ፓሪስ -የብርሃን ከተማ

0
102

የአውሮፓ የባህል ማዕከል፣ የፍቅር መፍለቂያ፣ የጥበብ እና የውበት መዲና ተብላ በብዙዎች የምትሞገሰው ፓሪስ በሴይን ወንዝ ዳርቻ የተንጣለለች ታሪካዊት እና ዘመናዊት ከተማ ናት። ይህች ከተማ ከቀላል የዓሣ አጥማጆች መንደር ተነስታ ዛሬ ላይ የዓለምን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የፋሽን እና የቱሪዝም አቅጣጫ ወደምትቀይር ታላቅ ከተማነት አድጋለች። የፓሪስን ጎዳናዎች መርገጥ በታሪክ ማህደር ውስጥ ወደኋላ እንደመጓዝ፣ በፋሽን ዓለም መድረክ ላይ እንደመራመድ እና በኪነ-ጥበብ ስራዎች ውስጥ እንደመዋኘት ይቆጠራል።

ታሪካዊ አመሰራረት

የፓሪስ ታሪክ የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ (በግምት በ250 ዓ.ዓ) “ፓሪሲ” የተባሉ የኬልቲክ ጎሳዎች አሁን ሴይን ወንዝ መሃል በሚገኘው እና “ኢል ደ ላ ሲቴ” በሚባለው አነስተኛ ደሴት ላይ ሰፍረው የዓሣ ማጥመጃ እና የንግድ መንደር ሲመሰርቱ ነው። ይህች ደሴት ዛሬም ድረስ የፓሪስ ታሪካዊ ማዕከል እና የኖትርዳም ካቴድራል መገኛ ናት።

በ52 ዓ.ዓ አካባቢ ሮማውያን አካባቢውን በጁሊየስ ቄሳር መሪነት ከተቆጣጠሩት በኋላ ከተማዋን “ሉቴሺያ” ብለው ሰየሟት። ሮማውያን በግራው የወንዙ ዳርቻ ላይ ሰፊ ከተማ፣ ፎረሞች (የከተማዋ ማዕከላዊ የሕዝብ መሰብሰቢያ)፣ የሕዝብ መታጠቢያዎች እና አምፊቲያትሮችን ገነቡ። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የሮማውያን ኃይል እየደከመ ሲመጣ ከተማዋ የቀድሞ ስሟን በመውረስ “ፓሪስ” መባል ጀመረች።

በ508 ዓ.ም የፍራንኮች ንጉሥ ክሎቪስ አንደኛ ፓሪስን የፈረንሳይ (የሜሮቪንጂያን መንግሥት) ዋና ከተማ አደረጋት። ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት በተለይም በመካከለኛው ዘመን ከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገች መጣች። በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ (የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ) መመስረት ከተማዋን የአውሮፓ የሃይማኖት እና የትምህርት ማዕከል አደረጋት።

በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ሉዊ 14ኛ እና ተከታዮቹ ዘመን ፓሪስ የፍልስፍና እና የሳይንስ (የብርሃናት ዘመን ወይም Age of Enlightenment) መናኸሪያ ሆነች። በ1789 ዓ.ም የተካሄደው እና የዓለምን ታሪክ የቀየረው ታላቁ የፈረንሳይ አብዮት የጀመረው እና የነደደውም እዚሁ ፓሪስ ውስጥ ነበር። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በባሮን ኃውስማን መሪነት የተካሄደው ታላቅ የከተማ መልሶ ግንባታ፣ የፓሪስን ጠባብ እና ጨለማ ጎዳናዎች ወደ ዛሬዎቹ ሰፋፊ መንገዶች እና ውብ መኖሪያ ሕንፃዎች በመቀየር ከተማዋን “የብርሃን ከተማ” የሚለውን ስሟን አጎናጸፋት።

የቱሪዝም እንቅስቃሴ

ፓሪስ በየዓመቱ በአማካይ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመቀበል በዓለም ላይ ቀዳሚ ከሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷ ናት። የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በጣም የተቀናጀ እና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

የፓሪስ ቱሪዝም ስኬታማ ሊሆን የቻለበት ምክንያት የተሟላ መሠረተ ልማት ስላላት ነው። ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግዙፍነታቸው እና በተሳላጭነታቸው የሚታወቁት የሻርል ደ ጎል እና የኦርሊ አየር ማረፊያዎች አሏት። ከዚህም በላይ በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው የሜትሮ (የከርሰ ምድር ባቡር) ትራንስፖርት ሥርዓት ማንኛውም ጎብኚ ያሰበበት ቦታ በደቂቃዎች ውስጥ በቀላሉ መድረስ እንዲችል ያደርገዋል።

