ማዲያትን እንዴት እንከላከል?

0
57

የቆዳ ቀለም የሰውን ውጫዊ ገጽታ ከሚወስኑ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ይሁንና በቆዳ ላይ ያልተለመዱ የተለያዩ የቀለም ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ማዲያት እና “ሃይፐርፒግመንቴሽን” የሚባሉት በተለይ በፊት (ግንባር፣ ጉንጭ እና አፍንጫ) በአንገትና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ጥቁር ወይም ቡናማ ነጠብጣቦችን የሚያስከትሉ የቆዳ በሽታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ቆዳን ከሚያበላሹ በሽታዎች መካከል በዚህ ሳምንት የጤና አምዳችን ማዲያት ላይ እናተኩራለን፡፡

ማዲያት በበርካታ ሰዎች ላይ የሚታይ ቢሆንም ምክንያቱን በትክክል መረዳት፣ ከሌሎች የቆዳ ችግሮች መለየትና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በመብሪጅ የቆዳ ክሊኒክ የቆዳ እና አባላዘር በሽታዎቸ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ምሕረቱ እንዬውን  በኵር አነጋግራለች፡፡ ዶ/ር ምሕረቱ እንዳሉት ማዲያት በቆዳችን  በዋናነት በፊታችን ቆዳ ላይ የሚፈጠር ጠቆር ያለ ነጠብጣብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም አልፎ አልፎ በወንዶችም ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ በወጣትነት የዕድሜ ክልል በሚገኙት ላይ የመከሰት አጋጣሚው ሰፊ ነው፡፡ ከአጠቃላዩ የሕዝብ ብዛትም አንድ በመቶው የሚሆነው ማዲያት ይከሰትበታል፡፡

ባለሙያው እንዳብራሩት በቆዳችን ውስጥ “ሜላኖሳይትስ” (Melanocytes) የተባሉ ሴሎች አሉ፡፡ እነዚህ ሴሎች ሜላኒን (Melanin) የተባለውን የቆዳ ቀለም የመሚያመርት ንጥረ ነገር ያመነጫሉ፡፡ ታዲያ ማዲያት የሚፈጠረው እነዚህ ሴሎች በተለያዩ ምክንያቶች ከመጠን በላይ ሜላኒን ማምረት ሲጀምሩ እና በቆዳ ላይ በመከማቸት  የጠቆረ ቦታ ሲፈጥሩ ነው፡፡

ማዲያት እንዲከሰቱ የሚያደርጉ ዋና ዋና መንስኤዎች

ዶ/ር ምሕረቱ እንደገለጹት የፀሐይ ብርሐን ጨረር (Ultraviolet Rays) ሜላኖሳይትስ ሴሎች በብዛት ሜላኒን እንዲያመርቱ የሚያነሳሳ ዋናው እና የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት የኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን ሆርሞኖች መጨመር ማዲያት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ “ፕሬግናንሲ ማስክ” ይባላል፡፡

የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒቶችን መጠቀም፣ ​ አልፎ አልፎ በሽታዎችን ለማከም የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለአብነትም የሚጥል በሽታን ለማከም የሚሰጠው መድሃኒት ማዲያትን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ሙቀት እና ጭንቀትም እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና ሰፊ እና የተረጋገጡ ጥናቶችን የሚጠይቁ  መሆናቸውን ነው ባለሙያው ያስረዱት፡፡

ባለሙያው እንዳሉት በእርግዝና ጊዜ የሚወጣው ማዲያት የተወሰነው ከወሊድ በኋላ ያለምንም ሕክምና ሊጠፋ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ  ሳይጠፋ በዛው የመቀጠል እድልም ሊኖረው ይችላል፡፡  ከጠፋ በኋላ እንኳ በቀጣዩ እርግዝናም ተመልሶ የመምጣት ሁኔታ ይኖረዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ማዲያትን ከድህነት ጋር ያገናኙታል፤ ይህ አስተያየት ልክ ነው? በማለት ለባለሙያው ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡  ዶ/ር ምሕረቱ እንዬው  እንዳሉት ምናልባት በተዘዋዋሪ  ድህነት ከሚያስከትለው ጭንቀት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡

