መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ ርዕዮተ ዓለማት፣ መንግሥታት ይቀያየራሉ፡፡ በአንጻሩም ሀገር በሀገርነቷ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ሀገር ማናቸውንም ውጣ ውረዶች እያለፈች በሀገርነቷ ጸንታ ትኖር ዘንድ ግን ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጓታል፡፡
ጠንካራ ተቋማት ያሏት ሀገር መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ ርዕዮተ ዓለማት፣ መንግሥታት ቢቀያየሩም በሀገርነቷ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ባንጻሩም ያለ ጠንካራ ተቋማት የምትገነባ ሀገር በአሸዋ ላይ በተሠራ ቤት ትመሰላለች፤ ውጣ ውረድን አልፋ ጸንታ የመኖሯ ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡
የአንዲት ሀገር ተቋማት ጠንካራ ይሆኑ ዘንድ ደግሞ ተቋማዊ ነጻነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሀገር ጸንተው በቆሙ ጠንካራ ተቋማት እየተመራች በጽናት ከዘመን ዘመን ትሸጋገር ዘንድ ተቋማቱ በዕውቀት፣ በሙያዊ ብቃትና በሕግ ብቻ ሊመሩ ይገባል፡፡ ተቋማቱ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው ውሳኔዎቻቸውን በሕግ፣ በዕውቀት እንዲሁም በሙያ ብቃት ተመሥርተው ማሳለፍ ያሻቸዋል፡፡
የተቋማቱ አሠራሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ አሠራሮች ለሕዝብ ይፋ መሆን አለባቸው፤ የተዛቡ ውሳኔዎችም ፈጥነው መታረም ይኖርባቸዋል፡፡
ተቋማት የጥቂት ልሂቃን መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ የብዙኃኑን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የንብረት ባለቤትነት መብትን የሚያከብሩና አካታች መሆንም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተቋማት አገልግሎታቸውን ተደራሽና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መስጠት አለባቸው፡፡ አገልግሎቶችን ከከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ ለሁሉም ዜጋ በእኩልነትና ያለምንም አድልዎ መስጠት ከጠንካራ ተቋማት የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የሥልጣን ክፍፍል እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓት ነው፡፡ የሥልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር ሥርዓት ከሌለ ያልተገደበ ሥልጣን የተሰጠው አካል ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሥራውን ቢጀምር እንኳን በሂደት ዐውቆም ይሁን ሳያውቅ ወደ አምባገነንነት ሊያዘነብል ይችላል፤ የሥልጣን ክፍፍል እንዲሁም ቁጥጥር ሥርዓቱ የተዛባ ከሆነ፡፡
ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ይቻል ዘንድ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው ተቋም አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት አሠራር ሊኖረው ይገባል፡፡
ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ለሕግ ተገዥ ሲሆኑ የሕግ የበላይነት ይሰፍናል፡፡ የሰዎች የበላይነት ቀርቶ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን እንዲሁም ተቋማት የሕግ የበላይነትን ሲያስከብሩ በዜጎችና በመንግሥት መካከል መተማመን ይፈጠራል፡፡ ይህ መተማመን ደግሞ በመንግሥትና በዜጎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር መሠረት ይጥላል፡፡
በመንግሥት እንዲሁም በዜጎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ሲፈጠር ደግሞ ባለሀብቶች ያለምንም ፍርሃት ሀብታቸውን፣ ዕውቀታቸውን እንዲሁም ጉልበታቸውን በልማት ላይ እንዲያውሉ፣ ዕድገት እንዲፋጠን፣ ገበያ እንዲረጋጋ በር ይከፍታል፡፡
የሕግ የበላይነት ሲሰፍን የመከላከያ ኃይል ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ ስለሚሆን የሀገር ጸጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠበቃል፤ የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፡፡ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት በሕንድ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን በመኖሩ ሀገሪቱ በሰላማዊ መንገድ እየተመራች ነው፡፡ በጀርመን ጠንካራ የማዕከላዊ ባንክ ዲሲፕሊንና ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በመኖሩ ሀገሪቱ ከናዚ ውድቀት በኋላ የጸና ሀገረ መንግሥት መሥርታ በዕድገት ጎዳና በመጓዝ ላይ ትገኛለች፡፡
ለኢትዮጵያ ሀገራችን ህልውና እና የጸና ሀገረ መንግሥት ምሥረታም ሁለት የማይነጣጠሉ ምሶሶዎች ያስፈልጉናል፤ የዴሞክራሲና የብቃት ምሶሶዎች፡፡ እነዚህ ምሶሶዎች ደግሞ ባንድ ቀን በአንድ አካል የሚገነቡ አይደሉም፡፡ የረዥም ጊዜ የጋራ ጥረትን ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ምሶሶዎች መጽናት የበኩሉን የመሪነት ሚና መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
በጥቅሉ ሀገር የምትጸናው በጠንካራ ተቋማትና በብቁ አስተዳደር ነው፡፡ ተቋማት በፖለቲካ ታማኞች ብቻ ከተሞሉ ብቃት አልባነት (ሚዲዮክራሲ) ይነግሣል፤ ሚዲዮክራሲ ደግሞ የመንግሥትን አገልግሎት ያዛባል፣ ሙስናን ያበዛል፣ በመጨረሻም ሀገርን ያፈርሳል፡፡ ሀገራችንን ከዘመናት የፖለቲካ ቀውስ አውጥተን ዘላቂ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን!
በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


