማሪያ ሥርዓቶችን ተጠቅማለች።
ሩዋንዳ – በCOVID-19 ወረርሽኝ ወቅት ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በዲጂታል መድረኮች ትምህርትን አስቀጥላለች።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here