የባሕር ዳር ብሔራዊ ስቴዲየም ቱሩፋቶች

0
52

የባሕር ዳር ብሔራዊ ስቴዲየም ከአምስት ዓመታት ዕገዳ በኋላ በቅርቡ የእድሳት ሥራዎች ተከናውነውለት ውድድሮች ይካሄዱበት ዘንድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደረገውን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ አስተናግዷል፡፡ በጣና ሐይቅ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ የስፖርት ማዕከል እንደገና የዓለም አቀፍ ትኩረት ለማግኘት በቅቷል፡፡

ይህ የካፍ እገዳ ሊነሳ የቻለው የአማራ ክልል መንግሥት 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መድቦ ባከናወነው  የማዘመን ሥራ ነው፡፡ ስቴዲየሙ ለምሽት ጨዋታ እና ለቴሌቪዥን ስርጭት የሚያበቃ ከ1400 ሉክስ በላይ አቅም ያለው ዘመናዊ መብራት እና ግዙፍ ዲጂታል ስክሪኖች የመግጠም ስራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራዎች እና የኤሌክትሮኒክስ መግቢያ በሮች ተካተውበታል፡፡

አራት ቡድኖች በአንድ ጊዜ የስፖርት ትጥቅ ሊቀይሩባቸው የሚችሉ ክፍሎች የበረዶ ገንዳ እና ማሳጅ የተሟላላቸው ክፍሎች አሉት፡፡ አምቡላንስ በቀጥታ የሚገባበት የድንገተኛ ህክምና እና የተጫዋቾች የዕፅ ምርመራ ማዕከል ተዘጋጅቶለታል፡፡ አንድ መቶ ሀያ የመገናኛ አውታሮችን ማስተናገድ የሚችል የሚዲያ ክፍል እና ለክብር እንግዶች የራሱ አሳንሰር ያለው ማረፊያ አለው፡፡

ጨዋታ በሌለበት ቀንም አገልግሎት የሚሰጡ ሱቆች ካፌዎች እና ጅም ቤቶች ያሉት ሲሆን ከ200 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ስታዲየሙ ባለ 8 መስመር ሰው ሰራሽ የሩጫ ትራክ አለው፡፡

በአርባ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ግዙፍ ስቴዲየም ከ50 ሺህ በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው፡፡ ግንባታው በ2002 ዓ.ም በ780 ሚሊየን ብር የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በግዝፈቱ ቁጥር አንድ ስታዲየም ሆኗል፡፡

የውሃ መውረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀውን የተፈጥሮ ሳር የሰራው 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያስተናገዱትን የኮትዲቯር ምርጥ ስታዲየሞች የገነባው ግሪጎሪ የተባለ ዕውቅ የፈረንሳይ ኩባንያ ነው፡፡ የካፍን መስፈርት ያሟሉት ደረጃቸውን የጠበቁ ቀለም ያላቸው ወንበሮች ደግሞ በሜድሮክ ኢትዮጵያ ስር ባለው አዲስ ጋዝ ኩባንያ ተገጥመዋል፡፡ ከዋናው የእግር ኳስ መጫዎቻ ሜዳ በተጨማሪ በቅጥር ግቢው ሁለት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መለማመጃ ሜዳዎች ተሠርተዋል፡፡

ይህም ለኢትዮጵያ ስፖርት እና ለአካባቢው ማህበረሰብ አዲስ የብርሃን ተስፋን ይዞ ብቅ ማለቱን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ አዲስዓለም ምህረት ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ስቴዲየሙ ከመጫወቻ ሜዳነት ባለፈ ሰፊ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቱሩፋት እንዳሉት አቶ አዲስዓለም ተናግረዋል፡፡

የሰላም እና የአንድነት ታላቅ መድረክ በመሆንም እንደሚያገለግል የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ዜጎችን በአንድነት ያስተሳስራል፤ ስቴዲየሙ ሕዝብን እንደሚያቀራርብ ከዚህ በፊት በነበሩ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በተግባር አሳይቷል፤ ወደፊትም ያሳያል፡፡

የባሕር ዳር ብሔራዊ ስቴዲየም ሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር ለመፍጠር ትልቅ ድልድይ ይሆናል፡፡ ስቴዲየሙ የሰላም መዝሙር የሚዘመርበት ልዩ መድረክ በመሆንም ያገልግላል፡፡ ብሔራዊ ስቴዲየሙ ትላልቅ ውድድሮችን እና ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የስፖርት ቱሪዝም ፍሰቱ ከጣና ሐይቅ መስህቦች ጋር በጥብቅ ይተሳሰራል፡፡ የንግድ ማህበረሰቡ ስቴዲየሙ ባመጣው ቱሩፋት ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆን አቶ አዲስዓለም ምህረት ይናገራሉ፡፡

ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል፡፡ “ወጣቶች በንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን ይለውጣሉ” ብለዋል፤ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ፡፡ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ያለው ድርሻም የጎላ እንደሆነ ነው መምህሩ የተናገሩት፡፡

“ብሔራዊ ስቴዲየሙ ታድሶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ የማዘውተሪያ ስፖርት ክፍተቶችን በመሙላት ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ይታደጋቸዋል፡፡ ከመደበኛ የስፖርት ውድድሮች ባለፈ ትላልቅ የባህል ዝግጅቶችንም ያስተናግዳል” ሲሉ አቶ አዲስዓለም አስረድተዋል፡፡ ስቴዲየሙን እንደ ስፖርት ማዕከል ብቻ መመልከት እንደማይገባ የሚናገሩት የስፖርት ሳይንስ መምህሩ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ታዋቂዋ አትሌት መሰለች መልካሙ እንዳረጋገጠችው ይህ ስታዲየም አትሌቶቻችን ሰዓት ለማሟላት ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ የሚያወጡትን ወጪ እና ድካም ያስቀርላቸዋል፡፡ ከእግር ኳስ ውጪ ማርሻል አርት ቴኒስ ፉትሳል እና የመዋኛ ገንዳዎችን ያካተተ በመሆኑ ሁለንተናዊ ጥቅም ይሰጣል፡፡

የስቴዲየሙን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ እንዲገነባ በማድረግ ለዓለም እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎች ማከራየት እንደሚችልም ተነስቷል፡፡ በተለይ የጎረቤት ሀገራትን ብሔራዊ ቡድኖች በቋሚነት እንዲያስተናግድ ከዚህም በላይ ደረጃውን ማሻሻል ይገባል ነው የተባለው፡፡

ስቴዲየሙ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ አቅም ይፈጥራልም ተብሏል፡፡ ታዲያ ይህንን ቱሩፋት የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ትልቅ ሀብት ሊንከባከበው ይገባል፤ የሚመለከታቸው አካላትም በንቃት መከታተል እንዳለባቸው አቶ አዲስዓለም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስቴዲየሙ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የስፖርት ግንባታ ውጤት ነው፡፡ የባሕር ዳር ብሔራዊ ስቴዲየም ለኢትዮጵያ የስፖርት እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ግዴታ መሆኑን በጎንደር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አቶ አዲስዓለም ምህረት አስገንዝበዋል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here