ጎብኝዎች ወደ ፓሪስ የሚመጡት ለዕረፍት ብቻ አይደለም፤ ለስብሰባዎች፣ ለኤግዚቢሽኖች፣ ለባህል ልውውጥ፣ ለጫጉላ ሽርሽር እና ለምግብ ፍለጋ (Gastronomy) ጭምር ነው። የፈረንሳይ ምግብ አዘገጃጀት እና የካፌ ባህል ራሱ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ የከተማዋ ውብ ካፌዎች እና የጎዳና ላይ ምግብ ቤቶች የቱሪዝም እንቅስቃሴው ዋነኛ አካል ናቸው። በሴይን ወንዝ ላይ የሚደረጉ የጀልባ ጉዞዎች  ቱሪስቶች ከተማዋን ለየት ባለ እይታ እንዲጎበኙ ያደርጋቸዋል።

የኢኮኖሚ ሁኔታ

ፓሪስ ከውበቷ እና ከባህሏ ባሻገር በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ማዕከላት አንዷ ናት። መላው የፓሪስ ክልል የፈረንሳይን የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት (GDP) ወደ 30 በመቶ የሚጠጋውን እንደሚያመርት የፓሪስ ይፋዊ የቱሪስት ቢሮ ድረ ገጽ ይገልጻል። ከተማዋ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ትልቁን የኢኮኖሚ ቀጠና ከሚመሰርቱት መነገጃዎች አንዷ ናት።

የፓሪስ የኢኮኖሚ ጥንካሬ በዋናነት የተመሰረተው በታላላቅ የፋይናንስ፣ የንግድ እና የቴክኖሎጂ ማዕከላቱ ላይ ነው። ከከተማዋ መሃል ወጣ ብሎ የሚገኘው እና የአውሮፓ ትልቁ የንግድ ቀጠና የሆነው ʺላ ዴፋንስ” ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን፣ የዓለም አቀፍ ባንኮችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን እና የትላልቅ ኮርፖሬሽኖችን ዋና መሥሪያ ቤቶች በአንድ ላይ በመያዝ የከተማዋ የፋይናንስ ሞተር ሆኖ ያገለግላል። ከዚህ በተጨማሪም ፓሪስ በዓለም ላይ ትልቁ የስታርት-አፕ ግቢ (አያሌ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ያሉበት ማዕከል) የሚባለውን “ስቴሽን ኤፍ” በማስተናገድ ዛሬ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂና የፈጠራ መናኸሪያ በመሆን የነገውን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አቅጣጫ እየቀረጸች ትገኛለች።

በሌላ በኩል ደግሞ የቅንጦት ዕቃዎች ምርት፣ ቱሪዝም እና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት እጅግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። እንደ “ኤልቪአምኤች” (LVMH)፣  “ኬሪንግ” (Kering) እና “ኤል ኦሬል” (L’Oréal) ያሉ የዓለም ግዙፍ የቅንጦት ዕቃዎች እና የመዋቢያ ምርቶች አምራቾች ዋና መሥሪያ ቤታቸውን ፓሪስ ማድረጋቸው ለከተማዋ የገበያ የበላይነት ትልቅ ጥንካሬን ሰጥቷታል። ይህ የንግድ መዋቅር በየዓመቱ ከሚካሄዱት የንግድ ትርኢቶች፣ ታዋቂው የአየር ላይ ሾው (Paris Air Show)፣ ስብሰባዎች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ከሚስበው የቱሪዝም ዘርፍ ጋር በመቀናጀት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ወደ ከተማዋ የኢኮኖሚ ካዝና እንዲፈስ ያደርጋል።

የፋሽን ሁኔታ

“ፋሽን ፓሪስ ውስጥ ይወለዳል፣ ከዚያም ዓለምን ይዞራል” ይባላል። ፓሪስ የከፍተኛ ፋሽን መገኛ እና የዓለም የፋሽን ዋና ከተማ ተብላ የምትታወቅ የዘመናዊ ዘይቤዎች መፍለቂያ ናት። ይህ ስም ዝም ብሎ የተሰጣት ሳይሆን ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በታሪክ ሂደት ውስጥ የዳበረ ነው።

