“ኡቡንቱ”

0
78

በጠዋቱ የጭስ ሽታ እና በቡና ጸሎት የሚነቃውን ጥንታዊውን የኢትዮጵያ መንደር እስኪ እናስታውስ። አሮጊቷ እናት ሲነጋ ቡና አፍልተው በረከቱ እንዲተርፍ ጎረቤትን ሳይጠሩ ጽዋውን አያነሱም።

በአጨዳ ወራት “ደቦ” ሳይጠራ፣ በደስታና በሀዘን “ዕድር” ሳይሰበሰብ፣ የአንዱ ችግር የሁሉም ሳይሆን የኖረበት የታሪክ ዘመን አልነበረም። አበው “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል” ሲሉ የተናገሩት እንዲሁ ለሆድ ብለው አልነበረም፤ የህልውናችንን ዋነኛ ምስጢር ጠንቅቀው ስለተረዱ እንጂ።

በኢትዮጵያዊው ማኅበረሰብ መለኪያ አንድ ሰው “ሰው” የሚባለው በግል ሀብቱ ወይም በብቸኛ ዝናው አልነበረም፤ ይልቁንም “ከሰው ጋር ባለው ሰውነቱ” ብቻ ነበር።

“ሰው መሆን” የሚባለው ጥልቅ ባሕላዊ እሴታችን ማኅበራዊ ትስስር የሕይወት እስትንፋስ መሆኑን ያበስራል። እኛ ጋር ደስታም ሆነ ሀዘን ብቻውን አይከወንም፤ ተካፍሎ ማለፍ እንጂ።

ዛሬስ? ያ የተከበረ የአብሮነት አጥር ፈርሶ በረጃጅም የግለኝነት ግንቦች ተተክቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በሺዎች የሚቆጠሩ “ተከታዮች” እያሉን በገሃዱ ዓለም ግን ሳሎናችን ውስጥ በብቸኝነት የምንታፈንበት ዘመን ላይ ደርሰናል። “እኔ ብቻ ካገኘሁ ሌላው ቢጠፋ ግድ የለኝም” የሚል በሽታ ትናንት የነበረንን የጋራ ማዕድ ነጥቆን የጥላቻ፣ የፍርሃትና የመከፋፈል እስረኛ አድርጎናል።

ይህ የእኛ ምድር ሰቆቃ ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም የተዘፈቀበት ጥልቅ የባዶነት አዘቅት ነው። ታዲያ ከዚህ አደጋ ለመዳን የባህር ማዶ ንድፈ-ሐሳቦችን ማሰስ አያስፈልገንም፤ መፍትሔው በደማችን ውስጥ በጥቁር አፍሪካዊ ማንነታችን መሠረት ላይ አለ።

ይኸውም የምዕራቡ ዓለም ካቆመው የቀዘቀዘ የግለኝነት አምልኮ በተቃራኒ መላው አፍሪካ ለዓለም ያበረከተው ሕያው መድኃኒት ነው – ኡቡንቱ!

በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት «አስባለሁ፤ ስለዚህ አለሁ» በማለት የዘመናዊውን ዓለም የግለኝነት  መሰረት ጣለ።

ይህ አስተሳሰብ ሰውን ራሱን የቻለ ገለልተኛ ደሴት አድርጎ ቀረጸው።

ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ግን የሰው ልጅ ያተረፈው ነገር ቢኖር በቴክኖሎጂ የተሳሰረ፣ በስሜት ግን እጅግ የተነጣጠለና በብቸኝነት የተጠቃ ማኅበረሰብን ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ብቸኝነትንና ማኅበራዊ መነጠልን ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ብሎ ባወጀበት በዚህ ዘመን፣ ከመካከለኛው እና ደቡብ አፍሪካ ምድር የሚፈልቀው ጥንታዊው የ”ኡቡንቱ” ፍልስፍና ለዓለማችን እጅግ አስቸኳይ መድኃኒት ሆኖ ብቅ ብሏል።

ኡቡንቱ ለዴካርት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ አጭርና ግልጽ ነው፦ «እኔ የሆንኩት አንተ ስለኖርህ ነው!» ይላል።