ኮምፒውተር ወይም ከስልክ የሚወጣ ብርሐን ለቆዳ ሕዋሳት መቆጣት ምክንያት በመሆን ማዲያትን ያባብሳሉ፡፡ የቆዳ መቆጣትን የሚያስከትሉ ወይም የኬሚካል ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ የፊት ቅባቶች እና ሳሙናዎች፣ የዘር ውርስ ማለትም በቤተሰብ ውስጥ ማዲያት ያለበት ሰው ካለ የመያዝ አጋጣሚው ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

ሕክምናዎቹ

 

ማዲያት ምንም እንኳን በጤና ላይ  አደገኛ በሽታ ባያስከትልም  የግለሰቡን የሥነ ልቦና ሁኔታ ሊነካ እንደሚችል ነው ዶ/ር ምሕረቱ ያስረዱት፡፡ ማዲያትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም ጊዜ እና ትዕግስት እንደሚጠይቅ ገልቷል፡፡  የሕክምናው ዋና ዓላማም ቆዳ ላይ የተከሰተውን  ጥቁር ቀለም መቀነስ፣ አዲስ ጥቁረት እንዳይፈጠር መከላከልና የቆዳን ተፈጥሯዊ ቀለም ማስተካከል ነው፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ ምርመራ፣ የፀሐይ መከላከያ፣ ተገቢ የቆዳ እንክብካቤ ወሳኝ ናቸው፡፡

በቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች የሚታዘዙ ዋና ዋና ሕክምናዎችም በቅባት/ክሬም መልክ የሚቀቡ፣ የቆዳ ሕዋሳትን የሚያድሱ፣ የላይኛውን የጠቆረ የቆዳ ሽፋን በልዩ ኬሚካል በማንሳት አዲስ ቆዳ እንዲተካ የሚያደርጉ ፣ የቆዳ የላይኛውን ክፍል በማሸት  የሞቱ ሴሎችን በማስወገድ በአዲስ የመተካት እንዲሁም የጠቆሩ የሜላኒን ክምችቶችን በሌዘር ጨረር የመሰባበር ሂደቶች ናቸው፡፡ ታዲያ ማዲያት በሕክምና ቢቀንስም እንደገና የመመለስ ባህሪ አለው፡፡ ይህም በዋነኛነት ለፀሐይ ጨረር መጋለጥ፣ የሆርሞን ለውጥ፣ የቆዳ መቆጣት እና የቆዳ ሕክምናን በድንገት ከማቋረጥ ጋር ይያያዛል፡፡

 

ማዲያትን የመከላከያ እና የመንከባከቢያ መንገዶች

 

ዶ/ር ምሕረቱ እንደገለጹት የመጀመሪያው የማዲያት መከላከያ መንገድ  የከፍተኛ የፀሐይ ብርሐን ተጋላጭነትን መቀነስ ነው፡፡  ከጠዋቱ አራት ስዓት እስከ ስምንት ሰዓት ያለው ከፍተኛ የፀሐይ ብረሐን ጨረር የሚለቀቅበት  በመሆኑ በዚህ ጊዜ ተጋላጭነትን መቀነስ ተገቢ ነው፡፡ የሥራ ሁኔታ አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር ወደ ውጪ አለመውጣት ይመከራል፡፡ ጥቁር ገበር ያላቸውን ጃንጥላ መያዝ፣ በየቀኑ ደመናማ ቀናትም ቢሆኑ እንኳ ቢያንስ በባለሙያ የታዘዘ  የፀሐይ መከላከያ ክሬም መጠቀም ይገባል፡፡ ይህንንም በየሁለት ሰዓቱ መድገም ያስፈልጋል፡፡