የፓሪስ የፋሽን የበላይነት በዓለም ላይ ካሉ “ታላላቅ አራት” የፋሽን ሳምንታት መካከል የመጨረሻዋ እና የላቀችው በምትባለው የፓሪስ ፋሽን ሳምንት አማካኝነት በየዓመቱ ይረጋገጣል። በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ደማቅ ዝግጅት ላይ የዓለም ታዋቂ ዲዛይነሮች፣ ሞዴሎች፣ ተዋናዮች እና ጋዜጠኞች ከተማዋን ያጥለቀልቋታል፤ እንደ ኮኮ ሻኔል፣ ክርስቲያን ዲዮር፣ ኢቭ ሴንት ሎረን፣ ሁበርት ዴ ጊቫንቺ እና ሉዊ ቩቶን ያሉ የፋሽን ዓለምን የቀየሩ ታላላቅ ዲዛይነሮች የተነሱት እና ታሪካዊ የፋሽን ቤቶቻቸውን የመሠረቱትም እዚሁ ፓሪስ ውስጥ ነው። እነዚህ ብራንዶች ለዘመናት የዘለቀውን የከተማዋን የጥበብና የውበት መሥፈርት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።

በተጨማሪም በአቬኑ ሞንቴኝ፣ ጆርጅ አምስተኛ እና ሻምፕ ኤሊዜ ጎዳናዎች መካከል የሚገኘው እና “ወርቃማው ትሪያንግል” በመባል የሚታወቀው ቀጠና የዓለም እጅግ የቅንጦት የፋሽን ሱቆች መገኛ ነው፤ በዚህ ስፍራ መገበያየት ራሱ የከፍተኛ ማህበራዊ ደረጃ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ የቅንጦት የገበያ ድባብ ከከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት አለባበስ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፤ በጣም ሳይጋነን ቀላል ግን ጥራት ያላቸውን ልብሶች በጥበብ በማቀናጀት የሚታወቀው እና በዓለም ዙሪያ የሚደነቀው የፓሪስ ሴቶች የፋሽን ዘይቤ ፓሪስን ዝም ብላ የፋሽን መሸጫ ሳይሆን በእያንዳንዱ ጎዳናዋ ላይ የምትተነፍስ ሕያው የፋሽን መድረክ ያደርጋታል።

ሌሎቹ የፓሪስ ገፅታዎች

ፓሪስ ከውበቷና ከፋሽኗ ባሻገር በስነ-ጽሑፍ፣ በምግብ ባህል እና በስፖርት ድምቀት ያላት ሚና የጎላ ነው፤ በተለይም የከተማዋ “የግራ ዳርቻ” (Left Bank) እንደ ቪክቶር ሁጎ፣ ኤሚል ዞላ እና ኧርነስት ሄሚንግዌይ ያሉ ታላላቅ ጸሐፊዎች የዓለምን ስነ-ጽሑፍ የቀየሩባቸው ታዋቂ ካፌዎች እና የፍልስፍና ውይይቶች መናኸሪያ ነው። ይህ በካፌዎች ውስጥ የሚንፀባረቀው ማህበራዊ ህይወት ከከተማዋ የላቀ የምግብ አዘገጃጀት (Gastronomy) ባህል ጋር የተሳሰረ ነው፤ እንደ ክሮይሰንት እና ባጌት ያሉ የዱቄት ውጤቶች፣ ምርጥ አይብና ወይኖች እንዲሁም በርካታ የደረጃ ማረጋገጫ የሚሼሊን ኮከብ ያገኙ የቅንጦት ምግብ ቤቶች የፓሪስ መገለጫዎች ናቸው፤ ከዚህም በላይ ከተማዋ የ2024 የክረምት ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን በከፍተኛ ድምቀት ያስተናገደች፣ የሮላንድ ጋሮስ ቴኒስ እና የቱር ደ ፍራንስ ብስክሌት ውድድር ማጠናቀቂያ መድረክ ናት፤ የፓሪስ ሳን ዠርመን (PSG) የእግር ኳስ ክለብ መገኛ በመሆን በዓለም ስፖርት ውስጥ ትልቅ አሻራም አላት።

