ከኦሃዮ አነስተኛ ከተማ ተነስታ የዓለምን የሥነ-ጽሑፍ መንበር የተቀዳጀችው ቶኒ ሞሪሰን ወይም ክሎኢ አርዴሊያ ዎፎርድ ቃላትን የጥበብ፣ የነፃነት፣ የታሪክ እና የሰብዓዊነት ድምፅ ያደረገች ታላቅ ደራሲ ናት፡፡ እ.አ.አ በ1993 ዓለም አቀፉን የሥነ ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት በመቀበል የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አሜሪካዊት ሴት በመሆን የሥነ ጽሑፍ ታሪክን በአዲስ መልክ ፅፋለች፡፡
በአውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር የካቲት 18/ 1931 በሎሬን፣ ኦሃዮ የተወለደችው ክሎኢ አርዴሊያ ዎፎርድ ያደገችው በወላጆቿ እንክብካቤ ነው፡፡ መኖሪያ ቤታቸው በጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ተረት፣ ዘፈኖች እና በታሪክ የተሞላ ነበር፡፡ ይህም ገና በለጋ እድሜዋ ለሥነ ጽሑፍ ልዩ ፍቅር እንዲያድርባት አድርጓል፡፡ እንደ ጄን ኦስቲን እና ሊዮ ቶልስቶይ ያሉ የዓለም ታላላቅ ደራሲያንን መጻሕፍትንም ታነብ ነበር፡፡ በ12 ዓመቷ የካቶሊክ እምነትን ከተቀበለች በኋላ አንቶኒ የሚለውን የክርስትና ስሟን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ እና በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የኮሌጅ ቆይታዋ ወደ “ቶኒ” በመቀየር በዓለም የምትታወቅበት መጠሪያዋ አድርጋለች፡፡
በሎሬን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በላቲን እና በትያትር ንቁ ተሳታፊ የነበረችው ቶኒ እ.አ.አ በ1949 በታዋቂው የጥቁሮች የትምህርት ማዕከል ወደሆነው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ በኢንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን እ.አ.አ በ1953 አጠናቃለች፡፡ እ.አ.አ በ1955 ደግሞ ከታዋቂው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡
ቶኒ እ.አ.አበ1958 በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ታስተምር በነበረበት ወቅት ከጃማይካዊው አርክቴክት ሃሮልድ ሞሪሰን ጋር ትዳር ልትመሰርት ችላለች፡፡ ሃሮልድ እና ስላቭ የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆችን ያፈሩ ቢሆንም ከስድስት ዓመታት የትዳር ቆይታ በኋላ ፍቺ ፈጽመዋል፡፡
ቶኒ ትዳሯ ቢፈርስም ብቻዋን ሁለቱን ልጆቿን እያሳደገች በቀን በሕትመት ድርጅት በኤዲተርነት ስትሠራ ነበር፡፡ በትርፍ ጊዜዋ ደግሞ የጥቁር ማሕበረሰብን ውስጣዊ ሕመም፣ የባርነትን ጠባሳ እና የሴቶችን ተጋድሎ በጥበብ ገልጻለች- በልብ ወለድ፡፡ እ.አ.አ በ1970 የጻፈችው ዘ ብሉ አይ (The Bluest Eye ) የመጀመሪያው ልብ ወለድ መጽሐፏ ሲሆን ያደገችበትን የማሕበረሰብ የውበት መለኪያዎች እና በጥቁር ሕፃናት ላይ የሚያደርሱትን የሥነ-ልቦና ጫና የሚያሳይ ነው፡፡
በሁለት ጥቁር ሴቶች መካከል ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት እና የማሕበረሰብ ጫና የሚዳስሰው ሱላ (sula)የተሰኘው መጽሐፏን ደግሞ እ.አ.አ በ1973 ነበር ለሕትመት ያበቃችው፡፡ እ.አ.አ በ1977 የጻፈችው ሶንግ ኦፍ ሰለሞን ( Song of Solomon ) የተሰኘው ድርሰቷ ደግሞ የአፍሪካ አሜሪካዊያንን ማንነት እና ታሪክ የሚመረምር ነበር፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያጎናጸፋት ሥራዋ ነበር፡፡
በባርነት ዘመን የነበረውን አሰቃቂ ሕይወትን፣ የነጻነት ተጋድሎ እና የልጇን ታሪክ ዳሷል የሚባለው ቢላቭድ መጽሐፏ እ.አ.አ በ1987 ነበር የታተመው፡፡ ይህ ሥራዋ በ1988 የፑሊትዘር (Pulitzer Prize) ሽልማትን እንድታገኝ አድርጓል፡፡ ፑሊትዘር ኦርጋናይዜሽን ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ሽልማቱ በአሜሪካ የጋዜጠኝነት፣ የሥነ-ጽሑፍ እና የሙዚቃ ቅንብር ዘርፎች ከፍተኛው ብሔራዊ ክብር ተደርጎ የሚወሰድ ዓመታዊ ሽልማት ነው፡፡
