የሀገር ብሔራዊ መዝሙር በዓለም አደባባይ ሲዘመር መስማት እና ሀገርን ወክሎ መሮጥ በአትሌቶቹ ዘንድ ታላቅ ኩራትን ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን በቅርብ ዓመታት በርካታ ታዋቂ አትሌቶች ዜግነታቸውን እየቀየሩ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ አስነብቧል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ መረጃ እንደሚያመለክተው ዜግነታቸውን የሚቀይሩ አትሌቶች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚህ አትሌቶች ከትውልድ ሀገራቸው ይልቅ ለባዕድ ሀገር መወዳደርን መርጠዋል፤ እየመረጡም ነው፡፡
አንድ አትሌት በሙያው ከፍተኛ ብቃት የሚያሳይበት ዘመን በጣም አጭር ነው፡፡ በአማካይ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ ብቻ የተገደበ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በጉዳት እና መሰል ምክንያቶች ከሜዳ የሚገለሉበት ጊዜ ድንገት በመሆኑ በዚህ አጭር እና ወርቃማ የዕድሜ ክልል ራሳቸውን መለወጥ እንዳለባቸው በማሰብ ሳይመሽ በፍጥነት ሁሉንም ለማከናወን እንደሚተጉ መረጃው ያትታል፡፡
የአፍሪካ አትሌቶችን ፍልሰት በተመለከተ በወጣው መረጃ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ አትሌቶች የሚከፈላቸው ክፍያ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ላባቸውን አፍስሰው ለሚያስመዘግቡት ውጤት የሚሰጠው ማበረታቻም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡
እነዚህ አትሌቶች ታዲያ ከስፖርቱ ዓለም ሲገለሉ የተረጋጋ የጡረታ ዋስትና አይኖራቸውም፡፡ በአንጻሩ የበለጸጉ ሀገራት ለአትሌቶች ከጥሩ የገንዘብ ክፍያ በተጨማሪ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እና የዕድሜ ልክ የጡረታ ዋስትና መስጠታቸው ስፖርተኞቹ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ እናት ሀገራቸውን በመተው ዜግነት እንዲቀይሩ ያስገድዳቸዋል ፡፡
በየሀገራቱ ባሉ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ የሚታየው የአስተዳደር ክፍተት አትሌቶች ዜግነታቸውን የሚቀይሩበት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ አስነብቧል፡፡ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት ጥራት ያላቸው የማሰልጠኛ ስፍራዎች እጥረት፣ ዘመናዊ የስፖርት ሳይንስ ድጋፍ አለማግኘት፣ በስፖርት መሪዎች ዘንድ የሚታየው ያልተገባ አሠራር በአትሌቶች ዘንድ ትልቅ ተስፋ መቁረጥን ይፈጥራል፡፡
እነዚህ ስፖርተኞች በሀገራቸው ስፖርት አመራር ተስፋ ሲቆርጡ የሙያ ነጻነታቸውን ወደ ሚያስጠብቅላቸው ሀገር መሰደድን ለመምረጥ ይገደዳሉ፡፡
የግንኙነት መሻከርም ሌላኛው በአትሌቶች ዘንድ በግልጽ የማይነገር ለአትሌቶች መሰደድ ትልቅ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የእርስ በርስ መናቆር አትሌቶች በሀገር ውስጥ ደኅንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡
በአትሌቶች እና በአሰልጣኞች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት፣ ሥራ አስኪያጆቻቸው (ማኔጀሮች) የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ማሳደዳቸው፣ አትሌቶች በሀገራቸው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው እና የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል ይላል፤ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ፡፡
በሀገር ውስጥ ባሉ የስፖርት ማህበራት በኩል የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥርም ውጥረቱን በማባባስ በአትሌቱ እና በፌዴሬሽኑ መካከል ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ እንዲሸረሸር በማድረግ የእትሌቶችን መሰደድ ያፋጥናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ባህል በሆነባቸው ሀገራት በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቦታ ለማግኘት እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል፡፡ መረጃው እንደሚያስነብበው በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸናፊ መሆን የሚችሉ በርካታ ብቁ አትሌቶች በሀገራቸው ባለው ከፍተኛ ውድድር ምክንያት በኦሊምፒክ መድረኮች የመሳተፍ እድልን ሳያገኙ ሊቀሩ ይችላሉ፡፡