ፓሪስ ታሪክን ከዘመናዊነት፣ ጥበብን ከኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ፋሽንን ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር አቀናጅታ የያዘች ልዩ ከተማ ናት። የሴይን ወንዝ ድልድዮች፣ የጎዳና ላይ ካፌዎች ሽታ፣ የሙዚየሞቿ ታላቅነት እና የሕዝቦቿ ጥበብ ፓሪስን ዘላለማዊት ከተማ ያደርጓታል። ፓሪስን አንድ ጊዜ የጎበኘ ሰው ትዝታዋ ሁልጊዜም በልቡ ውስጥ አብሮት ይኖራል ይላል የፈረንሳይ ብሐየራዊ ሚዩዚየም ቦርድ መረጃ። ለዚህም ነው ታዋቂው ጸሐፊ ኧርነስት ሄሚንግዌይ “ወጣት ሆነህ ፓሪስ ውስጥ ለመኖር ከታደልክ ከዚያ በኋላ በሕይወትህ ወደፈለግከው ቦታ ብትሄድ ፓሪስ ካንተ ጋር ትኖራለች፤ ምክንያቱም ፓሪስ የሚንቀሳቀስ በዓል ናት” ያለው።

 

 

አጫጭር እውነታዎች

መጎብኘት ያለባቸው ውብ የፓሪስ መስህቦች

ፓሪስ እያንዳንዱ ጥግ ታሪክ እና ጥበብ የሞላበት በመሆኑ ለመጎብኘት ረጅም ቀናትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የሚከተሉት ቦታዎች የከተማዋ መገለጫዎች እና ዋነኛ መስህቦች ናቸው፦

  1. የኤፌል ማማ

በ1889 ዓ.ም ለዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን ማስታወሻነት በጉስታቭ ኤፌል የተገነባው ይህ የብረት ማማ ዛሬ የፓሪስ እና የፈረንሳይ ዋነኛ ዓለም አቀፍ ምልክት ነው። 330 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ማማ ማታ ማታ በሚሊዮን በሚቆጠሩ መብራቶች ሲያበራ የሚፈጥረው ውበት እጅግ አስደናቂ ነው። ጎብኚዎች ወደ ላይኛው ፎቅ በመውጣት መላዋን ፓሪስ ቁልቁል መመልከት ይችላሉ።

  1. የሉቭር ሙዚየም

በዓለም ላይ ትልቁ እና ታዋቂው የጥበብ ሙዚየም ነው። ይህ የቀድሞ የነገሥታት ቤተ መንግሥት የነበረው ሕንፃ ታዋቂዋን የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺን “ሞናሊዛ” ሥዕል ጨምሮ ከ38,000 በላይ ታሪካዊ እና ጥበባዊ ቅርሶችን ይዟል። በግቢው መሃል የሚገኘው የመስታወት ፒራሚድ የጥንታዊ እና የዘመናዊ ሥነ-ሕንፃ ውህደት ማሳያ ነው።

  1. የኖትርዳም ካቴድራል

በፈረንሳይ ጎቲክ ሥነ-ሕንፃ (የሕንጻ ግንባታ ስልት ነው) የተገነባው እና በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥራው የተጀመረው ይህ ካቴድራል የፓሪስ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ወነኛ ማዕከል ነው። በ2019 ዓ.ም በደረሰበት የእሳት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥበብ ታድሶ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።

  1. ሻምፕ ኤሊዜ እና አርክ ደ ትሪዮምፍ

ሻምፕ ኤሊዜ በዓለም ላይ ካሉ ውብ እና ውድ የንግድ ጎዳናዎች አንዱ ነው። የቅንጦት ብራንዶች መገበያያ እና የካፌዎች መገኛ ነው። በዚህ ጎዳና ማጠናቀቂያ ላይ በናፖሊዮን ቦናፓርት ትዕዛዝ ለፈረንሳይ ጀግኖች መታሰቢያነት የተገነባው አርክ ደ ትሪየምፌ ይገኛል።

  1. ሞንማርት እና ሳክሬ-ከር

በከተማዋ ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኘው ሞንማርት የሰዓሊዎች እና የቅንጡ አርቲስቶች መንደር ነው። ጠባብና ጠማማ መንገዶቹ የድሮዋን ፓሪስ ያስታውሳሉ። በኮረብታው አናት ላይ የሚገኘው ነጩ የሳክሬ-ከር ባዚሊካ ውብ እይታን ያቀናጃል።

  1. የቨርሳይ ቤተመንግሥት

ከፓሪስ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኘው ይህ ቤተመንግሥት የሉዊ 14ኛ ፍፁም ንጉሣዊ ሥልጣን እና ድሎት ማሳያ ነው። አስደናቂው የመስታወት አዳራሽ እና ሰፊው የውኃ ምንጭ ያለበት የአትክልት ስፍራ የፈረንሳይን ጥንታዊ ጥበብ ያሳያሉ።

ምንጭ፡-የፓሪስ ክልላዊ መዳረሻ ድረ ገጽ (VisitParisRegion)

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here