ይህ ቢላቭድ የሚለው ሥራዋ በጎርጎሮሳዊያኑ 1998 ደግሞ ወደ ፊልም ተቀይሮ ኦፕራ ዊንፍሬይ መተወኗን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቶኒ ሞሪሰን በዓለም ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ለየት የሚያደርጓት እና ልዩ አሻራ እንዲኖራት ያስቻሏት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለአብነትም ከእሷ በፊት የነበሩ በርካታ ጥቁር ደራሲያን ታሪካቸውን ሲጽፉ ለነጭ አንባቢዎች ማብራሪያ የመስጠት ወይም ታሪካቸውን ከነጮች እይታ አንፃር የማነጻጸር አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ ቶኒ ሞሪሰን ግን ድርሰቶቿን የጻፈችው ሙሉ በሙሉ በጥቁሮች ሕይወት፣ ባህል፣ ሕመም እና ደስታ ላይ ብቻ በማተኮር ነው፡፡
“እኔ የምጽፈው ነጭ አፕልን እንደማይገልጸው ሁሉ ጥቁር መሆኔን ሳላብራራ ነው” በማለት የታወቀ አቋም ነበራት፡፡ ያልተነገሩና የተረሱ ታሪኮችንም በግጥም ታቀርባለች፡፡ በተለይም የባርነትን አሰቃቂ ገጽታ፣ ጥቁር ሴቶች የሚያልፉበትን ድርብ ጫና (የዘር እና የፆታ መድልዎ) እና የሥነ-ልቦና ጠባሳዎችን በከፍተኛ ጥበብ ገልፃለች፡፡ የምትጠቀማቸው ቃላት የቁስልን ያህል የሚያም ቢሆንም በውስጡ ጥልቅ የሆነ ግጥማዊ ውበት፣ ተረት እና አፈ-ታሪክ የተቀላቀለበት በመሆኑ የአንባቢን የመያዝ ልዩ ኃይል አለው፡፡
በሕትመት ዓለም ውስጥ ለጥቁር ደራሲያን መንገድ መክፈቷ ደራሲ ከመሆኗም በላይ በታዋቂው ራንደም ሃውስ የሕትመት ድርጅት ውስጥ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ዋና ኤዲተር ሆና እንድታገለግል አስችሏታል፡፡ በዚህ ኃላፊነቷ እንደ ሙሐመድ አሊ፣ አንጄላ ዴቪስ እና ሁይ ኒውተን ያሉ ታዋቂ ደራሲያን መጻሕፍቶቻቸው እንዲታተሙ ትልቅ መንገድ ከፍታለች፡፡
ቶኒ በመጻሕፍቷ ውስጥ ያሉትን እንደ ድህነት፣ ዘረኝነት፣ አስገድዶ መድፈር እና ማንነትን ማጣት ያሉ ከበድ ያሉ የሕይወት እውነታዎችን ሳትፈራ በግልጽ አንስታለች፡፡ ስለሆነም ሥራዎቿ በዓለም ዙሪያ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በስፋት ለጥናት እና ለትምህርት ሥርዓቱ( ካሪኩለም) አካል መሆን የቻሉ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ቶኒ የእነዚህ ሥራዎቿ ድምር ውጤት እ.አ.አ በ1993 በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የሚሰጠውን የኖቤል ሽልማት እንድታገኝ በማድረግ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አሜሪካዊት ሴት እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በዚህም የዘር እና የፆታ ግንቦችን ሰብራለች፡፡
የእንግሊዘኛ ቋንቋን የመጠቀም ችሎታዋ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የኖቤል ኮሚቴው “በጽሑፎቿ ውስጥ ያለው ቋንቋ ነፃ አውጪና ሕያው ነው!” ሲል አድንቋታል፡፡ የኖቤል ኮሚቴው ሽልማቱን የሰጠበትን ምክንያት ሲያብራራም “ራዕይ የታከለበትና የታሪክ ጥልቀት ያለው ድርሰቷ የአሜሪካን እውነታ ሕያው በሆነ መንገድ ስለሚገልጽ” በሚል ነበር፡፡ ቶኒ ነሐሴ5/ 2019 (እ.አ.አ.) በኒው ዮርክ ሕይወቷ ቢያልፍም ሥራዎቿ ግን ለዘላለም ሕያው ኾነው ይኖራሉ፡፡
የኖቤል ሽልማት፡-