ይህንን ክፍተት በሚገባ የሚገነዘቡ ሀገራት ደግሞ የዜግነት እና የገንዘብ ማባበያዎችን በማቅረብ በቀላሉ አትሌቶችን ያስኮበልላሉ፡፡ ለአብነት ትውልደ ኢትዮጵያዊት መሪም ዩሱፍ ጀማል ዜግነቷን ወደ ባህሬን በመቀየር የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏን የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ ያሳያል፡፡ አትሌት ሲፋን ሀሰንም በትውልድ ኢትዮጵያዊት ብትሆንም የኔዘርላንድስ ዜግነትን በመቀበል በኦሊምፒክ ታሪክ ድንቅ ድሎችን ማስመዝገቧን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በትውልድ ኬንያዊ የሆነው በርናርድ ላጋት የአሜሪካን ዜግነትን በመቀበል እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ በትውልድ ኬንያዊት የሆነችው ሩት ጄቤት የባህሬን ዜግነትን ተቀብላ በኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ አትሌቶች የተሻለ የውድድር ዕድል እና የኢኮኖሚ ዋስትና ፍለጋ ዜግነታቸውን የቀየሩ መሆናቸውን የዓለም አትሌቲክስ ያስነብበናል፡፡
ይህ የዜግነት መቀየር ሂደት በሁለቱም ወገኖች ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማሳረፉ ግን አይቀርም ይላል መረጃው፡፡ ምንም እንኳ አትሌቶች በገንዘብ ተጠቃሚ ቢሆኑም የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የሕይወት ዋስትና ቢያገኙም ለባዕድ ሀገር መሮጣቸው ግን ክፉኛ እንደሚያንገበግባቸው እና ምቾት እንደሚነሳቸው ነው መረጃው የሚያትተው፡፡
በትውልድ ሀገራቸው ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ደግሞ የከፋ መሆኑን መረጃው አልሸሸገም፡፡ አንድ ሀገር በከፍተኛ ወጪ ያሳደገቻቸውን ውድ ተሰጥኦዎች በአንድ ጀምበር ማጣቷ በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገርን ገጽታ ከመጉዳቱም በላይ በትውልዱ ዘንድ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሸረሸር ያደርጋል፡፡
ይህንን አስከፊ የአትሌቶች ፍልሰት ለመግታት እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ወርሃዊ ክፍያ እና የውድድር ማበረታቻ ሽልማቶችን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ተገቢ መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡
ይህንን ዓለም አቀፍ መረጃ ከሀገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ለችግሩ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የችግሩን ስፋት በሚገባ ለመረዳት ሀገራቸውን ሳይለቁ በጽናት የሚወዳደሩ አትሌቶች የሚያነሷቸውን ተግዳሮቶች አዳምጦ መፍታት ትክክለኛ መፍትሄ አመላካች መንገድ ነው፡፡
አትሌቶች ከስፖርቱ ዓለም በይፋ ሲገለሉ የሚኖራቸውን አስተማማኝ የህክምና እና የዕድሜ ልክ የጡረታ ዋስትና አስተማማኝ ማድረግ፤ በስፖርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ የሚታየውን ሙስና እና አድልዎ ማስወገድ፣ በአትሌቶች እና በአሰልጣኞች መካከል የሚፈጠሩ የጥቅም መሻከሮችን የሚፈታ ነጻ የጋራ መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ በብቃት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግልጽ አሰራር መፍጠር አትሌቶችን ከፍልሰት እንደሚታደግ የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማሰልጠኛ ስፍራዎችን እና የህክምና ማዕከላትን በስፋት በመገንባት የአትሌቶችን ፍልሰት መግታት እና የሀገርን ክብር በዓለም አደባባይ ማስጠበቅ እንደሚቻል የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል፡፡
በመጨረሻም መንግሥት እና የሚመለከታቸው የስፖርት ማህበራት ስፖርተኞችን በሀገር ለማቆየት አፋጣኝ የተግባር ርምጃዎችን መውሰድ መጀመር አለባቸው፡፡ የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ጀግኖችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን እነሱን መንከባከብ እና ማቆየት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


