ነጥሎ መሟገት

0
50

እኔ የማምነውን ካላመንክ ጠላቴ ነህ፤ የማቀርበውን ሀሳብ ከተቃወምክ ደግሞ ማንነትህን እዋጋሃለሁ የሚለው እኩይ አመለካከት የሠለጠነውን ዓለም አእምሮ እየሸረሸረ ይገኛል፡፡

በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የውይይት መድረኮች ወደ ጦር ሜዳነት ሲቀየሩ እውነት ከመካከል ጠፍታ ድምፅ ያወጣውና የተሳደበው የበላይ ይሆናል፡፡

ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጾችም ሆነ በመደበኛ መድረኮች የምንታዘበው መሪር እውነታ ይኸው ነው። ሀሳብን በሀሳብ ከመመከት ይልቅ ሰውን በማዋረድ፣ ስም በማጥፋት እንዲሁም ማንነትን በማሳጣት ክርክርን ለማሸነፍ መሯሯጥ፡፡

ይህ ደግሞ የክርክር እጦት ብቻ ሳይሆን የአንድ ማኅበረሰብ የሞራልና የሥነ ልቦና ውድቀት ማሳያ ነው፡፡

የኮምዩኒኬሽንና የሥነ አመክንዮ ሊቃውንት ይህንን አደገኛ አባዜ “አድ ሆሚነም” ወይም ባለቤቱን ማጥቃት ሲሉ ይጠሩታል፡፡

ፖል ግራሃም “የክርክር እርከኖች” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፉ የሰዎችን የሙግት ደረጃ በሰባት እርከኖች ከፋፍሎ አሳይቷል፡፡

በእነዚህ እርከኖች መሠረት በጣም ዝቅተኛውና ሥልጣኔ የጎደለው የክርክር ዓይነት ሰውን መሳደብ፣ ማንቋሸሽና ለሀሳቡ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የግል ታሪኩን ማጉደፍ ነው።

በአንጻሩ ከፍተኛውና የሠለጠነው እርከን የቀረበውን ዋና ሀሳብ ነቅሶ በማውጣት በአመክንዮ መተቸትና ማረም ነው፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙኃኑ ሙግት በመጀመሪያዎቹ ዝቅተኛ ደረጃዎች ላይ ተቸክሎ ይገኛል፤ ይህም የሠለጠነ ውይይትን ወደ መንደር ጭቅጭቅ ዝቅ አድርጎታል፡፡

ጀርመናዊው ፈላስፋ ዩርገን ሐበርማስ “የተግባቦት ተግባር ንድፈ ሀሳብ” በተባለው  መጽሐፉ እንዳስገነዘበው ጤናማ ማኅበረሰብ ሊገነባ የሚችለው በሀሳብ እና  በመደማመጥ ላይ በተመሠረተ ኅብረት ብቻ ነው፡፡

ሐበርማስ የውይይት ቅዱስ ዓላማ ሌላውን ማሸነፍ ወይም ማዋረድ ሳይሆን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሆነ ያስረዳል፤ ሆኖም ግን ግለሰባዊ እኔነት ከሀሳብ ጋር ሲጣበቅ ውይይት ይሞታል፡፡

የኖቤል ተሸላሚው ዳንኤል ካህነማን “ፋስት ኤንድ ስሎው ቲንኪንግ” በተሰኘው የምርምር ሥራው እንደገለጸው የሰው ልጅ አእምሮ የአመለካከት ልዩነትን እንደ አካላዊ አደጋ አድርጎ የመተርጎም ተፈጥሯዊ ዝንባሌ አለው፡፡

ይህ ስሜታዊ ግፊት ሰውን ራሱን ጠላት አድርጎ እንዲፈርጅ ይገፋፋዋል፤ በዚህም ምክንያት በአመለካከት የተለየንን ወገን እንደ ተቃዋሚ ኃይል እንጂ እንደ ማኅበረሰብ አባል አንመለከተውም፡፡

ሀሳብን ከሰው ለይቶ ያለመሟገት ባህል የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ ነው፡፡

የመጀመሪያው ቀውስ የዕውቀትና የፈጠራ ሞት ነው፤ ሰዎች በነጻነት አዳዲስ ሀሳቦችን እንዳያመነጩ፥ ጥያቄ እንዳያነሱና አማራጭ መንገዶችን እንዳይጠቁሙ የማኅበራዊ መገለል ፍርሃት ያጠላባቸዋል፡፡

ሁለተኛው አደጋ ጽንፈኝነትና ማኅበራዊ መከፋፈል ነው፤ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች በሀሳብ ልዩነት ምክንያት ብቻ አንዱ ሌላውን እንደ አውሬ የሚመለከትበት መርዛማ ድባብ ይፈጠራል፡፡

ሦስተኛው ጉዳት ደግሞ የተቋማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት መላሸቅ ነው፤ የሕዝብ ውይይቶች ጥራት ባጡ ቁጥር የሚወጡ ፖሊሲዎች፥ የሚወሰዱ ውሳኔዎችና የሚመረጡ አመራሮች በጥላቻ እንጂ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ አይሆኑም፡፡

በውጤቱም አገር የሰከነ ሀሳብ ማፍለቅ የማትችል፣ በጥላቻ የሰከረችና በስሜታዊነት የምትነዳ ማኅበረሰብ ስብስብ ትሆናለች፡፡

በተጨማሪም ዶግላስ ዋልተን “የአድ ሆሚነም ክርክሮች” በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያትተው የሰውን ሰብእና ማጥቃት የአቅመ ቢስነት መገለጫ ነው፡፡

