ኢቶሻ ብሔራዊ ፓርክ

0
51

 ኢቶሻ ብሔራዊ ፓርክ  የሚገኘው በናሚቢያ ሰሜናዊ ግዛት ነው፡፡ የተመሰረተውም እ.አ.አ መጋቢት 22 ቀን 1907 ሲሆን በይፋ ብሔራዊ ፓርክ መሆኑ የተበሰረው ደግሞ እ.አ.አ በ1967  ነው፡፡

የፓርኩ ስፋትም 22 ሺህ 270 ኪሎ ሜትር ስኩየር ተለክቷል፡፡ ወደ ፓርኩ ለማምራት ከናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ ተነስቶ ኢቶሻ (ትልቅ ነጭ ቀጣና) የተሰኘው ስፍራ መድረስ ይቻላል፡፡

ፓርኩ በቀደሙት ዘመናት ሐይቅ የነበረበት ስፍራ ነው፡፡ ሆኖም ሐይቁ  በመድረቁ  ነጭ አሸዋ ተነጥፎበት የተንጣለለው ደረቅ ሜዳማ ስፍራ ከዕጽዋት – ድርቅ ተቋቋሚ እሾሀማ ቁጥቋጦ እና የግጦሽ ሳር ለብሶ ይታያል፡፡  ለዝሆኖች ጥላ የሚሆኑት ኮሎፎስፐርመም ሞንፓኒ የተሰኙት የዛፍ አይነቶች የቀጣናው ጌጦች ናቸው፡፡

ከዱር እንስሳት ትልልቅ እና ትንንሽ 114 አጥቢ እንስሳት መገኘታቸው ተረጋግቷል፡፡  ከእነዚህም ውስጥ አንበሳ፣ ዝሆን፣ አቦ ሸማኔ፣ ጅብ…ይገኙበታል፡፡ ከአዕዋፍ 350 ዝርያዎች መገኘታቸውን ድረ ገጾች አስነብበዋል፡፡ ለጎብኝዎች  ተመራጩ ወቅት ከግንቦት እስከ  ጥቅምት ያለው የበጋ ጊዜ ነው፡፡ ከሕዳር እስከ ሚያዝያ ያሉት ወራት ዝናባማ እና ሞቃት ሲሆኑ በሰፊው ሜዳ ውኃ ስለሚተኛ ፍላሚንጎ የተሰኙት አዕዋፍ  መናኸሪያ ይሆናል፡፡

ፓርኩ ስድስት ማረፊያዎች አሉት፡፡ ማረፊያዎቹም በድንበር ላይ የተገነቡ ሲሆን የተናጠል እና የጋራ ማረፊያ፣ ማብሰያ እና የመታጠቢያ ክፍሎች ተዘጋጅተውላቸዋል፡፡ በፓርኩ ደቡባዊ አዋሳኝ ቀጣናም የድንኳን ማረፊያዎች፣ የፎቶ ግራፍ ማንሻ ድብቅ ስፍራዎች ተዘጋጅተው ጎብኝዎችን ይጠባበቃሉ፡፡

ለዘገባችን በመረጫ ምንጭነት፦ ኢቶሻ ናሽናል ፓርክ፣ ኔቸር ትራብል ናሚቢያ እና ትሪሊስት ድረ ገጾችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here