ኖቤል በዓለማችን ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ሽልማቶች አንዱ ነው፡፡ እ.አ.አ. በ1895 በስዊድናዊው የኬሚስትሪ ባለሙያ፣ ኢንጂነር እና የዳይናማይት ፈጠራ ባለቤት አልፍሬድ ኖቤል የኑዛዜ ቃል መሠረት ተመሰረተ፡፡ ሽልማቱ የተጀመረው እ.አ.አ በ1901 ሲሆን በየዓመቱ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በየዘርፋቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ይሰጣል፡፡ ሽልማቱ የሚሰጠው በፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሕክምና፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሰላም እና በኢኮኖሚክስ ዘርፍ የላቀ ውጤት ላመጡ ነው፡፡
በርካታ ሰዎች አንድ ተሸላሚ ከተሸለመ በኋላ ወንጀል ቢሠራ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጽም ሽልማቱን ይነጠቃል ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ኖቤል ፋውንዴሽን ሕግ የተከለከለ ነው፡፡ በአልፍሬድ ኖቤል ኑዛዜም ሆነ በኖቤል ፋውንዴሽን መመሪያ አንቀጽ 10 ላይ ሽልማትን የመንጠቅ፣ የመሰረዝ ወይም ውሳኔውን የመቀየር ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለም፡፡
የኖቤልን ሽልማት እንደ ኔልሰን ማንዴላ፣ ኮፊ አናን፣ ዎሌ ሶዪንካ፣ ዐቢይ አሕመድ እና በጥቅሉ 30 አፍሪካዊያን መጎናጸፋቸውን የኖቤል ፋውንዴሽን ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
መረጃ
በአሁኑ ዘመን በዓለማችን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎችን በመሸጥ እና አዳዲስ የሀሳብ አድማሶችን በመክፈት ላይ ያሉ ሴት ደራሲያን እና ስራዎቻቸው፦
*ጄ.ኬ. ሮውሊንግ፡- “የሃሪ ፖተር” መጽሐፍት ስብስብ (Harry Potter”)ይህ ሥራዋ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ እና የቅዠት (Fantasy) ሥነ-ጽሑፍን የቀየረ ሥራ ነው፡፡ ከ600 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች የታተሙ ሲሆን ወደ85 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡
*ማርጋሬት አትዉድ፦ “ዘ ሀንድ ሜድስ ቴል” (The Handmaid’s Tale) የሚለው ሥራዋ የወደፊቱን ጨለማ ዓለም እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና የምታሳይበት፣ ወደ ታዋቂ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም የተቀየረ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሀፉ 10 ሚሊዮን ኮፒ ተሽጧል፡፡
*ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቺ፡- “ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን” (Half of a Yellow Sun) እና አሜሪካናህ (Americanah) በሚሉ ጽሑፎች ይህች ናይጄሪያዊት ደራሲ በዘመናዊ የአፍሪካ ሥነ-ጽሑፍ፣ ስለ ባሕል፣ ዘረኝነት እና ሴትነት (Feminism) በመጻፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆናለች፡፡ ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን መጽሐፍ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከ800ሺህ በላይ ቀጅ የተሸጠ ሲሆን ወደ35 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ አሜሪካናህ የሚለው ደግሞ ወደ አ500ሺህ ቅጂ ሲታተም በ25 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡
*አሩንዳቲ ሮይ ፦ “ዘ ጋድ ኦፍ ስሞል ቲንግ”(The God of Small Things) — የማን ቡከር ሽልማትን ያገኘችበት እና በሕንድ ያለውን የመደብ ሥርዓትና የቤተሰብ ምስጢር የምታሳይበት ድንቅ መጽሐፏ ነው፡፡ በዓለም ላይ ስምንት ሚሊዮን ቅጅ ተሸጧል፡፡
ምን|ጭ፡- አማዞን ድረገጽ
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