አንድ ግለሰብ የቀረበለትን አመክንዮ በዕውቀት መመከት ሲሳነው ቀላሉን መንገድ ይመርጣል፤ ይህም የባለቤቱን ማነት፣ ጾታ፣ ዘር፣ እምነት ወይም ያለፈ ታሪክ በመጎተት ሀሳቡን ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡

ይህ ድርጊት የአመክንዮ ውድቀት ብቻ ሳይሆን ግብረ ገባዊ ሽንፈት ጭምር ነው፤ ምክንያቱም እውነት የተናጋሪውን ማንነት እይታ ሳይሆን በራሷ ሚዛን ተመዝና የምትጸድቅ መሆኗን መካድ ነው፡፡

ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ክርክርን የእውነት መውለጃ እንጂ የድል ማወጃ አላደረገውም፤ እርሱ ከተከራካሪዎቹ ጋር ሲነጋገር ሀሳባቸውን እንጂ ሰብእናቸውን አይመረምርም ነበር፡፡

የኮምዩኒኬሽን ሳይንስ ምሁራን እንደሚመክሩት ፍሬያማ ክርክር እንዲኖር የበጎ አሳቢነት መርሕ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡

ይህ መርሕ የተቃራኒ ወገንን ሀሳብ በክፉ ዓይን ከመተርጎም ይልቅ በተቻለ መጠን በላቀና በጠንካራ መልኩ ተረድቶ ምላሽ መስጠትን ይጠይቃል፡፡

ሀሳብን ከሰው ለመለየት የመጀመሪያው እርምጃ የራስን እውቀት ፍጹም አለመሆን መቀበል ነው፤ ጆን ስቱዋርት ሚል ስለ ነጻነት በተባለው መጽሐፉ እንዳሰፈረው የተቃዋሚውን ሀሳብ የማያውቅ ሰው የራሱንም ሀሳብ በቅጡ ሊያውቅ አይችልም፡፡

ስለዚህ የተለየ አመለካከት ያለው ሰው የውድቀታችን መንስኤ ሳይሆን የዕውቀታችን አድማስ ማስፊያ ነው፤ እርሱ የያዘው የተለየ እይታ እኛ ያላየነውን የእውነት ክፍል እንድንመለከት በር ይከፍትልናል፡፡

ስለዚህ ከዚህ አዘቅት ለመውጣት በኅብረተሰባችን ውስጥ የክርክር ሥነ ምግባር ሥር መስደድ አለበት፡፡ በትምህርት ቤቶች፥ በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በሚዲያ መድረኮች ዜጎች በሀሳብ ብቻ እንዲፋለሙ ማስተማር ይገባል፡፡

አንድን ሀሳብ ስንቃወም “ሀሳቡ ስህተት ነው” ማለት እንጂ “አንተ ስህተት ነህ” ወደሚል ማንነትን የሚነካ ዘለፋ መሸጋገር የለብንም፡፡

የቋንቋ አጠቃቀማችን ከስድብ፣ ከስም ማጥፋት እንዲሁም ከማንቋሸሽ የጸዳ መሆን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የቋንቋ ጥራት የአስተሳሰብ ጥራት መስታወት ነው፡፡

ውይይት የሰው ክብር የሚጠበቅበት፣ እውነት የሚፈለግበትና ልዩነቶች እንደ ውበት የሚታዩበት የሥልጣኔ አውድማ መሆን ይገባዋል እንጂ የቂም በቀል መወጣጫ ሊሆን አይገባም፡፡

በመጨረሻም ልብ ልንለው የሚገባው ታላቅ እውነት አለ፤ የሰው ልጅ ክብር የማይደፈር ቅዱስ ሀብት ሲሆን ሀሳብ ግን ሊፈተሽ፣ ሊተች፣ ሊለወጥና ሊጣል የሚችል ጊዜያዊ ግንባታ ነው፡፡

የሰው ልጅ ዋጋው የሚለካው ባቀረበው ሀሳብ ትክክለኛነት ሳይሆን በሰብአዊ ማንነቱ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እኛ የምንታገለውና የምንሟገተው ከሀሳቦች ጋር እንጂ ከሰዎች ጋር መሆን እንደሌለበት ማመን የሥልጣኔ መጀመሪያ ነው።

ምክንያቱም ሀሳብን ከሰው ለይቶ የመሟገት ሥነ ምግባር ሳይኖረን ዴሞክራሲያዊት፣ ፍትሐዊትና ሰላማዊት አገር መገንባት አይቻልም፡፡

ልዩነቶቻችንን በክብር የምንቀበልበትና ሰውን ሳናዋርድ በሀሳብ ብቻ በጨዋነት የምንከራከርበት መልካም ልማድ ሲጎለብት ብቻ የሰው ልጆች እውነተኛውን የነጻነትና የዕውቀት ብርሃን እንጎናጸፋለን፡፡

ያን ጊዜ የጋራ መድረኮቻችን የጥላቻ ማቀጣጠያ ከመሆን ወጥተው የፍቅር፣ የኅብረትና የዕድገት እውነተኛ ድልድይ ይሆናሉ፤ ይህም ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ የታላቅ ሥልጣኔ ቅርስና የሕዝቦች ጸጋ ነው፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here