የሠላሳ ሁለት ዓመቱ ቻይናዊ በከፈተው የጀርባ መቧጨሪያ አገልግሎት መስጫ ሳሎን ሕይወቱን እየመራ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ዣንግ ዚያ ኦቻኦ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሰባት ያህል ሥራዎችን በመተዳደሪያነት ሊሰማራባቸው ከአንዱ አንዱ እየቀያየረ ሞክሯቸዋል፤ ግን እንዳሰበው አዋጪ አልሆኑለትም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሚስት የባሏን ጀርባ ስትቧጭር ይመለከታል፡፡ ይህንኑ ሁነት እንደ እርሱ የተመለከቱ የሰጡትን አስተያየት ሲያነብም መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ወይም ተቋማትን እንደሚሹ ይረዳል፤ ሥራውንም ይጀምራል፡፡
ዣንግ የመጀመሪያውን የመቧጨሪያ አገልግሎት መስጫ ሳሎን ከፍቶ ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛውን አከታትሎ ይከፍታል – አዋጪነቱን በመገንዘብ፡፡ ሁለቱ የጀርባ መቧጨሪያ አገልግሎት መስጫዎችም በአንድ ወር እስከ 15 ሺህ ዶላር አስገኝተውለታል፡፡ የሥራውን አዋጪነት በማየትም በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች አንድ መቶ መቧጨሪያ ሳሎኖች ለመክፈት ማቀዱን ድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡
በከተሞች የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ውጥረት ያለባቸው መሆኑ ለጭንቀት ማቃለያ መቧጨሪያ አገልግሎቱን ለማስፋፋት እንዲወስን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለትም ተናግሯል፡፡
ተገልጋዮች ከወገባቸው በላይ ራቁታቸውን ሆነው በሆዳቸው ሲተኙ ጀርባቸውን በፕላስቲክ ጥፍር በመቧጨር ለሚሰጥ የአንድ ሰዓት አገልግሎት 45 ዶላር እንደሚያስከፍል ታውቋል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