ከባድ የፀሐይ ብርሐን በሚኖርበት ጊዜ ሰፊ ባርኔጣ እና የፀሐይ መነጽር ማድረግም ተመራጭ ነው፡፡  የፊት ቆዳን አለመፈተግ እና ቆዳን በኀይል ማሸት ወይም ጎጂ ኬሚካል ያላቸውን ሳሙናዎች መጠቀምም ማዲያትን ስለሚያባብስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡ ማዲያት የሚያመጡ የወሊድ መከላከያዎችን ከውስጥ ደዌ የጤና ባለሙያ ጋር ተነጋግሮ በሌላ መቀየር ተገቢ ነው፡፡

ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የፊት ማስዋቢያ ወይም የሆርሞን ክሬሞችን መጠቀም ቆዳን ያሳሳል እንዲሁም ማዲያቱን ይበልጥ ሊያባብሰው ስለሚችል በራስዎ ማዲያትዎን ለማጥፋት ከመጀመርዎ በፊት የቆዳ ሕክምና ባለሙያ (Dermatologist) ማማከር ተመራጭ እንደሆነ ባለሙያው መክረዋል፡፡

      

መረጃ

ጤናማ ቆዳ እንዲኖረን  ማስወገድ የሚገቡን ዋና ዋና ድርጊቶች ፡-

* ፊትን አዘውትሮ በሙቅ ውኃ አለመታጠብ

ፊትን አዘውትሮ በሙቅ ውኃ መታጠብ ቆዳችን ራሱን ለመጠበቅ የሚያመርተውን ተፈጥሯዊ ዘይት ጠርጎ ያጠፋዋል፡፡ ይህም ቆዳችን ከመጠን በላይ እንዲደርቅ፣ እንዲቆጣ እና ለቶሎ ማርጀት (መሸብሸብ) እንዲጋለጥ ያደርጋል፡፡

 

* ሜካፕን ሳይታጠቡ መተኛት

ቀኑን ሙሉ የዋለውን ሜካፕ፣ አቧራና ላብ ሳይታጠቡ መተኛት የቆዳ ቀዳዳዎች እንዲደፈኑ ያደርጋል፡፡ ይህም ቆዳ በቂ አየር እንዳያገኝ በማድረግ  ለቆዳ መገርጣት ምክንያት ይሆናል፡፡

* ብጉርን መጭመቅ ወይም መንካት

በፊት ላይ የሚወጡ ብጉር ወይም እብጠቶችን በእጅ መጭመቅ፣ መቧጨር ወይም በተደጋጋሚ መንካት በእጃችን ላይ ያሉ ባክቴሪያዎች ወደ ቆዳ ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይህም ኢንፌክሽን በመፍጠር ጥቁር ጠባሳ ፊት ላይ ይተዋል፡፡

* ፊትን በፎጣ ወይም በልብስ ማዳረቅ

የፊት ቆዳ በጣም ስስ  በመሆኑ ፊትን ከታጠቡ በኋላ በደረቅ ፎጣ ወይም በልብስ መጥረግ እንዲላላጥ ያደርጋል፡፡ ያለ ዕድሜም የቆዳ መሸብሸብን ያፋጥናል፡፡

* በቂ ውሃ አለመጠጣትና ያልተመጣጠነ ምግብ

በቀን ውስጥ የምንጠጣውን የውኃ መጠን መቀነስ፣ ጣፋጭ እና ቅባት የበዛባቸው ወይም የታሸጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ የፊት ቆዳን ስለሚጎዱ እነዚህን ልማዶች ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ በቀን ቢያንስ ከሰባት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውኃ መጠጣት እና አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማዘውተር ይመከራል፡፡

 

* በቂ እንቅልፍ አለማግኘት

በቂ እንቅልፍ አለመተኛት ማለትም በቀን ውስጥ ከሰባት ሰዓት በታች መተኛት የዐይን ስር መጥቆርንና የቆዳ መገርጣትን ያመጣል፡፡

 

ምንጭ፡- ማዮ ክሊኒክ (Mayo Clinic) እና ዌብ ኤምዲ (WebMD)

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here