“ኡቡንቱ” የሚለው ቃል የመጣው ከደቡብ አፍሪካው የዙሉ እና የሾሳ  አባባል ሲሆን ሙሉ ሐረጉ «Umuntu ngumuntu ngabantu» ይላል። ቀጥተኛ ፍቺውም፦ “አንድ ሰው ሰው የሚሆነው በሌሎች ሰዎች አማካኝነት ነው” ማለት ነው።

ኬንያዊው ታዋቂ ፈላስፋና የሃይማኖት ምሁር ፕሮፌሰር ጆን ኤስ. ምቢቲ  እ.ኤ.አ በ1969 ባሳተሙትና አህጉራዊ ድንቅ ስራ በሆነው የአፍሪካ ሀይማኖት እና ፍልስፍና በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እውነት እንዲህ ሲሉ ያሰፍሩታል፦ “እኛ ስላለን እኔ አለሁ፤ እኔ ስላለሁም እኛ አለን።”

በኡቡንቱ እይታ ሰው ብቻውን ፍጹም ሊሆን አይችልም። የሰው ልጅ ሰብአዊነት፣ ክብሩ፣ ደስታው አልፎ ተርፎም ቁሳዊ ስኬቱ ከሚኖርበት ማኅበረሰብ ጋር ባለው ጤናማ ትስስር ብቻ ይለካል። የአንዱ መራብ የሁሉ ረሃብ፣ የአንዱ ውርደት የሁሉ ውርደት፣ የአንዱ ስኬት ደግሞ የሁሉ ድል ነው።

የኡቡንቱ ፍልስፍና ረቂቅ የቤተ-መጻሕፍት ጽንሰ-ሐሳብ ብቻ ሆኖ አልቀረም። ደቡብ አፍሪካ ከአስከፊው የአፓርታይድ (የዘረኝነት) አገዛዝ ስትወጣ ወደ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ የበቀል ጦርነት እንዳታመራ የታደገው ይኸው እሴት ነበር።

የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ “ነገ ያለ ይቅርታ አይታሰብም” በተሰኘው  መጽሐፋቸው የደቡብ አፍሪካን የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን  የመሩበት ዋነኛ መርህ ኡቡንቱ እንደነበር ያብራራሉ።

ቱቱ  “ኡቡንቱ ማለት የኔ ሰብአዊነት ከአንተ ሰብአዊነት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን ማወቅ ነው። ሌላውን ሰው ሳዋርድ ራሴን አዋርዳለሁ” ብለዋል።

ኔልሰን ማንዴላም ቢሆኑ ለ27 ዓመታት ያሰሯቸውን ጨቋኞች በበቀል ሳይሆን በይቅርታና በአብሮነት አቅፈው አገሪቱን ወደ አንድነት የመሩት በዚሁ በደማቸው ውስጥ በነበረው የኡቡንቱ ባህል ተመርተው ነው።

ኡቡንቱ ቅጣት ተኮር ፍትህን  ወደ ፈዋሽ እና አቃፊ ፍትህ  የመቀየር ተዓምራዊ አቅም አለው።

በአካዳሚው ዓለም በኩል የደቡብ አፍሪካው ፈላስፋ ሞጎቤ ራሞሴ “አፍሪካዊ ፍልስፍና በኡቡንቱ” በተሰኘው የምርምር መጽሐፋቸው ኡቡንቱ ሥነ-ምግባራዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የዲሞክራሲ፣ የአመራር እና የአካባቢ ጥበቃ ፍልስፍና እንደሆነ በማስረጃ አሳይተዋል።

በተጨማሪም በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከ85 ዓመታት በላይ የተካሄደውና በዓለም ላይ ረጅሙ የተባለው “የጎልማሶች እድገት ጥናት” ያረጋገጠው እውነት የኡቡንቱ ማረጋገጫ ነው።

ለሰው ልጅ ረጅም ዕድሜ፣ ጤና እና እውነተኛ ደስታ ዋነኛው ቁልፍ ሀብት ወይም ዝና ሳይሆን ጥልቅ ማኅበራዊ ትስስር እና ፍቅር መሆኑን ነው። ግለኝነት ሰውን ለጭንቀትና ለልብ ህመም ሲዳርግ አብሮነት እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ግን የሰውን ልጅ የመኖር ተስፋ ያረዝማሉ።

ለዛሬው ዓለም እና ለእኛ ምን ያስተምረናል?

ዛሬ ዓለማችን በፖለቲካ ፅንፈኝነት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ እና በራስ ወዳድነት እየታመሰች ነው። “እኔ ካገኘሁ ሌላው ቢጠፋ ግድ የለኝም” የሚለው የካፒታሊዝም ስግብግብነት ዓለማችንን ወደ ከፋ የሀብት ልዩነትና የተፈጥሮ ውድመት እየነዳት ይገኛል።

በአገራችንም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ የሚታዩ ግጭቶችና መከፋፈሎች መሰረታቸው የሌላውን ህመም እንደ ራስ አለመቁጠር ነው። ኡቡንቱ ዛሬም ድረስ ቆም ብለን እንድናስብ ይጠይቀናል። ጎረቤትህ ተርቦ ያንተ ማዕድ ሙሉ ሊሆን ይችላል? የሌላው ወገን ሰብአዊ መብት ተገፎ ያንተ ነፃነት ዘላቂ ይሆናል? ይለናል።

ኡቡንቱ ጥንታዊ የአፍሪካ ስጦታ ቢሆንም መልእክቱ ግን ዘመናትን የሚሻገር ዓለም አቀፍ እውነት ነው። ሰው መሆን የሚቻለው ከሰዎች ጋር በመኖር ብቻ ነው።

ሌላው ሲስቅ አብሮ መሳቅ፣ ሌላው ሲያለቅስ አብሮ ማልቀስ፣ የሰው ልጅ መከራ የጋራ መከራ መሆኑን አምኖ መቀበል – ይህ የኡቡንቱ መንገድ ነው።

ዓለም ከገባችበት የብቸኝነት እና የጥላቻ አዘቅት የምትወጣውም “እኔ” ከሚለው ጠባብ ቅጥር ወጥታ “እኛ” ወደሚለው ሰፊው የአፍሪካዊ የሰብአዊነት አደባባይ ስትመለስ ብቻ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያችንም ሆነች መላዋ ዓለም ከገባችበት የፖለቲካ ንትርክ፣ የደም መፋሰስና የመነጠል አባዜ የምትድነው ይህንን የቀደምት አባቶቻችንን አደራ ስታድስ ብቻ ነው።

ኡቡንቱ ለደቡብ አፍሪካውያን ብቻ የተተወ ጽንሰ-ሐሳብ ሳይሆን ለእኛም ለኢትዮጵያውያን የዕድራችን፣ የደቧችን እና በማዕድ የመካፈላችን ጥልቅ መንፈሳዊ ቋንቋ ነው።

የወንድምህ ወይም የእህትህ ደም በከንቱ ሲፈስ ያንተ ሰላም ዘላቂ ሊሆን አይችልም፤ የጎረቤትህ ጎጆ ሲፈርስም ያንተ ቤት ዋስትና አይኖረውም። እውነተኛው ድል ሌላውን ረግጦ ማለፍ ሳይሆን በሌላው ህመም ውስጥ የራስን ሰብአዊነት ማግኘት ነው።

ማረፊያ

የኡቡንቱ መሠረታዊ መርህ

“ኡቡንቱ ማለት እኛ ሰው መሆን የምንችለው በሌሎች ሰዎች ሰብአዊነት በኩል ብቻ መሆኑን ማመን ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ የምናሳካው ማንኛውም ነገር የሌሎችም ሰዎች ድካም እና አስተዋጽኦ ውጤት ነው፡፡” ኔልሰን ማንዴላ

“የኡቡንቱ መንፈስ ያለው ሰው ልበ-ክፍት እና ለሌሎች ተደራሽ ነው፤ የሌሎች ብልጽግና  እና  መልካምነት አያስፈራውም፡፡

ምክንያቱም የራሱ ክብር እና ጥንካሬ ከማኅበረሰቡ ክብር የመነጨ መሆኑን ያውቃል፡፡”

ሊቀ ጳጳስ  ዴስሞንድ ቱቱ (ስለ ኡቡንቱ ባሕርይ የተናገሩት)

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here